1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት

ሐሙስ፣ ግንቦት 15 2016

ሰሞኑን በኢትዮጵያ የዩኤስ አምባሳደር ስለ ኢትዮጵያ የፖሊሲ ንግግር እና መንግሥት የሰጠው ምላሽ "የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ችግር ያለበትና ጠንካራ አይደለም ማለት ተደርጎ" ሊወሰድ እንደማይገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ። ኢትዮጵያ በራስ ገዟ ሶማሊላንድ የሚገኘውን የቆንስላ ጽሕፈት ቤቷን ወደ ሙሉ ኤምባሲ ማሳደጓ ምን ያህል እውነት ነው ?

https://p.dw.com/p/4gCOX
አምባሳደር ነቢዩ ተድላ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ
አምባሳደር ነቢዩ ተድላ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ምስል Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት


ሰሞኑን በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ስለ ኢትዮጵያ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር እና መንግሥት የሰጠው ምላሽ "የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ችግር ያለበትና ጠንካራ አይደለም ማለት ተደርጎ" ሊወሰድ እንደማይገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ። የአምባሳደሩ መግለጫ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ እና ወዳጃዊ ግንኙነት የሚፃረር ነው ሲል ያጣጣለው የውጭ ገዳይ ሚኒስቴር "መመልከት የሚገባን ጉዳዮች ካሉ በመመካከር አብረን ልንሠራ የምንችል ይሆናል" በማለት ቃል ዐቀባዩ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ዛሬ ተናግረዋል። ይህንን በተመለከተ መገልጫ ያወጣው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ፤ የአሜሪካን ጥሪ በበጎ እንደሚያየው እና መንግሥት "ጥሪውን ተቀብሎ ወደ ሃቀኛ ድርድር እንዲገባ" ጠይቋል። ኢትዮጵያ በራስ ገዟ ሶማሊላንድ የሚገኘውን የቆንስላ ጽሕፈት ቤቷን ወደ ሙሉ ኤምባሲ ማሳደጓን የተመለከተ መረጃዎች መውጣታቸው ምን ያህል እውነት ነው ተብለው በዛሬው መግለጫቸው የተጠየቁት ቃል ዐቀባዩ በጉዳዩ ላይ መናገር እንደማይችሉ ተናግረዋል። 

ኤርቪን ማሲንጋ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ
ኤርቪን ማሲንጋ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ ምስል Seyoum Getu/DW


ቃል ዐቀባዩ ምን አሉ ?


በቅርቡ በርእሠ ብሔር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ከተሾሙት 24 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦች መካከል አንዱ የሆኑት ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ያደረጉት ንግግር፤  የሉዓላዊ መንግሥታትን፣ የወዳጅ ሀገራትን ፣ የእኩልነት መርህን እና የሀገራት ትክክለኛ የግንኙነት መስመርን በጠበቀ መልኩ ያልተደረገ ብሎም መደበኛ የሆኑ አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የአሠራር ሂደቶችን የጣሰ መሆኑን ጠቅሰዋል። "ሀገራችን ባጋጠማት ወቅታዊ እና ጊዜያዊ ብሎም ልንሻገራቸው የምንችላቸው ችግሮቻችን ልክ ሳይሆን፤ ግንኙነቱ እንዲመሠረት የምንፈልገው፤ ባለን አቅም፣ ባለን ታሪካዊ ግንኙነት ልክ ሊሆን ይገባል"።


የፓርቲዎች ኮከስ የአሜሪካን ጥሪ ደግፋል


በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴስት አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በመንግሥት እና በተዋጊዎች መካከል ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በአወዛጋቢው ንግግራቸው ጠይቀው ነበር። ዘጠኝ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያቀፈው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ "ሃቀኛ፣ አሳታፊና ተዓማኒ ሀገራዊ መግባባትና ዕርቅ ለነገ የማይባል የዛሬ ጥያቄ ነው" ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ የአምባሳደሩን ንግግር ደግፏል። ኮከሱ "የሚታየው የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ረገጣ ከሰላማዊ ህዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ማሳደድ፣ አፈናና እስራት ወደ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስራትና ግድያ በማደጉና የሰላማዊ ትግል በር መዘጋቱ" ን በመግለጫው ጠቅሷል። የፓርቲዎች ስብስብ መንግስት ከአሜሪካ የቀረበውን ጥያቄ እና ጥሪ ተቀብሎ "ወደ ሃቀኛ ድርድር እንዲገባ" መጠየቁንም  የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ኦቶ ግርማ በቀለ ለ ዶቼ ቬለ ተናግረዋል። "መንግሥት እንደነዚህ ያሉ ምክሮች ከወዳጅ ሀገራት ሲሰጡ ሁልጊዜ ተከላካይ ሳይሆን፤ በቀና ወስዶ ለሀገሪቱ በሚጠቅም፣ ሰላም እና መረጋጋትን በዘላቂነት ለመፍታት ግብአት አድርጎ እንዲወስድ" ይገባል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ምስል Seyoum Getu/DW

የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አምባሳደር ማይክ ሀመር ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ "የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ትጥቅ በማስፈታት፣ በማቋቋም እና የግጭት ማቆም ስምምነት በተሳካ ሁኔታ እንዲተገበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ" ውይይት ተደርጓል ያሉት ቃል አቀባዩ "የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ችግር ያለበትና ጠንካራ አይደለም ማለት ተደርጎ" ሊወሰድ እንደማይገባ ግን ገልፀዋል።

ሀርጌሳ ስለሚገኘው ቆንስላ ጽ/ቤት የተሰጠ አስተያየት


ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ 24 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦችን እንደ ቃል አቀባዩ አባባል "ችሎታን፣ ብቃትንና የዲፕሎማሲ ልምድን መሰረት" አድርገው ሾመዋል። 
ሶማሊላንድ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ወደ ኤምባሲ ማደጉን የሚገልፁ መረጃዎች ተጠቅሰው ጉዳዩ ምን ያህል እውነት ነው የተባሉት ቃል አቀባዩ በጉዳዩ ላይ መናገር እንደማይችሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል በሚለው ጉዳይም ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡበትም። የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር በቅርቡ ለዶቼቬለ ግን የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት "በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ" ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚኖሩ ተጋላጭ ኢትዮጵያውያንን ልሰተኞች ለማስመለስ በጀመረው ጥረት እስካሁን 27,057 ዜጎች መመለሳቸውን ገልጿል።

 

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ