1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋትና የህዝቡ ግንዛቤ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 11 2012

የዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሲል የፈረጀው ኮቪድ 19 የሰዎችን መተንፈሻ አካላት የሚጎዳ ተላላፊ አይነቱ የተለየ አዲስ ተሐዋሲ መሆኑ ከተነገረ ወራት ተቆጠሩ። ሳይንቲስቶችን አሁንም በመቶ ሺህዎች ለተቆጠሩ የበርካታ ሃገራት ሰዎች ሞት ምክንያት ስለሆነው ተሐዋሲ የሚያደርጉት ምርምር እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/3cUCV
Äthiopien Coronavirus-Callcenter 8335
ምስል DW/Solomon Muchie

«መዘናጋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ይበዛሉ»

የዓለምን ትኩረት የሳበውና የወትሮ እንቅስቃሴዋን ለጊዜው ምንነቱ ወዳልታወቀ አቅጣጫ ያዞረው ኮቪድ 19 ዛሬም የሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሏል። 349 147 ደርሰዋል በመላው ዓለም በተሐዋሲው የረገፉት። የተያዙትም 5 ሚሊየን ሊደፍኑ 200 ሺህ ገደማ ቀርቶታል። ይህ ቁጥር በአንድ ጀንበር አልነበረም ከዚህ የደረሰው። 32ሺህ ዜጎቿን በሚያስደንቅ ፍጥነት ያጣችው ጣሊያንም ሆነች ከኋላዋ ተነስታ በሦስት እጥፍ በልጣ 90ሺህ ዜጎቿን የቀበረችው ዩናይትድ ስቴትስ ተሐዋሲውን የቻይና፤ የሚጎዳውም ቻይናን ግፋ ቢል እሲያን ነው የሚል መዘናጋት እንደነበረባቸው ዛሬ በቁጭት ይነገርባቸዋል። በሽታው ሰደድ እሳት ነው ይሉታል። በትንሿ አንዲት አካባቢ ታይቶ ውስጥ ውስጡን ተቀጣጥሎ ድንገት ሰፊ አካባቢን የሚሸፍን አደገኛ ተላላፊ በሽታ ነው። ለዚያውም ገና የመተላለፊያ መንገዱም ሆነ የሚጎዳው የአካል ክፍል በመበርከቱ ለተመራማሪዎች ሌላ የቤት ሥራ እንደሆነ የቀጠለ። 

Äthiopien | Vaterstetten | Alem Katema Verein | Corona Hilfe- Schuztmaksen
ምስል Alexander Bestle

የተሐዋሲው ምንነትና የትመጣ ተጠንቶ ሳያበቃ፤ የሚጎዳው የአካል ክፍልም አይነቱ እየበረከተ መያዣው በጠፋበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የታማሚዎች ቁጥር በትንሹ ጀምሮ ከፍ እያለ በመሄድ ላይ መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር የሚወጣው መረጃ ያመለክታል። ትናንት እንደተሰማው በ24 ሰዓት ውስጥ ምርመራ ከተደረገላቸው 35ቱ፤ ዛሬ ደግሞ ከተመረመሩት 14 ሰዎች በኮቪድ 19 መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 365 አድርሷል። የታማሚዎች ስብጥር በተመለከተም በአዲስ አበባ የተገኙት ቁጥር የበለጠ ሲሆን በመቀጠል ሶማሌ ክልል፣ እንዲሁም ኦሮሚያና ትግራይ ክልል መሆናቸው ተገልጿል። እስካሁን በኢትዮጵያ ምርመራው የተደረገላቸው 62,300 ሲሆኑ በተሐዋሲው ተይዘው በለይቶ ማቆያ ሆነው የህክምና ክትትል የሚደረግላቸው 238 መሆናቸውም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በፅኑ የታመሙ የሉም፤ አዲስ ያገገሙ ሰዎች  4 ደርሰዋል። ከበሽታው ማገገማቸው የተመዘገበው በጥቅሉ 120 ናቸው። የዓለም መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡትና መላው ዓለምን በየዕለቱ ማነጋገሩ የቀጠለው አዲሱ የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታዩ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ጭራሽ ሰዎች ስለበሽታው ግንዛቤ ያላቸው እንደማይመስል በየማኅበራዊ መገናኛው የሚሰራጩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች ያሳያሉ። ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኙ የዶቼ ቬለ ዘጋቢዎች ጥቂቱን በያሉበት ያስተዋሉትን እንዲያካፍሉን ጠይቄያቸዋለሁ። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዴት ይሆን? ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ማዕቀፉ ያድምጡ። 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ