1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የውሃ እና የኃይል እጥረት ተጽዕኖ በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 23 2010

 በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቶች እጥረት በማሕበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ እና በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳርፏል። 

https://p.dw.com/p/33zfD
Flash-Galerie Dürre ohne Ende Äthiopien Landleben im Norden Rural life in Northern Ethiopia
ምስል picture-alliance/Ton Koene

የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት

በኢትዮጵያ በተለይም የገጠሩ የአገሪቱ ክፍል70 ከመቶ አካባቢ የሚሆነው ሕዝብ ይኸውም ከ 10 ሰው ሰባቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ :: ይህን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ በተለይም ለመሰረታዊ ፍጆታም ይሁን ለምጣኔ ኃብት ዕድገት ወሳኝ የሆኑትን የኤሌክትሪክ ኃይል እና ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አገልግሎቱን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመላው ሕብረተሰብ ለማዳረስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈርጀ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን መንግሥት እየገለጸ ነው :: ይሁን እንጂ በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ሌሎችም የኃይል አማራጮች ተሰርተው ከአገር አልፈው እንደ ኬንያ ታንዛንያ ጅቡቲ ሱዳን ፣ ርዋንዳ እና ሌሎችም ጎረቤት የአፍሪቃ አገራት ጭምር ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ አስገኛለሁ የሚሉት የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትም ሆነ የውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር እንኳንስ የገጠሩን የአገሪቱ ክፍል ይቅርና የከተማውንም ሕብረተሰብ የኤሌክትሪክም ሆነ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቶች በተገቢው መንገድ ማዳረስ እንደተሳናቸው ነው ሕብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታውን የሚገልጸው :: የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ መቋረጥ እና የፈረቃ አገልግሎት በአንዳንድ ከተሞችም ለዓመታት ያለ ኃይል አቅርቦት የኤሌክትሪክ መስመሮች በየመንገዱ ተዘርግተው የሚታዩበት ሁኔታ ተቋማቱን በመልካም አስተዳደር እጦት ሲያስወቅሱት መቆየታቸውን የመስኩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ :: እንዲህ ዓይነቱ ውስብስብ ችግር ባልተቀረፈበት ሁኔታ መንግሥት የአገልግሎት ክፍያ የታሪፍ ማሻሻያ ጥናት ማቅረቡ በማሕበረሰቡ ዘንድ  ቅሬታን እንደፈጠረ ይነገራል :: በኢትዮጵያ በአዲሱ ታሪፍ አስፈላጊነት እና በኤሌክትሪክ እና ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ማሻሻያ ስራዎች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን አቶ ብዙነህ ቶልቻን በውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ጠይቀናቸው ነበር :: 
« በኢትዮጵያ አልፎ አልፎ የ ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የሚታይባቸው ሁኔታዎች አሉ :: ይህም በተጠቃሚው ሕብረተሰብ ላይ እንደዚሁም የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥርበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነው :: የኃይል መቆራረጥ እጥረት ችግርን ለመፍታት የማሰራጫ መስመሮችን የማሻሻል ሥራዎች በተለያዩ ከተሞች እየተሰሩ ይገኛሉ :: አንዳንዶቹም ወደመጠያቀቁ ተቃርበዋል :: በአዲስ አበባ በባህር ዳር በመቀሌ በደሴ በድሬዳዋ በጅማ በአዳማ እና በአዋሳ የ8 ከተሞችን የሥርጭት የማከፋፈያ ኔትወርክን የማሻሻል የሙከራ ሥራ እየተሰራ ነው :: በስድስት ተጨማሪ ከተሞችም ማለትም በጎንደር አዲግራት ሻሸመኔ ወላይታ ሶዶ ሐረር እና ደብረማርቆስም የማሻሻያ ሥራ ለመስራት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ::» 

Symbolbild Idee Strom Glühbirne
ምስል colourbox/K. T. Segundo

በኢትዮጵያ ያጋጠመውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የመቆራረጥ ችግር ለማቃለል በ 14 ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ አንድ ሶስተኛ ያህሉ አካባቢ መንግሥት የጀመራቸው የኤሌክትሪክ ማሻሻያ ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸው ታውቋል :: የአየር ንብረት ሲለዋወጥ የሚጠፋውንም የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ አማራጭ ዘዴዎች መቀየሳቸውን አቶ ብዙነህ ገልጸውልናል::
« በአሁኑ ወቅት የንጹህ መጠጥ እጥረትን ለማቃለል በ342 ወረዳዎች በ 24 መካከለኛ ከተሞች እና በ 120 አነስተኛ ከተሞች ላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት የማስፋፋት ሥራ በፕሮግራም ተቀርጾ እየተሰራ ነው :: በዚህም እንቅስቃሴ ከስድስት ሚልዮን የሚልቁ ዜጎችን የንጹሕ መጠጥ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ::» 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና ዋልታ እና ምሰሶ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ የህዳሴ ግድብ የግንባታ እንቅስቃሴም የተለያዩ እክሎች እንደገጠሙት እየተነገረ ነው :: በመንግሥት በጀት እና በሕዝብ ሃብት የግንባታው ሥራ የተጀመረው ይህ ግድብ አሁን በሚታየው የአሰራር ፍጥነቱ በቀጣዮቹ 10 ዓመታትም የመጠናቀቁ ነገር አሳሳቢ መሆኑን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥጋታቸውን ይፋ አድርገው ነበር :: ግንባታው በመከላከያ ብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ / ሚቴክ / አቅም ብቻ ከግብ ሊደርስ እንደማይችልም ተጠቁሟል : : በጣሊያኑ ተቋራጭ ሳሊኒ የሚካሄደው የግድቡ የሲቭል ኢንጂነሪንግ ክፍል ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ ሲገኝ በሚቴክ የሚከናወነው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ ክፍሉ ማለትም የጄኔሬተር እና ተርባይኖች ተከላ ስራው ግን መጓተቱን የውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ባለፈው ሰሞን ይፋ አድርጓል :: ከዓመታት በፊት መንግሥት በነደፈው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሃገሪቱን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማሳለጥ ይሰራሉ እየተባሉ ዘሬም የግንባታ ሥራቸው የተጓተቱ አያሌ ፕሮጀግቶች በተለይም በኃይሉ ዘርፍ ከባድ የኢኮኖሚ ማነቆ መፍጠራቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምሕር የሆኑት ዶክተር ታደለ ፈረደ ያስረዳሉ:: 
«በመጀመሪያ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመንግሥት የተጀመሩ በርካታ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ዕቅዶች ነበሩ :: ይሁን እና ሁሉም በሚባል ደረጃ አልተጠናቀቁም :: በተለይም በኃይል ሥርጭቱ ዙሪያ ግንባታን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን አቅርቦቱን በተገቢው መንገድ ማሻሻል ተገቢ ነው :: የኢነርጂው ዘርፍ አገሪቱ ለነደፈችው የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ስኬት እንዲሁም ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ዋንኛ ግብአት በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው ::አሁን ያሉት ኢንዱስትሪዎች ከውሃ በሚገኝ የሃይል ምንጭ የሚንቀሳቀሱ እንደመሆናቸው ኢንዱስትሪዎች በጥራት እና በብቃት አምርተው በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን በሙሉ አቅም ለመስራት በቂ የኃይል አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል :: የሃይል መቆራረጥ ከአቅማቸው በታች እንዳያመርቱ እና ማሽኖቻቸው እንዲበላሹ በማድረግ ለኪሳራ ይዳርጋቸዋል የስራ አጥ ቁጥርም እንዲበራከት ያደርጋል:: ይህ ችችግር በምጣኔው ሃብት ላይ ከባድ ተጽዕኖ ፈጥሯል ::»
በስኳር እና የተለያዩ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ችግር አሳይቷል በሚልዮን የሚቆጠር ከፍተኛ የበጀት ብክነትም እንዳለበት ተረጋግጧል ተብሎ በተደጋጋሚ በመንግሥት አካላት ሲወቀስ የነበረው ሚቴክ ለግድቡም ሥራ መዘግየት ምክንያት መሆኑ ይፋ ሆኗል :: በቅርቡ እንኳ ግድቡ ከሚያስፈልጉት 16 የ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሁለቱ ብቻ ተተክለው ሙከራ ቢደረግም በቴክኒክ እክል አለመሳካቱ የግንባታውን ሥራ የበለጠ እንዲጓተት አድርጎታል ተብሏል :: በኮንትራት ውሎቹ ላይ ከ አራት ዓመታት በፊት ሁለት ጄኔሬተሮችን በያዝነው ዓመት ደግሞ ቀሪዎቹን በሙሉ የመትከል ሥምምነት ቢኖርም አስካሁን አንዱም ስራ አለመጀመሩን ነው ውስጥ አዋቂ ምንጮች የሚገልጹት:: የውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህን እንደ ኃይል አቅርቦቱ ሁሉ ተመሳሳይ ችግር የሚታይበትን የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትስ ለመፍታት ምን እቅድ ተነድፏል ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ መልስ ሰተውናል :: 
« የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት የሚከሰትበት ሁኔታ እንዳለም ታውቋል:: በተለይም በደረቅ እና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎች አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማቅረብ ማዳረስ የሚቻልበት መርሃ ግብር ተነድፎ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወደ ተግባር የሚገባበት ሂደት ተጀምሯል :: እ.ኤ.አ በ 2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ውስጥ ዕቅዱን መተግበር የሚጀመርበት ሁኔታ አለ :: በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ውስጥ እስካሁን ከ6 ሚልዮን በላይ ዜጎችን የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ::» 

Äthiopien Grand Renaissance Staudamm
ምስል Reuters/T. Negeri

 ለበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል አምርቶ የመሸጥ እቅድ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በሃገር ውስጥ የሚታየውን እጥረት ለመቅረፍ እሳካሁን የተጓዘበት መንገድ የሕብረተሰቡን ችግር ሙሉ በሙሉ መፍታት አልቻለም:: ያም ቢሆን መንግሥት የሃይል እጥረትን ለመቅረፍ ከጎርጎሪዮሳዊው  2010 - 2017 ዓ.ም የሚዘልቅ " ብርሃን ለሁሉም " የተሰኘ መርሃ-ግብር ነድፎ የጀመረው እንቅስቃሴ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል በቀጣዮቹ ዓመታት የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል:: የንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማቃለልም በአነስተኛ ወንዞች ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል ቴክኖሎጂን በመተግበር እና ከፀሃይ ብርሃን ተጨማሪ ሃይል በማመንጨት አገልግሎቱን ለብዙሃኑ ተደራሽ ለማድረግ የተግባር ሥራ መጀመሩ ታውቋል :: ይሁንና በተለይም የኃይሉ ዘርፍ መሰረታዊ መፍትሄ ባላገኘበት ሁኔታ የውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አዲስ የታሪፍ ማሻሻያ ለውይይት ማቅረቡ በሕብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩ አልቀረም :: የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት እና ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ስለዚሁ የሚሉት አለ :: 
« የታሪፍ ማስተካከያ የቀረበበት ዋናው ምክንያት ከዛሬ 12 ዓመታት በፊት ማለትም እ.ኤ.አ በ1998 ዓ.ም የተደረገውን የታሪፍ ለውጥ ማሻሻል በማስፈለጉ ነው :: የኃይል አቅርቦት ገቢ እና ወጭን ለማመጣጠን እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ችግር ለመቅረፍ ተጨማሪ የፋይናንስ ወጭ በመጠየቁ ነው :: ይህንንም ፋይናንስ ለአገልግሎት ከሚቀርበው የኤሌክትሪክ ሽያጭ በተቻለ መጠን በተመጣጣኝ እና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ገቢ መሰብሰብ የሚቻልበት መንገድን ታሳቢ ያደረገ ነው :: ማሻሻያው በሚኒስትሮች ምክርቤት ከመጽደቁ በፊት ጥናት እና ውይይት ላይ ሲሆን ዝቅተኛ ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ተጽዕኖ አይፈጥርም ::ከዚህ ሌላ ከ 50 kw/hr በታች ተጠቃሚ የሚሆኑ ደንበኞች ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ አይኖርም ::»

የኤሌክትሪክ ኃይሉን ሥርጭት እጥረት ለመቅረፍ በየቦታው መንግሥት የጀመራቸው ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ ዛሬም ድረስ ከግንባታ እስከ ጥራት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳለባቸው የመስኩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ:: በቅርቡ እንኳ 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የኮንትራት ስምምነት የተፈረመበት የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ከግማሽ በታች 25 ሜጋ ዋት ብቻ ማመንጨቱ ብዙዎችን ማነጋገሩ አልቀረም :: የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ዶክተር ታደለ ፈረደ በኢትዮጵያ የሚታየው የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት እጥረት እና ተደጋጋሚ መቋረጥ በኢንዱስትሪው ክፍለ-ኢኮኖሚም ሆነ በማሕበረሰቡ የዕለት ተዕለ ኑሮ ላይ መጠነሰፊ ችግር እያስከተለ መሆኑን ይገልጻሉ :: አሁን በኢትዮጵያ የሚታየውን የኃይል እጥረት ለማቃለል የግሉን ኢንቨሥትመንት በዘርፉ እንዲሳተፍ ማድረግ አንዱ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም ዶክተር ታደለ ይመክራሉ:: 
« መንግሥት የኃይል ማምረቱንም የሥርጭቱንም አገልግሎት አጠቃሎ በሞኖፖል መያዙ ለሃይል እጥረቱ ዋና ምክንያት እንደሆነ ይታመናል :: በዚህም ምክንያት ያለውን የተመረተውን እንኳን በበቂ ሁኔታ ማሰራጨት እና ማዳረስ አልተቻለም :: አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር በቅርብ እንደ ኢነርጂ ሴክተሩ ያሉትን ዘርፎች በተወሰነ ደረጃ ወደ ግል ለማዞር የነደፈው ዕቅድ የሚደገፍ ነው :: ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ አንጻር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ቢያንስ ኃይል የማከፋፈሉ ስራ ላይ ቢሳተፍ አሁን የሚታየውን የኢነርጂ አቅርቦት ችግር መቅረፍ ይቻላል :: »

እንዳልካቸው ፈቃደ

አርያም ተክሌ