1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ተስፋ

ሐሙስ፣ መጋቢት 21 2015

የፌዴራል የሥራና ክህሎት ሚስቴር በመላ አገሪቱ በሚገኙ 70 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከ163 ሺህ በላይ ወጣቶች ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ተመዝግበው ሥልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አስታወቀ። በሲዳማ ክልል በሚገኘው የሀዋሳ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ፣የውጭ የሥራ ስምሪት ለሚያደርጉ ወጣቶች የሥራ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ፡

https://p.dw.com/p/4PVxM
Äthiopien Job Training
ምስል Shewangizaw Wegayoh/DW

የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ተስፋ

ኢትዮጵያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ወደ ውጭ አገራት ለስራ ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ የፌዴራል የሥራና ክህሎት ሚስቴር አስታወቀ፡፡  የሚኒስቴሩ አንድ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊ ለዶቼ ቬለ DW እንዳሉት አሁን ላይ በመላ አገሪቱ በሚገኙ 70 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከ163 ሺህ በላይ ወጣቶች ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ተመዝግበው ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ ፡፡  
በሲዳማ ክልል በሚገኘው የሀዋሳ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ  የውጭ የሥራ ስምሪት ለሚያደርጉ ወጣቶች የሥራ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ፡፡ ወጣት  ብርቱካን በለጠ እና መሠረት ወርቁ በምግብ ዝግጅት ፣ በፅዳት እና  በቤት አያያዝ ሙያዎች በኮሌጁ እየሠለጠኑ ከሚገኙ መካከል ናቸው  ፡፡ በተለይም ወጣት ብርቱካን የውጭ አገር ሥራ የመጀመሪያዋ መሆኑን  ገልጻለች ፡፡  ከወንዶ ገነት ወረዳ በመምጣት በኮሌጁ ሥልጠናውን በመከታተል ላይ እንደምትገኝ የምትናገረው ብርቱካን “ አዚህ የተገኘሁት ለሥራ ጉዞው የሚስፈልገኝን ክህሎት ለመቅሰም ነው ፡፡ ምክንያቱም በቀጣይ ወደ ውጭ አገር በመጓዝ በሥራ ላይ በምሠማራበት ወቅት በራስ የበራሴ እንድተማመን ከማድረጉም በላይ በሥራ ሂደት ሊገጥመኝ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ያስቀርልኛል የሚል አምነት አለኝ “ ብላለች፡፡ 
መሠረት ወርቁ በበኩሏ  ከዚህ ቀደም በደላላ አማካኝነት ባደረገችው ጉዞ ተጠቃሚ ሳትሆን መቀርቷን በማስታወስ “ አሁን በድጋሚ ለመሄድ እየተዘጋጀት እንደምትገኝ ገልጻለች  ፡፡ አሁን የማደርገው ጉዞ እንደከዚህ በፊቱ ሳይሆን የት እንደምሄድ ፣ ምን እንደምሠራ ፣ ምን ያህል እንደሚከፈለኝ ገልፅ በመሆኑ አላሥፈላጊ እንገልትን ያስቀርልኛል “ በማለት ተናግራለች ፡፡  
አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ የሲዳማ ክልል የስራ ክህሎትን ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ናቸው ፡፡ አሁን የተጀመረው የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት በባህሪው ለየት ያለ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ “ ክልላችን ከዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን እየሠራ ይገኛል  ፡፡ በአሁኑወቅት በአራት  የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች 4 ሺህ 252 ወጣቶች እያሠለጠንን እንገኛለን “ ብለዋል    
በአሁኑወቅት ሳውዲአርቢያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ከኢትዮጵያ ሠተኞችን ለመውሰድ ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸውንና እንዳንዶቹም ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸውን የፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚስቴር  አስታውቋል፡፡ 
አነኝህን የሥራ እድሎች ለመጠቀም በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው በሥራና ክህሎት ሚስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ዓለሙ ለዶቼ ቬለ DW  የገለጹት ፡፡ 
አሁን ላይ በመላ አገሪቱ በሚገኙ 70 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከ163 ሺህ በላይ ወጣቶች ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ተመዝግበው ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ አበበ   “ የሥራ ሥምሪት ሥልጠናው ቀደምሲል የነበረውን የዘፈቀደ አካሄድ ያስቀራል ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊን በወጭ አገራት የሚደርስባቸውን እንግልት ለመቀነስ ይረዳል ፡፡ በአጠቃላይ ዘርፉን በማዘመን የዜጎችን ክብር ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል  “ ብለዋል፡፡  
ኢትዮጵያዊያን በተለይ ወደ አረብ አገራት የሚያደርጉት የሥራ ጉዞ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚታዩበት በተደጋጋሚ አየተነገረ ይገኛል ፡፡ የሳውዲአረቢያ መንግሥት በህገ ወጥ መንገድ ገብተዋል በሚል በተለያዩ የአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ያቆያቸው ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውንን አሁን ድረስ ወደ አገር ቤት የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል።

Äthiopien Job Training
ምስል Shewangizaw Wegayoh/DW
Äthiopien Job Training
ምስል Shewangizaw Wegayoh/DW
Äthiopien Job Training
ምስል Shewangizaw Wegayoh/DW

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር