1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮቪድ 19 አፍሪቃ ውስጥ መስፋፋት ስጋት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 1 2013

ክትባት ለዜጎቻቸው በስፋት ማደረስ መቻላቸውን የሚገልጹ ሃገራት ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ቀስ በቀስ ኅብረተሰባቸው ላይ ጥለውት የሰነበቱትን እገዳ ማንሳት ጀምረዋል። በአንጻሩ የአፍሪቃ ሃገራት ዛሬም ክትባቱን ለማግኘት ይጠባበቃሉ።

https://p.dw.com/p/3ubRB
Data visualization COVID-19 New Cases Per Capita – 2021-06-02 – Africa - English

«የኮቪድ 19 ክትባት አቅርቦት ጥያቄ»

በመላው ዓለም በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 174,3 ሚሊየን በልጧል። ከእነዚህ መካከልም 157,9 ሚሊየኑ ከበሽታው ሲያገግሙ 3,75 ሚሊየን በላይ ሰዎችም አልቀዋል። አሁን አስቀድሞ በወረርሽኙ የተጠቁና በርካታ ዜጎች ያለቁባቸው ሃገራት የተሐዋሲውን ስርጭት ለመግታት ባደረጉት ከዓመት በላይ የዘለቀ እልህ አስጨራሽ ጥረትና ክትባትን ለየዜጎቻቸው የማዳረስ ሥራ ወረርሽኙ አሳርፎባቸው ከነበረው ተጽእኖ በመጠኑ ማንሰራራት የጀመሩ ይመስላል። በተለይ እዚህ ጀርመንና የአውሮጳ ሕብረት አባል ሃገራት የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት መቃረብን በማስመልከት በወረርሽኙ ስጋት በየቤቱ ተወስኖ የከረመው ኅብረተሰብ በሙቀቱ ወቅት በመጠኑም ቢሆን ተንቀሳቅሶ መንፈሱን እንዲያነቃቃ የአየር እና የየብስ ድንበሮቻቸውን ክትባት ለወሰዱ አለያም ተመርምረው ከተሐዋሲው ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጫ ለያዙ እንዲሁም በኮቪድ 19 ተይዘው መዳናቸው የተረጋገጠ ሰዎች ከሀገር ወደ ሀገር ተንቀሳቅሰው መዝናናት እንዲችሉ መፍቀዳቸውን እያሳወቁ ነው።

Deutschland | Coronavirus | Restaurant in Berlin
ምግብ ቤቶች ማስተናገድ ጀምረዋል፤ በርሊን ከተማምስል Maja Hitij/Getty Images

በተቃራኒው አሁን በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት የተሐዋሲው ስርጭት ስጋት መሆኑ ይታያል። ለምሳሌ ዩጋንዳ የዜጎች እንቅስቃሴና መስተጋብር ላይ የጥንቃቄ እገዳ መጣሏን የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ዝርዝር ማብራሪያ አመላክተዋል። ሙሴቪኒ በዚህ መልእክታቸው በሀገሪቱ የጤና ባለሞያዎች የተሰጡ የጥንቃቄ ማሳሰቢያዎችና ምክሮችን ኅብረተሰቡ በማስተዋል ተግባራዊ እንዲያደርግ ነው ጥሪ ያቀረቡት። ዩጋንዳ ውስጥ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ክፍት መሆን የሚችሉት የመድኃኒት መሸጫዎች ብቻ ናቸው። በሠርግም ሆነ በቀብር ሥርዓት ላይ ከ20 በላይ ሰዎች መገኘት አይችሉም። ዩጋንዳ ብቻ ሳትሆን ስጋቷን ያሳየችው የዓለም የጤና ድርጅት ባጠቃላይ አፍሪቃ ውስጥ የኮቪድ 19 መስፋፋት እንዳሰጋው አመልክቷል። የአፍሪቃ ሃገራት የጤና ጥበቃ ሥርዓት እንዲህ ላለው ወረርሽኝ ይኽ ነው የሚባል ዝግጅት እንደሌለው ያመለከተው ድርጅቱ በዚህ መሀል በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊበራከት እንደሚችል ነው ያሳሰበው። በአፍሪቃ የዓለም የጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኮቪድ 19 ቀውስ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቲየርኖ ባልዴ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ በተለይ በደቡባዊ አፍሪቃ ወረርሽኙ መስፋፋቱን አመላክተዋል።

«በአሁኑ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታን እየተመለከትን ነው። በደቡብ አፍሪቃ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች በደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት እና በደቡብ አፍሪቃ ዙሪያ በሚገኙ ሃገራት ባጠቃላይ ማለት ይቻላል። በዚያም ላይ በእነዚህ ሃገራት ሁሉ በዚህ ጊዜ ከአንድ ዓመት እና ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በሆነው ወረርሽኝ ምክንያት የሚታየው መዳከም በጣም አስቸጋሪ ነው።»

እሳቸው እንደሚሉት የወረርሽኙ ስርጭት በደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት ላይ ቢጠናም መካከለኛው እና በሰሜናዊ አፍሪቃ ሃገራትም መስፋፋቱ አሳሳቢ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ሃገራቱ ወረርሽኙን የመቋቋም አቅማቸው ሌላው የስጋት ምንጭ ነው። አሳሳቢነቱንም ዶክተር ባልዴ በአጽንኦት ይገልጻሉ።

Illustration eine Coronavirus-Mutation
ምስል DesignIt/Zoonar/picture alliance

«በጣም አሳሳቢ ነው፤ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን እንገኛለን፤ በዚህም በአንዳንድ ሃገራት በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን እያየን ነ፤ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪቃ፣ በናሚቢያ፣ በአንጎላ እንዲሁም በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ጎንጎ። በሌላ በኩል ደግሞ ሁለተኛው የወርሽኝ ማዕበልን በሌሎች ቦታዎችም እያየን ነው። እናም መለዋወጥ አለ። ዋናው አስፈላጊ ነጥብ ግን እዚህ ጋር ይዞታውን በቅርበት መከታተልና በየሃገራቱም ሆነ በተባባሪዎች አማካኝነት አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ ነው።»

አስፈላጊ እና ውጤታማ ርምጃዎች ሲሉም ክትባቱን፤ የኦክስጂን አቅርቦትን ማጠናከሩን እንዲሁም በኅብረተሰቡ ውስጥ አስፈላጊዎቹ የጥንቃቄ ርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚያስተባብር ግብረኃይልን ማሰማራትን እንደሚያጠቃልልም አመልክተዋል። የአፍሪቃ ሃገራት የጤና አገልግሎት ተቋማትን የማጠናከሩ ሥራ ገና ዓመታትን የሚፈጅ የረዥም ዓመት ዕቅድ መሆኑ ግልጽ ነው። አሁን ላለው ወቅታዊ ችግር በበለጸጉት ሃገራት እየተሰጠ የሚገኘው የኮቪድ 19 ክትባት በርካቶች አፍሪቃ ውስጥ ቢፈልጉም የሚያገኘት ዕድላቸው ጠባብ መሆኑ ይነገራል። የዓለም የጤና ድርጅትም በተደጋጋሚ የበለጸጉ ሃገራትን ለሌሎችም እንዲያስቡ ሲወተውት ታይቷል። በዚህ ረገድ ድርጅቱ ለአፍሪቃ ምን እያደረገ ይሆን? የድርጅቱ የአፍሪቃ ጽሕፈት ቤት የኮቪድ 19 ቀውስ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቲየርኖ ባልዴ።

«የህንድ ኩባንያ አስትራዛኒካ ክትባትን አቅርባለሁ ብሎ እንደነበር ይታወሳል፤ ይኽ ሕንድ ላይ ካለው ሁኔታ ጋር የሚገናኝ ሲሆን አማራጭ ተስፋና ቃል የተገቡልንም አሉ። አብዛኞቹ የምዕራብ ሃገራት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን ያሉት በአሁኑ ጊዜ ተጨማሪ ክትባቶችን ለአፍሪቃ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል። ይኽ ረዥም ጊዜ እንደማይወስድ እና ባስቸኳይ ይቀርብልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይኽ በዚህ እንዳለ ደግሞ በየሃገራቱ በአነስተኛ መጠን ያሉት ክትባቶች በጥንቃቄ ይዳረሳሉ ብለን እንጠብቃለን። አፍሪቃ ውስጥ አሁን ካለን ክትባት 5,0 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው እስካሁን ሥራ ላይ የዋለው። ስለዚህ ሕዝቡ ክትባቱን ለመውሰድ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል። ይኽ በጣም አስፈላው ነገር ነው።»

Uganda Coronavirus Impfung
ምስል Luke Dray/Getty Images

በአፍሪቃ የዓለም ጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኮቪድ 19 ቀውስ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የኮቮድ 19 ክትባትን አፍሪቃ ውስጥ ሰዎች በቀላሉ እንዳልተቀበሉት ነው ያመለከቱት። በእርግጥ ይኽን መሰሉ አዝማሚያ በአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን  በሌሎችም ሃገራት መታየቱ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። እንዲያም ሆኖ ከሌሎች ሃገራት አንጻር አቅርቦቱ ሲታይ አቅም በሌላት አፍሪቃ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።  

ለምሳሌ ጀርመን ከትናንት ጀምራ የኮቮድ 19 ክትባትን መከተብ ለሚፈልጉ በሙሉ ዝግጁ ማድረጓን አስታውቃለች። ጀርመን ላለፉት ሳምንታት በሽታ የመከላከል አቅማቸው በተለያዩ ተላላፊ ያልሆኑ ነገር ግን ጠንከር ያለ የህክምና ክትትል በሚያስፈልጋቸው ህመሞች ለተያዙ ሰዎች እና በዕድሜ ለገፉ ወገኖች ቅድሚያ ስትሰጥ በመስጠት ክትባቱን አዳርሳለች። ክትባቱን የሚፈልግ ያውም አማርጦ ማግኘት እንደሚችል ነው ከሰዎች የየግል ገጠመኝ የተረዳነው።

በአፍሪቃ የዓለም ጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኮቪድ 19 ቀውስ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቲየርኖ ባልዴ እንዳመለከቱት እስካሁን አፍሪቃ ውስጥ በኮቫክስ አማካኝነት ከቀረበው ክትባት የወሰደው ኅብረተሰብ 5,0 በመቶ የሚሆን ነው። እንደ የዓለም የጤና ድርጅት ግምት በቀጣይ ሦስት እና አራት ወራት በርካቶች ክትባቱን እንዲያገኙ ይደረጋል።

«በወቅቱ የዓለም የጤና ድርጅት ጉባኤ እስከ መስከረም ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነው ኅብረተሰባችን ክትባቱን እንዲያገኝ ለማድረግ አቅደናል። ለዚህም በርካታ ጥረቶች እንደተደረጉ ነው፤ በጣም ከሩቅ እንደተነሳን ይታወቃል። ከወራት በፊት ይኽ ነው የሚባል ክትባት እንኳን በአህጉራችን አልነበረንም። አሁን ግን 50 ሚሊየን ገደማ ክትባት ቀርቧል፤  እናም ለጊዜው ጥሩ የሚባል ልምድ ነው ያለው፤ ሆኖም ግን የክትባቱ ብዛት ፍጹም በቂ አይደለም። ይኽም ግልጽ ነው። ተጨማሪ ክትባቶችን ለማግኘት የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፤ ሆኖም እዚህ ጋር አጽንኦት ልሰጥ የምፈልገው ሰዎች ሄደው ክትባቱን እንዲወስዱ ነው።»

Madagascar Covax
ምስል Mamyrael/AFP

ከዚህም ሌላ  አፍሪቃ የክትባቱ አቅርቦት ዋነኛ ችግሯ እንደሆነ የመነገሩን ያህል ሰዎች ክትባቱን በጥርጣሬ መመልከታቸውም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ነው ዶክተር ባልዴ ያመለከቱት። ምንም እንኳን እስከ መስከረም ወር ድረስ 30 በመቶው አፍሪቃዊ ይከተባል ቢባልም የተሐዋሲውን ስርጭት በጋራ የመከላከል በህክምናው ኸርድ ኢሚውኒቲ የሚባለውን ለመገንባት ይቻል ይሆን?

«ይኽን በእርግጠኝነት ለመናገር በጣም አዳጋች ነው። አሁን ካለው አንጻር ግን በርካታ ቁጥር ያለው የተከተበ ሰው መኖሩ መልካም ነገር ነው የሚሆነው። ይኽ ወሳኝ ጉዳይ ነው፤ አንዳንዱን ወሳኝ ነገር ላናገኝ ብንችልም ይኽን በአህጉዳችን ማድረጉ በራሱ የማይናቅ ትልቅ ስኬት ነው። እዚያ ላይ ለመድረስ በርካታ መሰናክሎች አሉ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የምናከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ወደዚያ ሊያደርሱን የሚችሉ መንገዶች ናቸው።»

 የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት ብቻ በ14 የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሳያሰልስ እየጨመረ መሄዱን፤ በተለይም ደግሞ በስምንት የአፍሪቃ ሃገራት ቀደም ሲል ከነበረው ከ30 በመቶ በላይ ከፍ ብሎ መታየቱን አመልክቷል። በተለይም ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት የክረምቱ ወራት በመቃረቡ ቅዝቃዜውን ተከትሎ ወረርሽኙ ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

Palästina COVID-19 | COVAX Initiative | Ankunft der Impfstoffe
ምስል Ayman Nobani/Xinhua/picture alliance

በዓለም የጤና ድርጅት በሚደገፈው ኮቫክስ 600 ሚሊየን ክትባት ለአፍሪቃ እንደሚቃረብ ታቅዶ ነበር። በዚህም ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን አፍሪቃዊ ለመከተብ ታስቧል። ሆኖም የዓለም የጤና ድርጅት አሁንም ተጨማሪ 200 ሚሊየን ክትባት እስከ መስከረም አፍሪቃ ውስጥ ለማዳረስ ዕቅድ ይዟል። እንዲያም ሆኖ ክትባቱን ለማግኘቱ ካለው ተግዳሮት ባልተናነሰ ክትባቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚደረገው ጥረት ሌላው ፈተና መሆኑ እየተነገረ ነው።  

በዚህ አጋጣሚ አንድ የዘወትር አድማጫችን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም አዲስ አበባ ላይ ውስጥ የታዘቡትን ለእናንተም ማጋራቱ ጠቃሚ ይመስለናል። በሀገሪቱ በድጋሚ ኅብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ ጭንብል እንዲያደርግ የሚያስገነዝበው መመሪያ ከወጣ ወዲህ ቀደም ሲል የታዩ መዘናጋቶች በዚህ ረገድ እየተስተካከሉ መጥተዋል ይላሉ እኚህ ታዛቢ፤ በአደባባይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያደርጉ በዝተዋል ይኽም ግሩም ይበል ይላሉ። ሆኖም አብዛኛው ሰው በተለያዩ አጋጣሚዎች በቤትም ሆነ በአዳራሽ የሚሰባሰብበት ዝግጅት ላይ ሲገኝ ሰብሰብ ብሎ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦም ቢሆን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛውን ወደ ኪሱ ይከታል። ለመሆኑ ማኅበራዊ መራራቅ የሚለው ነገር የቱ ጋር ነው? በቤት ውስጥ ሰዎች በመሰባሰባቸው ንፋስም እንደሚፈለገው መጠን እንዲህ ባለው ሁኔታ ስለማይገኝ ጥንቃቄው ይጓደላል። እናም ራስን ከተሐዋሲው መከላከል ለሌላውም ማሰብ ነውና ክትባቱ ቢገኝም ባይገኝም ጥንቃቄው መቀጠል እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ