1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ጦርነት የኢትዮጵያን አስጎብኚ ድርጅቶች እንዴት አከረሟቸው?

ረቡዕ፣ ጥር 11 2014

የገና በዓል የሚከበርከበት የታኅሳስ ወር መጨረሻ እና በጥምቀት የሚደምቀው የጥር ወር የኢትዮጵያ ቱሪዝም ገበያ የሚደራበት፤ አስጎብኚዎችም ሥራቸው የሚሞቅበት ወቅት ነበር። የኮቪድ ወረርሽኝ እና ጦርነት ግን የአገሪቱን ቱሪዝምና በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ለፈተና ዳርገዋል። ለሰራተኞች ደሞዝ፤ ለቢሮ ኪራይ መክፈል የተቸገሩ አስጎብኚዎች ጭምር አሉ።

https://p.dw.com/p/45n6T
Äthiopien - Heißester Ort der Erde
ምስል DW/J. Martinez

የቤጋ ቱር ኦፐሬሽን ባለቤት እና ኃላፊ የተሠማሩበት የስራ ዘርፍ ሲቀዛቀዝ ሰራተኞቻቸውን አሰናብተው ቢሯቸውን የመዝጋት ሐሳብ ሽው ብሎባቸው ነበር። አቶ በቀለ ጋረድ ይኸን ሐሳብ ለመጋፈጥ የተገደዱት የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ተጽዕኖ የኢትዮጵያን ቱሪዝም በተጫነበት፤ እንደ እርሳቸው በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩም በተፈተኑበት ወቅት ነው።

"እኔ እንዲያውም በግሌ መዝጋት አለብኝ ብዬ ለገቢዎች ሚኒስቴር አመልክቼ ነበር" የሚሉት አቶ በቀለ "መኪኖቹ ትንሽ ትንሽ ስለሚከራዩ ትንሽ መታገስ አለብኝ" በሚል በውሳኔው ሳይገፉበት ቀሩ። ወረርሽኝ እና ጦርነት የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ ቢያሳድርም "ስለእኛ ማግኘት ብዙውን አናስበውም። ያገር ሰላም መሆን ነው ትልቁ ነገር" ሲሉ አንገብጋቢውን ጉዳይ ይጠቅሳሉ። "ሀገራችን ሰላም ሲሆን፤ ይኸ ወረርሽኝ ሲወገድልን ተስፋ አለን፤ አንዘጋውም በሚል ብዙዎቻችን በዚህ ዘርፍ የተሠማራን ሰዎች እየተነጋገርን፤ እርስ በርሳችን እየተደጓጎምን ይኸው እዚህ ደርሰናል" ሲሉ አቶ በቀለ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

ከሰሜን ተራሮች እስከ ኦሞ ሸለቆ፤ ከላሊበላ እስከ ባሌ ተራሮች በኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ መዳረሻዎችን ለአገር ውስጥ እና ባሕር ተሻግረው፤ ድንበር አቋርጠው ብቅ ለሚሉ የውጭ ዜጎች የሚያስጎበኘው ቤጋ ቱር ኦፐሬሽን ባለቤት ተስፋ በሁለት ጉዳዮች ላይ የተንጠለጠለ ነው። አንድም ሐብታም ደሐ ሳይል ዓለምን ያመሰው የኮቪድ ወረርሽኝ ሲቆም፤ አንድም ሲያፏጩ አመት ያለፋቸው የኢትዮጵያ ጦር መሣሪያዎች ዝም ሲሉ። የቤጋ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ በቀለ የተጋፈጡት ፈተና ግን የብቻቸው አይደለም። የአፍሪካን አድቬንቸር ቱርስ የተባለ የራሳቸውን ተቋም ከመመሥረታቸው በፊት በተለያዩ አገር አስጎብኚ ድርቶች ውስጥ የሠሩት አቶ አበበ ሐረገወይን ዘርፉን በቅርብ ከሚያውቁ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው።

Äthiopien - Heißester Ort der Erde
በአፋር ክልል የሚገኘው የኤርታሌ እሳተ ገሞራ ከመላው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚያቀኑ የአገር ጎብኚዎችን ቀልብ ከሚስቡ ተፈጥሯዊ ትዕይንቶች አንዱ ነው። ምስል DW/J. Martinez

አቶ አበበ ሐረገወይን "እንደ ሀገር ኮቪድ በመጣበት ጊዜ ትልቅ ተጽዕኖ አድርሶብናል። እስከ ማቆም ደረጃ የሚባል ድረስ ደርሶብናል። ከዚያም በኋላ ጦርነቱ ተጽዕኖ አሳድሮብናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነገር ከባድ ነበረ" ሲሉ ተናግረዋል።

"በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንቀርም የሚሉ አንዳንድ ቱሪስቶች ይመጡ ነበር፤ ወደ ደቡብም ይሔዱ ነበር። ግን በመሥሪያ ቤታችን ላይ ተግዳሮት ነበረው" የሚሉት አቶ አበበ ስለ ተጽዕኖው ሲጠየቁ  "እኔ አማርሬ አልነግርህም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። "አፍሪካን አድቬንቸርስ ቱር የሚኖረው፤ የኢትዮጵያ ቱሪዝም የሚኖረው ኢትዮጵያ ስትኖር ነው። ኢትዮጵያን ለማቆየት የሞቱ ሰዎች፤ የተጋደሉ ሰዎች፤ የቆሰሉ ሰዎች አሉ። አሁን እኔ ቢዝነስ ቀዘቀዘብኝ ብዬ ከእነሱ በላይ አላማርርም" ብለዋል።

እንደ አቶ አበበ ጋረድ እና አቶ በቀለ ሐረገወይን ያሉ የአገር አስጎብኚ ተቋማት ባለቤቶች እና አመራሮች ከሥራቸው መቀዛቀዝ በላይ ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያስከተለው ቀውስ እጅግ አሳስቧቸዋል። የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ያዳረሰው እና በአንጻራዊነት ጋብ የማለት አዝማሚያ ያሳየው ጦርነት ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ዓለምን ያሳሰበ ነው። ይኸ ጦርነት ላለፉት በርካታ አመታት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ካስተዋወቀቻቸው የቱሪስ መዳረሻዎች ቀዳሚዎቹ በሚገኙበት የጉዞ መስመር መካሔዱ ደግሞ በተለይ ለዘርፉ ከባድ ራስ ምታት ሆኗል።

BG Tigray | Negash
በትግራይ ክልል የሚገኙ የየሓ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ፣ የደብረ ዳሞ ገዳም እና የአል-ነጃሺ መስጂድን የመሳሰሉ የቱሪስት መዳረሻዎችም ከአይን የራቁ ሆነዋል። የአል-ነጃሺ መስጂድ በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበታል። ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

የአክሱም ስልጣኔ ቅሪቶች፣ የአክሱም ሐውልቶች እና የጽዮን ቤተ-ክርስቲያን የሚገኙባት የአክሱም ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ በኤርትራ ወታደሮች በህዳር 2012 ከተገደሉ በኋላ ከሐዘኗ ተጽናንታ በሯን ለአገር ጎብኚዎች ገና አልከፈተችም። ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ግንኙነቱ በተቆራረጠው የትግራይ ክልል የሚገኙ የየሓ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ፣ የደብረ ዳሞ ገዳም እና የአል-ነጃሺ መስጂድን የመሳሰሉ የቱሪስት መዳረሻዎችም ከአይን የራቁ ሆነዋል። አስራ አንድ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትን በውስጧ የያዘችው የላሊበላ ከተማ የውጊያ ወላፈን እየደጋገመ ከጠበሳቸው መካከል አንዷ ናት። የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና የጎንደር አብያተ መንግሥታት የሚገኙበት የአማራ ክልል ጦርነት ካስከተለው ውድመት በቅጡ ባያገግምም በጥምቀት ሞቅ ሞቅ ሲል ታይቷል።

የሰርቲን ሰንስ አገር አስጎብኚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ኤርሚያስ ሰገን "ከዚህ በፊትም አንዳንዴ በፖለቲካ ምክንያትም እና ጊዜያዊ በሆኑ ምክንያቶች ቱሪዝም ላይ ትንሽም ነገር ሲፈጠር የሚያደናቅፉት ነገሮች ይበዙ ነበር። እነዚያን የተወሰኑ ተጽዕኖዎች ማለፍ እንችላለን። የአሁኑ ግን ተጽዕኖ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆም ነው። ተጽዕኖ የሚባልም አይነት ነገር አይደለም" ሲሉ ዘርፉ የገጠመው ፈተና ከዚህ ቀደም ከታየው የበረታ እንደሆነ ይገልጻሉ።

"የኮቪድ ወረርሽኝ አብዛኛውን ድርጅት ከሥራ እንዲወጣ አድርጎታል። ደሞዝ መክፈል እና የቢሮ ኪራይ እንኳ ከፍሎ ለመቆየት የሚያስቸግር ደረጃ አድርሶታል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ተስፋ ነበረው። በወቅቱም መንግሥት የተወሰነ ከባንኮች ጋር በማያያዝ በብሔራዊ ባንክ በኩል በ5 በመቶ ወለድ ድርጅቶች እንዳይዘጉ ለማገዝ ሞክሯል። እሱ ግን ለአንድ አመት ነው የቆየው። ለኮቪድ ወቅት ብቻ የተደረገች ነች። ከዚያ በኋላ ደግሞ ጦርነቱ ሲጀምር እንደገና ያንሰራራል ወይም ይሻሻላል ተብሎ የተጠበቀውን ሥራ ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ አቁሞታል" የሚሉት አቶ ኤርሚያስ ወደ ደቡባዊ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች ሥራቸውን ቢያከናውኑም "አጥጋቢ የሚባሉ አይደሉም" በማለት ይገልጿቸዋል።  

Äthiopien Lalibela | Orthodoxe unterirdische monolithische Kirche Bete Giyorgis
አስራ አንድ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትን በውስጧ የያዘችው የላሊበላ ከተማ የውጊያ ወላፈን እየደጋገመ ከጠበሳቸው መካከል አንዷ ናት። ምስል picture alliance / Sergi Reboredo

በኮቪድ ምክንያት በዓለም አገራት ገቢራዊ የተደረጉ የጉዞ ዕቀባዎች ለሶስቱ ኩባንያዎችም ሆነ ለኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ከባድ ፈተና አስከትለዋል። በኢትዮጵያ ውጊያ ሲቀሰቀስ አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት ዜጎቻቸው ወደ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር እንዳያቀኑ የሰጧቸው ተደጋጋሚ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች ነበሩ። አቶ በቀለ የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ሁለቱ ተደራራቢ ተግዳሮቶች ካሳደሩት ጫና ገና እንዳላገገመ ይናገራሉ። "ታለፈ የሚባለው በዘርፉ ጥሩ ሥራ፤ ጥሩ እንቅስቃሴ መኖሩ ሲረጋገጥ ይመስለኛል" የሚሉት አቶ በቀለ "የኮቪድ [ወረርሽኝ ከተነሳ] ጀምሮ እኔ እንዳየሁት ምንም እንቅስቃሴ የለም። የሚመጣ እንግዳ የለም፤ የምንሰራው የለም" በማለት ዘርፉ የሚገኝበትን ደረጃ አስረድተዋል።

"ሰራተኛ ቀጥረህ ስታስተዳድር ለእነሱ [ደሞዝ] መክፈል መቻል አለብህ። የራስህን ቤተሰብ ማስተዳደር አለብህ። እንቅስቃሴ ከቆመ ደግሞ ሠራተኛም ማስተዳደር ይቸግርኻል"  ያሉት አቶ በቀለ ጋረድ በአስጎብኚዎች ማኅበር በኩል የቀረበላቸው ብድር በዘርፉ ለተሰማሩ አንጻራዊ ፋታ እንደሰጣቸው ጠቅሰዋል። "ማኅበሩ በጠየቀው መሠረት ከብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች መመሪያ ደርሷቸው የየአቅማችንን ያኸል ብድር እንዲፈቀድልን ተደርጎ ሠራተኛ ሳንበትን እስካሁን ይዘናል። ያንን ብድር የምንመልስበት አቅም ስላልነበረ በየአመቱ እየተራዘመ [ቆይቷል]፤ አሁንም እንዲራዘም ተጠይቋል። ለአንድ አመት ነበር የተፈቀደው አሁንም እንዲራዘም ተደርጓል። በመንግሥት በኩል ይኸ ስላለ ሠራተኛ ለመበተን አልደረስንም" በማለት አስረድተዋል።

"አገራችን ሰላም ከሆነ…"

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ዲያስፖራ እንቅስቃሴ የአፍሪካን አድቬንቸር ቱር ባለቤት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ሐረገወይንን ልብ አሙቋል። ኢትዮጵያ በምታደርጋቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በከፍተኛ ባለሥልጣናት እና በአምባሳደሮች ጭምር የማስተዋወቅ ሥራ ሊከናወን እንደሚገባ አቶ አበበ ይመክራሉ። "መንግሥት አዲስ አበባ ላይ ጥሩ ጥሩ መዳረሻዎች ሰርቷል። ጎርጎራ ላይ ፕሮጀክት አለ፤ አምቦ ላይ ፕሮጀክት አለ፤ ባሌ ላይ ፕሮጀክት አለ፤ ኮይሻ ላይ ፕሮጀክት አለ። ታላቁ የኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብ በራሱ የቱሪስት መስህብ ነው። እነዚህ ነገሮች አገራችን ሰላም እስከሆነች ድረስ የማይዛቅ የቱሪዝም ሐብት ናቸው ብለን በተስፋ እየጠበቅን ነው" ሲሉ አቶ አበበ ተናግረዋል።

Äthiopien Orthodoxe Christen
የአክሱም ስልጣኔ ቅሪቶች፣ የአክሱም ሐውልቶች እና የጽዮን ቤተ-ክርስቲያን የሚገኙባት የአክሱም ከተማ በህዳር 2012 በኤርትራ ወታደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ እንደተገደሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሒውማን ራይትስ ዎች ባወጧቸው የምርመራ ዘገባዎች ይፋ አድርገዋል።ምስል picture-alliance/dpa/C. Frentzen

አቶ አበበ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚሉት ጉዳይ ግን በኢትዮጵያ ሰላም ማውረድ ነው። ይኸ የእርሳቸው ሐሳብ ብቻ አይደለም። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአገር አስጎብኚ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ለዘርፉ ማገገም ተስፋቸውን በቀዳሚነት በኢትዮጵያ ሰላም ላይ ጥለዋል። "አሁን ያለው የጦርነቱ ሁኔታ ቢስተካከል፤ እየተስተካከለ ያለም ይመስለኛል አሁን፤ ኢትዮጵያ በሌላው ዓለም የመጎብኘት ዕድሏ በጣም የጨመረ ይመስለኛል። ጨምሯልም ብዬ ነው የማስበው። አሁን ያሉት ነገሮች ቢስተካከሉ ምን አልባት እንዲያውም ማስተናገድ ከሚያቅተን በላይ እንግዳ እናገኛለን ብዬ ነው እኔ ተስፋ የማደርገው። ተጨማሪ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተዋወቁ፤ መጎብኘት አለባቸው የተባሉ ቦታዎችም አሉን። የበለጠ እንጎበኛለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን ያለችውን ጊዜ እንደምንም ማሳለፍ ነው ለብዙዎቻችን የሚከብደን እንጂ፤ ይቺን ካለፍን በጣም የተሻለ መጪ ጊዜ አለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ሰገን ተናግረዋል።

አገራችን ሰላም ከሆነ ወደ ፊት ብዙ ሥራ ይሰራል ብለን እናስባለን" ያሉት አቶ በቀለ ጋረድ በበኩላቸው ዘርፉ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት "አስጎብኚዎችን እያበረታቱ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረግንው ጥረት አልሰመረም።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ