1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወለጋው ጭፍጨፋ፤ የቴዲ አፍሮ ናዕትና «አረንጓዴ ዐሻራ»

ዓርብ፣ ሰኔ 17 2014

አርቲስት ቴዲ አፍሮ በወለጋው ጭፍጨፋ ሣልስት ማክሰኞ ዕለት «ናዕት» የተሰኘ ነጠላ ዜማ ለአድማጮች አድርሷል። በዚያኑ ዕለት የጠቅላይ ሚንስትሩ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ስለ ልማት እና «አረንጓዴ ዐሻራ»ን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸውን በተመለከተም ከኅብረተሰቡ የተሰነዘሩ አስተያየቶችን ቃኝተናል። የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት አተያየቶች።

https://p.dw.com/p/4D9hX
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

ዘግናኝ ጭፍጨፋው ከዳር እስከ ዳር ቁጣ ቀስቅሷል

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ነዋሪዎች የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው የአማራ ብሔር ተወላጆች በታጠቁ ኃይሎች መጨፍጨፋቸው ከዳር እስከ ዳር ቁጣ ቀስቅሷል። ዘግናኝ ጭፍጨፋውን በተመለከተ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። አርቲስት ቴዲ አፍሮ ወይንም ቴዎድሮስ ካሣሁን የወለጋው ጭፍጨፋ በተፈጸመ በሣልስቱ ማክሰኞ «ናዕት» ወይንም እያመመው ቁጥር ፪ የተሰኘ ነጠላ ዜማ ለአድማጮች አድርሷል። በእንጉርጉሮ የተቃኘ ዜማው በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጸሙ ግድያዎች እና በደሎች በኅብረተሰቡ ዘንድ የፈጠሩትን ኅመም እና ሰቆቃ ያስተጋባበት ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየትት ሰጥተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት እንደዘበት በተቀጠፈበት ሰሞን የጠቅላይ ሚንስትሩ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ስለ ልማት እና «አረንጓዴ ዐሻራ»ን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸውን በተመለከተም ከኅብረተሰቡ የተሰነዘሩ አስተያየቶችን ቃኝተናል።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Ozan Kose/AFP/Getty Images

የወለጋው ዘግናኝ ጭፍጨፋ

የአንድም ሰው ብቻ ቢሆን ክቡር የሰው ልጅ ሕይወት ሲቀጠፍ እጅግ ያንገበግባል። የሁለት መቶ፤ ሦስት መቶ፤ አምስት መቶ፤ ሰባት መቶ እንዲያ እንዲያ እያለ ኢትዮጵያ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በግፍ ማለቃቸው ለዓመታት እየተለመደ መጥቷል። ላለፉት አራት ዓመታትም፦ ጊዜ እና ወቅት እየጠበቁ በሚፈጸሙ የተደራጁ ጥቃቶች ዜጎች በግፍ ሲጨፈጨፉ እና ለእልቂት ሲዳረጉ የሚፈጠረው ቁጣ የአንድ ሰሞንኛ ብቻ ኾኖ እየተረሳ መደጋገሙም ቀጥሏል።

«...ሰዎች ይገደላሉ። በሟቾች ቁጥር፣ ብሔር፣ ሃይማኖት ላይ እንጨቃጨቃለን። ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ይጮሃሉ፤ መንግስት አነስተኛ መግለጫ ያወጣል፤ የፀጥታ ኃይሎች አጥቂዎቹን ደመሰስን ይላሉ ...እንረሳዋለን...ትንሽ ቆይቶ ይደገማል።» የቤተማርያም የትዊተር አስተያየት ነው።  

በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በአብዛኛው የአማራ ብሔር ተወላጅ የኾኑ ነዋሪዎች የተጨፈጨፉት መንግሥት «ኦነግ ሸኔ» ሲል በሚጠራቸው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ታጣቂዎች እንደሆነ ይናገራል።ታጣቂዎቹ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ያደረጃቸዉ ሚሊሺያዎች ባሏቸው ነፍሰ ገዳዮች ጭፍጨፋው እንደተፈጸመ ይገልጣሉ። ከጭፍጨፋው የተረፉ ነዋሪዎች እጅግ በስጋት ውስጥ ተውጠው ሬሳ ለቀማ እና ቀብር ላይ አሁንም ይባዝናሉ። ፖለቲከኞች በየፊናቸው አስተያየታቸውን መስጠት  ቀጥለዋል።

«250 በላይ ንጹሃን የአማርኛ ተናጋሪዎች በሸኔ በግፍ ተጨፍጭፈዋል። እሳክሁን በሺዎች አልቀዋል። የኦሮሚያ ክልል ይህን ማስቆምና ከላከል ካልቻለ ህዝቡ ሌላ አካባቢ እንዲሄድ ማድረግ ወይንም ማስታጠቅ ይገባል» የነዓምን ዘለቀ የትዊተር አስተያየት ነው። በግፍ የተጨፈጨፉት በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች መሆናቸው በስፋት እየተነገረ «የአማርኛ ተናጋሪዎች» በሚል የተሰጠው አስተያየት በአስተያየት ሰጪው ላይ ከእየ አቅጣጫው ብርቱ ትችት አጭሯል።

አንቶኒዮ ሙላት በትዊተር ገጻቸው ላይ፦ «አማርኛ መናገራቸው አይደለም እያስገደላቸው ያለው፤ ኦሮምኛም ተናጋሪ ናቸው ተወልደው ያደጉበት አካባቢ ስለሆነ። የሞት ፍርዳቸው ብሔራቸው አማራ በመሆኑ ብቻ ነው» ሲሉ አስተያየት ሰንዝረዋል።

Infografik Karte Äthiopien AM

ሐና በትዊተር ጽሑፋቸው «ያለቁትን ወገኖቹን በሥም እንኳን ለመጥራት የሚሽኮረመምመሪ» ሲሉ ጽፈዋል። «መሪ» የሚለውን ቃል በትምእርተ-ጥቅስ ለብቻው ሸብበውታል።  «ያጠፋነው ምን ያህል ሆኖ ነው ግን እነዚህ ላይ የጣለን???» ሲሉም አስተያየታቸውን ቋጭተዋል። 

«በጣም ያሳዝናል እንደዚህ አይነት ጭካኔ የት ሀገር አለ ሲሉ የጠየቁት ደግሞ ናትናኤል ታምሩ ናቸው፤ በፌስቡክ ጽሑፋቸው። «የሠው ነገር ብቻ» በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ በአጭሩ፦ «መግሥት አለ ወይ ያሥብላል» ብለዋል። «መንግስት ስላልቻለ ስላም አስከባሪ ይግባልን ወይም መንግስት ሀገርቱን በወታደራዊ መንግስት ይምራልን» ይኼ ደግሞ የአክሊሉ ኃይሉ የፌስቡክ መልእክት ነው።

ሞሐመድ ሐሰን ትዊተር ላይ ያሰፈሩት ጽሑፍ፦ «አሌክዛንደር ቡላቶቪች፣ ኤንሪኮ ቼሩሊ ወይም የተስፋዬ /አብን ልቦለድ ጠቅሰን ሳይሆን የወለጋ መሬትን አናግረን በታሪክ እንጠይቃችኋለን» በሚል ይነበባል። አሌክዛንደር ቡላቶቪች በዘመነ ምንሊክ የሩስያ መልእክተኛ ኾኖ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ስለ አቢሲኒያ ስልጣኔ የጻፈ ነው። «ከእንጦጦ እስከ ባሮ ወንዝ» እና «ከዳግማዊ ምንሊክ ሠራዊት ጋር» በተባሉት መጽሐፍቱ ግንዛቤውን ከወቅቱ ዓለም አቀፍ ፖለለቲካዊ ምልከታው ጋር አሰናስሎ ጽፏል። ኤንሪኮ ቼሩሊ በተለይ፦ በኢትዮ ሴሜቲክ ቋንቋዎች እና በሶማሊያ ባሕላዊ ሕግ ላይ በጻፋቸው ይታወቃል። ተስፋዬ ገብረአብ ደግሞ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥላቻ እንዲስፋፋ ይሰብካል በሚል በተተቸው «የቡርቃ ዝምታ» በተሰኘው መጽሐፉ ይታወሳል። 

«የሞተ ተጎዳ» ይለናል ሕያብ በትዊተር ጽሑፉ። «መሬት ላይ ያልወረደ ትግል ነገ በሌላ አጀንዳ ይረሳል። የሞተ ተጎዳ ራሳችሁን ለአደጋ አጋልጣችሁ ለወገናችሁ የቆማችሁ እና የሕዝብ እምቢተኝነትን ለማስተባበር የምትደክሙ ስዎችን ልቤ ታከብራችሗለች። የሌሎቻችን ዋይታ አፍታ እና የቁራ ጩኸት ነው።»

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

የወለጋው ጭፍጨፋ በተከሰተ በሣልስቱ ለአድማጮች «ናዕት»  በሚል ርእስ የቀረበው የቴዲ አፍሮ ወቅታዊ የሬጌ ዜማ ነው። ይህ ነጠላ ዜማው እስከ ትናንት ከሰአት ድረስ ብቻ 48 ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ዐይተውታል። 15 ሺህ ግድም አስተያየቶችንም አስተናግዷል።

«ምንም እንኳን የፌዴራል መንግሥት የሐዘን መግለጫ ባይሰጥም ቴዲ አፍሮ በሙዚቃ የሐዘን መግለጫ አውጥቷል። እናመሰግናለን።» አዲስ ሞኒተር የተባሉ የዩቲዩብ ተጠቃሚ ያሰፈሩት መልእክት ነው። «ድሮም ቢሆን መግለጫ የምንጠብቀው ከእውነተኛው ንጉሣችን ነው እናመሰግናለን ቴዲያችን የምር የልባችን ነህ።» ይህ የዩቲዩብ መልእክት ደግሞ በሠርኬ ብርሃኑ የተሰጠ ነው። ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች መልእክታቸውን በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት የልብ ምስሎች እንዲሁም በዘውድ አሽቆጥቁጠውታል። «ለታሪክ የሚቀመጥ ሙዚቃ ነው ፈጣሪ ለሀገራችን ሰላምን ፍቅርን ያውርድልን ዘረኞችን ልቦና ይስጣቸው።» ይኼም መልእክት ከቴዲ አፍሮ «ናዕት» ዜማ ስር የተሰጠ ነው።

ቴዲ «እያመመው መጣ» እያለ እንጉርጉሮውን በማሲንቆ ሲቃ አጅቦ ይቀጥላል።  ፋሲል የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «እኛ ግን ከመዋደድ ይልቅ መለያየትን፣ ከመፋቀር ይልቅ መጠላላትን፣ ካንድነት ይልቅ መበታተንንን መርጠን ጥላቻና ዘረኝነትን መካከላችን አስገብተን እንዲህ አይነት ደረጃ ላይ ደርሰናል» ሲሉ ቁጭታቸውን አስፍረዋል።

አቤል ዋበላ በትዊተር የእንግሊዝኛ ጽሑፋቸው፦ «ቴዲ አፍሮ የእኛን ትውልድ ቁጣ እና የልብ መከፋት አጠቃሎታል» ሲሉ ጽፈዋል። «የሚያዜም ይመስላል ሲያጣጥር ተጨንቆ፤ ውስጡን ሲሰብቅለት እያለ ማሲንቆ»

አረንጓዴ ዐሻራ

የቴዲ አፍሮ «ናዕት» እንጉርጉሮ በወለጋ ጭፍጨፋ ሣልስት ከጥግ እስከ ጥግ ባስተጋባበት ዕለት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በትዊተር ገጻቸው አጭር መልእክት ይዘው ብቅ ብለዋል። «4ኛውን ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርን አስጀምረናል» ሲል ይነበባል የጠቅላይ ሚንሥትሩ ወቅታዊ መልእክት። ከአጭሩ መልእክት ጋር ጠቅላይ ሚንሥትሩ ሳር መሀል መሬት እየኮተኮቱ ችግኝ ሲተክሉ የሚታይባቸው ዐራት ፎቶግራፎች ተያያይዘዋል።

Äthiopien - Weltrekord im Bäume pflanzen -Symbolbild
ምስል picture-alliance/G. Fischer

አብራር የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ እዛው የጠቅላይ ሚንስትሩ መልእክት ስር ቀጣዩን ጽፈዋል። «በጎ ሥራዎችዎን ሁሌም እናከብራለን እናደንቃለን አረንጓዴ ዐሻራው ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን፥ የዜጎች ነፍስ ከልማት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል» ብለዋል። «ሩዋንዳ በብሄር ሰውን መፈረጅ ሕገወጥ ነው ያሉንን በተግባር ለማዋል ለምን ተሳነዎት?» ሲሉም ጠይቀዋል። «ሀገርን መንከባከብ የዜጎቿን ሕይወት በመጠበቅ ይጀምራል» ሲል የሚነበበው መልእክት ደግሞ የጂ ፋሲል ነው። «አረንጓዴ አሻራ»ን በተመለከተ በእንግሊዝኛ ያሰፈሩትን ስድብ ዘለነዋል።

ከጠቅላይ ሚንሥትሩ ባሻገር የማዕድን ሚንስትር ታከለ ዑማ በትዊተር ይፋዊ ገጻቸው «መትከላችንን እንቀጥላለን» ሲሉ ማክሰኞ ዕለት በእንግሊዝኛ በአጭሩ ጽፈዋል። ችግኝ ሲተክሉ የሚታይበት ፎቶግራፍም አያይዘዋል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ሽመልስ አብዲሳም  «የወደፊቱ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኤኮኖሚ» በሚል በእንግሊዝኛ ቋንቋ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩትው ጽሑፍ «4,8 ቢሊዮን ችግኞች እና 1,3 ቢሊዮን የቡና ችግኞች ተክለናል» በሚል ይነበባል። እጅግ ሰፋፊ አረንጓዴ የለበሱ ማሳዎች የሚታዩበት ፎቶግራፍም ተያይዟል። ይህ መልእክት እና ፎቶግራፍ ማክሰኞ ዕለት ትዊተራቸው ላይ ቀርቦ ነበር። አሁን ገጻቸው ላይ ዐይታይም። የሰሞኑን እና ከዚህ ቀደም ተከታትሎ የቀጠለውን ግድያ በመቃወም በቃ እና ቀይ አሻራ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ዘመቻዎችም ተጀምረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ