1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮቪድ 19 የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴና ውጤቱ

ማክሰኞ፣ መስከረም 5 2013

የዓለም የጤና ድርጅት ምንም እንኳን ብዙ ሰዎች የኮቪድ 19 ምልክቶችን ባያሳዩም ሃገራት የመመርመር አቅማቸውን አጠናክረው በስፋት ምርመራዎች እንዲያደርጉ መክሯል። በአንዳንድ ሃገራት በየዕለቱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም ምርመራው ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ እስከትናት ድረስ 1,147,268 ምርመራዎች መደረጋቸውን የጤና ጥበቃ መረጃ ያመለክታል።

https://p.dw.com/p/3iVqW
Coronavirus I Köln
ምስል picture-alliance/dpa/M. Becker

«የኮሮና መመርመሪያ ቁሳቁስ ማምረት መጀመሩ»

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ መረጃዎች በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱን ያመለክታሉ። በዚህ መሀልም ለተሐዋሲው መከላከያ የሚሆን መድኃኒት የማቅረቡ ፉክክር ተጠናክሯል። ነሐሴ ወር ላይ ኖቫ ቫክስ የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ መድኃኒት አምራች ኩባንያ በዓለም ትልቁ የክትባት አምራች መሆኑ ከሚነገርለት የሕንዱ ሴረም ተቋም ጋር በትንሹ አንድ ቢሊየን ክትባት ለማምረት ተፈራርሟል። የክትባቱ ማምረት ሂደት አሁን በመካከለኛ የምርት ደረጃ ላይ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን ሁለቱ ተቋማት የሚያዘጋጁት ክትባትም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሃገራት የሚውል ነው ተብሏል። ቻይና  የጀመረችው የክትባት ማምረት ሂደት እስከመጪው ኅዳር ሊደርስ ይችላል ባይ ናት። ጀርመን በበኩሏ ክትባት ለገበያ የማቅረብ ፉክክሩን አልወደድኩትም በእርጋታ እስከ መጪው ጎርጎሪዮሳዊ 2012 ዓ,ም አጋማሽ ላደርስ እችላለሁ እያለች ነው።

USA Coronavirus Impfstoff-Test
ምስል H. Pennink/AP Photo/picture-alliance

የዓለም የጤና ድርጅት ሃገራት የኮቪድ 19 ምርመራን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እያሳሰበ ነው። ከመነሻው ችግሩ ተባብሶ በታየባቸው እንደቻይና ባሉ ሃገራት ሰዎች በፈቃደኝነት ምርመራውን ማካሄድ ጀምረዋል። ሆንኮንግ ለ1,8 ሚሊየን ሕዝብ ምርመራ አድርጌ በሽታው የተገኘባቸው 42 ብቻ ናቸው ብላለች። የቻይና የተጀመረው ሰዎች በመደዳ የመመርመሩ ሂደት የበሽታው ምልክት ሳይታይባቸው ተሐዋሲው ያለባቸውን ለይቶ ለማወቅ የተደረገ ጥረት መሆኑ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ትናንት በተካሄደው ምርመራ ባጠቃላይ 64,786 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ መያዛቸው ሲረጋገጥ፤ ከእነዚህ ውስጥ 25333ቱ ከህመማቸው አገግመዋል። በተሐዋሲው ተይዘው የሚገኙት ደግሞ 38429 ሰዎች ናቸው። ባለፈው መጋቢት ወር አንድ ሰው ላይ ታይቶ ቀስ በቀስ የተዛመተው የኮሮና ተሐዋሲ የሚተላለፍባቸውን መንገዶችና የመከላከያ ስልቶችን ኅብረተሰቡ መረዳቱን ሆኖም ግን ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ጉድለት መኖሩን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዮርዳኖስ አለባቸው ይናገራሉ።

Niederlande Utrecht Coronatest
ምስል picture-alliance/dpa/R. Utrecht

በዓለም የጤና ድርጅት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽ ሰጪ ቡድን አባል ማርግሬት ሃሪስ ባደረጉት ቃለምልልስ ዛሬም የተሐዋሲው ስርጭት በሰሜን እና በደቡብ አሜሪካ ሃገራት ተባብሶ መቀጠሉን አመልክተዋል። በተጨማሪም በሜዲትራኒያን ባሕር በስተምሥራቅ ባሉ ሃገራትና በሰሜን አፍሪቃ፣ እንዲሁም በአረብ ሃገራትም መዛመቱ መባባሱን ጠቁመዋል። በመፍትሄነት ያቀረቡት ደግሞ ሃገራት እንደእስራኤል ለሁለተኛ ጊዜ የዜጎችን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት እንዳይዳረጉ በተዘጋ ስፍራ መሰባሰብን፣ በተለያየ ዝግጅት ሰበብ በአንድ ቦታ የሰዎችን በርክቶ መገኘትን እንዲሁም ርቀት አለመጠበቅ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። የወረርሽኙን የመዛመት ስልት ከማራቶን ያመሳሰሉት ባለሙያዋ ሰዎች እጅ በመታጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን መጠቀምን ሳይዘናጉ መፈፀሙ ይረዳልና ሰዎች ይህን በአግባቡ መፈፀም ከቻሉ የስርጭቱን አድማስ ማጥበብ እንደሚቻል መክረዋል። 

ሸዋዬ  ለገሠ

አዜብ ታደሰ