1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዋሽግተን-ሪያድ ወዳጅነት

ሰኞ፣ የካቲት 22 2013

ግራ ካጋባ ግራ-አጋቢዉ የአጉርሰኝ ላጉርስሁ ወዳጅነት፣ ከሕዝብ ፍላጎት፣ ከየሐገራቱ መሰረት፣ ከመብት ነፃነትም በልጦ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አብነቲቱ የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች እና  የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ተምሳሌይቲ የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት ወዳጅነት ለ76 ዘመናት ፀንቶ መቆየቱ በሆነ ነበር።አልሆነም።

https://p.dw.com/p/3q4SV
Kombobild Joe Biden, US-Präsident & Salman ibn Abd al-Aziz, König Saudi-Arabien

የዋሽግተን-ሪያድ ወዳጅነት፣ የዴሞራሲ-ፈላጭ ቆራጮች ጥምረት


ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት መጠናቀቂያዉ ነዉ።ጦርነቱ ያነደደዉ ዓለም ግን ለቀዝቃዛዉ ጦርነት  ዉሽንፍር እየሰነቀ ነዉ።ዕለቱ፣ በተለይ ለአዉሮጳ-አሜሪካኖች የፍቅር ነዉ።የካቲት 14፣ 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የበረሐማዋ ግን ስልታዊቱ ሰፊ፣ የነዳጅ ቋት ሐገር ንጉስና የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት አሸናፊ፣ ኃያል፣ ሐብታም ሐገር ፕሬዝደንት በዚያ የጦርነት ፍፃሜ ግን የአዲስ ቀዝቃዛ ጦርነት ዋዜማ፣ በዚያች የፍቅር ቀን፣ አል ቡሐይራሕ አል-ሙራ አል ኩብራ-በተባለዉ የግብፅ ጨዋማ ሐይቅ ላይ የሁለቱን ሐገራት ፖለቲካዊ ጋብቻ ፈጠሙ።የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ግድያ ቅሌት የ76 ዘመኑን ጋብቻ ያፈርሰዉ ይሆን? 
«እኔና እርስዎ በፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን በአካልም ተመሳሳይ ነን----» አሉ ንጉሱ ለፕሬዝደንቱ።አልዋሹም።ቁርጥራጭ ክፍለ-ግዛቶችን በጠንካራ ክርናቸዉ ደፍልቀዉ ሰፊዋን በረሐማ ሐገር የመሰረቱት ንጉስ አብዱል አዚዝ ኢቢን አብዱል ረሕማን አል ሳዑድ የሚላወሱት በግድ በምርኩዝ-ድጋፍ ነበር።አርጅተዋል።ወፍረዋልም።
በምጣኔ ሐብት ድቀት፣በፖለቲካ ዉዝግብ፣ በጥቁር ነጮች ፍጅት ግራ ቀኝ ስታወዥቅ የነበረችዉን ትልቅ ሐገር ተረክበዉ ባጭር ጊዜ ከምጣኔ ሐብት ዉድቀት፣ ከርስበርስ ንትርክ አዉጥተዉ ከአስፈሪዉ  ጦርነት ድል አድራጊዎች አንዷ ያደረጉት ፍራንክሊን ዲ ሩዘቬልት የጤና እጦት አዳክሟቸዉ የሚንቀሳቀሱት በተሽከርካሪ ወንበር ነዉ።1945።
ሩዘቬልት ለንጉሱ ከሸለሟቸዉ ስጦታዎች አንዱ ተሽከርካሪ ወንበር ነበር።ንጉሱ ባንፃሩ ፕሬዝደንቱን ለማየት ሲጓዙ በጎችም አስከትለዉ ነበር። አንድ አሜሪካዊ ፀሐፊ «አንድ ንጉስ፣ አንድ ፕሬዝደንት እና ስምንት በጎች» የአረብ-አሜሪካኖችን የግንኙነት መሠረት ጣሉ ይላል።
በ1950ዎቹ የወጡ ዘገቦች እንዳመለከቱት እኒያ፣ ልጣቸዉ የራሰ፣ ጉርጓዳቸዉ የተማሰ አዛዉንታት መሪዎች ባደረጉት ዉል መሠረት አሜሪካኖች የንጉሱን፣ የልጅ፣ የልጅ-ልጅ ዉላጆችን ስልጣን፣ የነዳጅ ቋቲትን ሐገር ደንሕነት ይጠብቃሉ።ነዳጅዋንም እንዳሻቸዉ ይዝቃሉ። 
                       
«ስለ ስብሰባዉ የተሰነደ መረጃ የለም።ይሁንና ሁሉም የታሪክ ተመራማሪዎችና የአሜሪካ መርሕ አዉጪዎች እንደሚስማሙበት የዉይይቱ መሠረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለነገስታቱ ቤተሰብ ከለላ ትሰጣለች።ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ የነዳጅ ሐብቷን ዩናይትድ ስቴትስ እንድታበለፅግ ልዩ ፈቃድ ትሰጣለች።»  
ሁለቱ መሪዎች የዚያን ዕለት፣ እንግሊዞች ግሬት ቢተር ሌክ ከሚሉት የግብፅ ሐይቅ ላይ መሕለቋን ከጣለችዉ የአሜሪካ መርከብ ላይ በዕዉቅ ወጥቤት የበሰለዉን የበግ ሥጋ እያጣጣሙ ያደረጉት ስምምነት በየዘመኑ እንቅፋት አላጣዉም።በአብዛኛዉ በእስራኤል አረቦች ጠብና ጦርነት ሰበብ የሚሻክረዉ ወዳጅነት በተለይ በ1973ቱ ጦርነት ወቅት አረቦች በጣሉት የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ ሰበብ ክፉኛ ተናግቶ ነበር።
አረቦች በተለይም ሳዑዲ አረቢያዎች የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ መጣላቸዉ ያናደዳቸዉ የያኔዉ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን የአሜሪካ ጦር የባሕረ-ሠላጤዉን አረብ ሐገራት የነዳጅ ጉርጓዶችን እንዲቆጣጠር ለማዝመት እስከማቀድ ደርሰዉም ነበር።
የኒከስን የፀጥታ አማካሪ የነበሩት ሐንሪ ኪንሰንጀር «የሠለጠነዉ ዓለም በ8 ሚሊዮን አረመኔዎች መታገቱ ፈፅሞ ተቀባይነት የለዉም» በማለት የደነፉትም ያኔ ነዉ።ይሁንና ኪሲንጀር በተለይ የሶቭየት ሕብረቶችን ማንጃበብ ሲስተዉሉ፣ ያሉትን ባሉ በ3ኛዉ ወር ንጉስ ፈይሰል ዙፋን ስር ሆነዉ «አላማችን ከግርማዊነትዎ ጋር መስራትና ወዳጅነታችን ለረጅም ጊዜ እንዲፀና መጣር ነዉ።» ለማለት ተገድደዋል። 
ዩናይትድ ስቴትስ መስከረም 2001 በአብዛኛዉ በሳዑዲ አረቢያ ተወላጅ አሸባሪዎች በተጠቃች ማግስትም የሪያድ ዋሽግተኖች ወዳጅነት ታጉሎ ነበር።የሪያዶች ዶላር ዋሽግተን ላይ ሲዘረገፍ ግን የነበረዉ ቀጠለ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕም በ2016 የምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት አስፈራርተዉ ነበረዉ።
                                        
«ለሳዑዲ አረቢያ ከለላ እንሰጣለን።ሐብታም ናቸዉ።ንጉሱን እወዳጀዋለሁ።ንጉስ ሰልማንን።እነግራቸዋለሁም ንጉስ ሆይ! ጥቃት የምንከላከልላችሁ እኛ ነን።እኛ ባንኖር ኖሮ ሁለት ሳምንት እንኳን ስልጣን ላይ አይቆዩም።ለጦራችን መክፈል አለብዎት።»
ዴሞክራሲን የመሰረቱት  ግሪኮች «ወርቅ የተጫነች አሕያ ስትገባበት የማይናድ ግንብ የለም።» የሚል አባባል አላቸዉ አሉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ ከነብዙ ችግራቸዉ ግልፅ ናቸዉ።ዶላር ካስገኘ የዴሞክራሲ ቀንዲል ለምትባለዉ ዩናይትድ ስቴትስ ዴሞክራሲ፣ የፕረስ ነፃነት፣ ሰብአዊ መብት፣ምናምን ብሎ መርሕ ከማለት ባለፍ ትርጉም የለዉም።
ትራምፕም ሥልጣን በያዙ ማግስት ከማንኛዉም ሐገር ቀድመዉ የጎበኙት ነዳጅ የሚዛቅበት፣ ለነገስታት-ሹማምንት ዶላር የሚረጭባትን ሐገር ነዉ።ትራምፕ ከሪያድ የሚሽቱን ዶላር ባገኙ ባመቱ ጥቅምት 2018 አሜሪካ ያስጠጋችዉ፣ ሜሪ ላንድ የምታኖረዉ፣ ለአሜሪካ ጋዜጣ የሚሠረዉ ሳዑዲ አረቢያዊ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ኢስታንቡል-ቱርክ ሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ዉስጥ ተገደለ።
የቱርክ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ከሁለቱም በላይ የራስዋ የዩናይትድ ስቴትስ መርማሪዎች እንዳረጋገጡት ገዳዮች የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ያዘዙ፣ ያደራጁ፣በልዩ አዉሮፕላኖች ያዘመቷቸዉ የሐገሪቱ የስልለላ፣የጥበቃና የሕክምና ባለሙያዎች ናቸዉ።ግድያዉ አሳዛኝ፣ አገዳደሉ ሰቅጣኝ ነበር።
የ60 ዓመቱን ጋዜጠኛ ቀጥቅጠዉ ገደሉት።አጥንቱን በመጋዝ ቀርጥፈዉ፣ ስጋዉን በመርዝ አድቅቀዉ ዱቄቱን በተኑት።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስገዳዮችን ሊናገሩ ቀርቶ የምርመራዉን ዉጤት ራሱን አፈኑት።ሲጠየቁ መለሱ «ደንበኛዬን ላጣ? ሞኛችሁን ፈልጉ» እያሉ። 
 «በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለምታወጣልን ሐገር፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ አሻቅቦ በበርሚል 150 ዶላር እንዳይገባ ዋጋዉን እንድትቀንስ ስጠይቅ የቀነሰችልኝን ሐገር ምንም አልናገርም።የነዳጅ ዋጋ አሁን ጥሩ ነዉ።ሳዑዲ አረቢያን ተናግሬ የዓለምን ኤኮኖሚ፣ የሐገራችንን ኤኮኖሚ ማጥፋት አልፈልግም።ጅል አይደለሁም።»
አሜሪካ ዶላር ካየ ጅል አይደለም።ጆ ባይደን አሜሪካዊ ናቸዉ። በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ኃይለኛ ተቀናቃኛቸዉን ትራምፕን ለማሳጣት የሠብአዊ፣ የጋዜጠኛና የመናገር መብት ተቆርቋሪዎችን ጩኸት እንደ ዕጩ ፕሬዝደንት ሞቅ-ደመቅ አድርገዉ ጮኹ።ሥልጣን በያዙ በወሩ  የምርጫ ዘመቻቸዉ ቃል ገቢር መሆኑን ለማረጋገጥ የሪያድ-ዋሽግተን ግንኙነት በዲስ መርሕ መቃኘት አለበት አሉ።
«ትናንትና ከንጉሱ ጋር ተነጋግሬያለሁ።ከልዑሉ ጋር አይደለም።(የግንኙነቱ) ደንቦች መቀየር እንዳለባቸዉ ግልፅ አድርጌላቸዋለሁ።ከፍተኛ ለዉጥ መደረጉን ዛሬና ነገ እናሳዉቃለን።ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን።»
የካቲት 26።አስተዳደራቸዉ ባለፈዉ አርብ ስለጀማል ኻሾጂ ግድያና አገዳደል የአሜሪካ የስልላ ድርጅት ያጠናቀረዉ ዘገባ ይፋ አደረገዉ።የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መስተዳድር አፍኖት የነበረዉ ዘገባ አልጋዋራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ጋዜጠኛዉ እንዲያዝ ወይም እንዲገደል ማዘዛቸዉን ይጠቁማል።ገዳዮች ያደረጉትን ያደረጉትም በአልጋወራሹ ዕዉቅና መሆኑን ያጋልጣል።
የባይደን አስተዳደር በግድያዉ በቀጥታ ተካፍለዋል ባላቸዉ 76 ሰዎች ላይም የቪዛ ማዕቀብ ጥሏል።አልጋወራሹ ግን አልተነኩም።እንዲያዉም የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ይፋ የሆነዉ ዘገባ የግድያዉን ቅሌት ቢያጋልጥም አልጋወራሹን በቀጥታ ተጠያቂ የሚያደርገዉ የዘገባዉ ክፍል አሁንም ይፋ አልሆነም።
                                 
ያም ሆኖ የባይደን አስተዳደር የወሰደዉ ርምጃ እንደ 1967ቱ፣ እንደ 1973፣2001ዱ የሪያድ-ዋሽግተንን ጥብቅ ወዳጅነትን ማንገራገጩ አልቀረም።በተለይ ባይደን የሐብታም ሰፊ፣ ስልታዊ፣ የሙስሊም እምነት መፍለቂያቱን ሐገር ዘዉድ ለመጫን የሚቋምጡትን ወጣት አልጋወራሽን ገሸሽ ገለል አድርገዉ በመኖርና መሞት መሐል የሚንጠራወዙትን የ86 ዓመት አባታቸዉን ቀረብ-ጠጋ ማድረጋቸዉ ወጣቱን አልጋወራሽ ከመኮርኮም የሚቆጠር ነዉ።እንደገና ዩሱፍ ያሲን።
                                     
የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት አርብ የወጣዉን ዘገባና የጆ ባይደን አስተዳደርን ማዕቀብ ነቅፈዉታል።የአልጋ ወራሻቸዉን በአስገዳይነት መጠርጠር፣ መተቸትም «ከእዉነት የራቀ» ብለዉታል።እንዲያዉም ለነገስታቱ ያደሩ የሚመስሉት የፖለቲካ አዋቂ አብዱል አዚዝ አል ዮሱፍ እንደሚሉት የዋሽግተኖች እርምጃ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድናት አቋም ነፃብራቅ ነዉ።
                                    
«የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድናትን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ነዉ።ቡድናቱ ለሳዑዲ አረቢያ ወዳጅ አለመሆናቸዉን የሚያሳይ ነዉ።እንዲሕ አይነቱ ዘገባ በጣም ግራ አጋብቶናል።»
ግራ ካጋባ ግራ-አጋቢዉ የአጉርሰኝ ላጉርስሁ ወዳጅነት፣ ከሕዝብ ፍላጎት፣ ከየሐገራቱ መሰረት፣ ከመብት ነፃነትም በልጦ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አብነቲቱ የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች እና  የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ተምሳሌይቲ የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት ወዳጅነት ለ76 ዘመናት ፀንቶ መቆየቱ በሆነ ነበር።አልሆነም።
አሁንም የሆነዉ የሪያድ ምናልባት በሪያድ በኩልም የአቡዳቢ ወጣት ገዢዎች እንዳሻቸዉ እንዳይፈነጩ  ያዝ፣ ሞስኮ ወይም ቤጂንጎች ጉያ እንዳይወሸቁ ደግሞ ለቀቅ ማድረግ ነዉ።አገም ጠቀም።የሪያድና የአቡዳቢ ገዢዎች እነ ግብፅን ገዝተዉ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ኢራን፣ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮያና ኤርትራም ጭምር ላይ ለመጋለብ፣ አቶ የሱፍ እንደሚሉት፣ «ያለአቅማቸዉ እየተንጠራሩ ነዉ።»
ሳዑዲ አረቢያ ከዩናይትድ ስቴትስ ብዙ የጦር መሳሪያ በመግዛት የሚቀድማት የለም።በመቶ ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።ሳዑዲ አረቢያ ለአሜሪካ 3ኛዋ ነዳጅ ዘይት አቅራቢ ሐገር ናት።የጦር መሳሪያን ቀንሶ-ግን ነዳጅን ጨምሮ የሁለቱ ሐገራት የሸቀጥ የንግድ የንግድ ልዉዉጥ በዓመት 38 ቢሊዮን ዶላር ነዉ።37 ሺሕ የሳዑዲ አረቢያ ወጣቶች በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ይማራሉ።
ባይደን አስተዳደር ጅምር ርምጃ እንዳጀማመሩ ከቀጠለ ለመካከለኛዉ ምስራቅና ለአፍሪቃ ምስቅልቅል ትንሽ እና የሩቅ ተስፋ ሰጪ ነዉ።የአሜሪካኖችን ስምና ጥቅም ለመጠበቅ፣ ራሳቸዉ ገዢዎቹ አላቅማቸዉ ሲንጠራሩ-በየሐገሮቻቸዉ ላይ ያደረሱትን ኪሳራ ለመግታትም ጠቃሚ ነዉ።

Mohammed bin Salman
ምስል picture-alliance/dpa/SPA
USA Treffen Präsident Trump mit Prinz Mohammed bin Salman
ምስል picture-alliance/dpa/K. Dietsch
Saudi-Arabien | Kronprinz Mohammed bin Salman
ምስል Bandar Algaloud/Saudi Royal Court/REUTERS
Jamal Kashoggi
ምስል Getty Images/M. Al-Shaikh

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ