1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

3 ሰዎች ተገደሉ

ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2012

በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በከተማዋ በተቀሰቀሰው ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የጊዳሚ ወረዳ አስተዳደር አስታዉቋል፡  ግጭቱ የተቀሰቀሰው ባልታቁ ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት ላይ ቦምብ በመወርወሩና ተኩስ በመከፈቱ መሆኑንም የጊዳሚ ወረዳ አስተዳደዳሪ አቶ ደሳለኝ ቱጁባ በስልክ  ተናግረዋል፡

https://p.dw.com/p/3PjcR
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

ወለጋ ዉስጥ በሁለት ወረዳዎች ሰዉ ተገደለ

በቄለምና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ሰሞኑን በተቀሰቀሰ ግጭት የአንዲት ከተማ ከንቲባን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ተገደሉ።የየአካባቢዉ ባለስልጣናትና ነዋሪዎች በየፊናቸዉ እንዳሉት በቄለም ወለጋ፣ ጉዳሚ ወረዳ ባለፈዉ ቅዳሜ ማታ በተነሳ ግጭት ሁለት የከተማይቱ ነዋሪዎች ተገድለዋል።የሁለቱን ሰዎች ሕይወት ያጠፋዉ ግጭት የተቀሰቀሰዉ ማንነታቸዉ በዉል ያልታወቁ ሰዎች ባካባቢዉ በሠፈረዉ የመከላከያ ጦር ላይ  ቦምብ ከተጣሉ በኋላ ነዉ።በማግስቱ ዕሁድ ደግሞ በምዕራብ ወለጋ የጉልሶ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ተካልኝ ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገድለዋል።የአሶሳዉ ወኪላችን ነጋሳ ደሳለኝ ጉዳዩን ተከታትሎታል። 
በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በከተማዋ በተቀሰቀሰው ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የጊዳሚ ወረዳ አስተዳደር አስታዉቋል፡  ግጭቱ የተቀሰቀሰው ባልታቁ ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት ላይ ቦምብ በመወርወሩና ተኩስ በመከፈቱ መሆኑንም የጊዳሚ ወረዳ አስተዳደዳሪ አቶ ደሳለኝ ቱጁባ በስልክ  ተናግረዋል፡፡ የተገደሉት ሰዎች የተማዋ ነዋሪዎች ሲሆኑ ከመካከልቸውም አንዱ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ናቸው ተብሏል፡፡ 
በከተማዋ የነበረው ጥቃት የተፈጸመው በመንግስት ጸጥታ ሀይሎች መሆኑን የአካባቢ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ እንደሚሉት ደግሞ በወቅቱ በመከላከያ ሰራዊትና በታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ስለነበር ሰዎቹ በማን እንደተገደሉ ለማወቅ አልተቻለም። እስካሁን በግዲያውም ሆነ ቦምብ ወርውረዋል የሚጠረጠሩ ሰዎች አልተያዙም።
ከትናት በስቲያ በምዕራብ ወለጋ የጉልሶ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አበበ ተካልኝ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳደርና ጸጥታ ዘርፍ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ከንቲባው ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ብዙ ቁጥር ባላቸው ሲቪል በለበሱ ሰዎች መገደላቸውን የጉልሶ ወረዳ አስተዳደር ጸጥታ  ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋ ልኪሳ በስልክ አብራርተዋል፡፡ከንቲባው  የሚኖሩት ከከተማው ራቅ ባለ አካባቢ  ስለበር ጥቃት አድራሾችን በቀላሉ ለመለየት እና ወደ ህግ ለማቅረብ በወቅቱ አልተቻለም ብለዋል፡፡ 
በሁለቱም አካባቢዎች በተፈጠረው ጥቃት እና ግዲያ የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ እያጣራን ነው ከማለት ውጪ አስካሁን የተያዘም ሆነ ለህግ የቀረበ ተጠርጣሪ አለመኖሩን ገልጸውልኛል፡፡ ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ይፋ ባደረገው መግለጫ በ2012 ዓ፣ም በክልሉ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሀይልን ትጥቅ እንደሚያስፈታ አስታዉቆ ነበር።

ነጋሳ ደሳለኝ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት በቀለ