1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ተዋህሲ ክትባትና ተግዳሮቶቹ

ረቡዕ፣ መጋቢት 8 2013

በዓለም ላይ ሚሊዮኖችን ለህመምና ለሞት እየዳረገ የሚገኘውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራት ለዜጎቻቸው ክትባት መስጠት ጀምረዋል።ይሁንና የክትባቱ ደህንነት ፤ውጤታማነትና የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዲሁም ክትባቱ በበቂ ሁኔታ አለመገኘት አሁንም ፈተዎች ናቸው።

https://p.dw.com/p/3qktR
Weltspiegel 17.03.2021 | Corona | AstraZeneca-Impfstoff
ምስል Hannibal Hanschke/REUTERS

የኮሮና ተዋህሲ ክትባትና ተግዳሮቶቹ



የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን  ጉዳት ለመቀነስ በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል።እነዚህ ምርምሮች ፍሬ አፍርተውም ለበሽታዉ መከላከያ ይሆናሉ የተባሉ የተለያዩ ክትባቶችን ማምረት ተችሏል።በርካታ ሀገራትም ዜጎቻቸውን ከወረርሽኙ ለመታደግ ክትባቶቹን በመስጠት ይገኛሉ። ኢትዮጵያም በሳምንቱ መጀመሪያ የተዋህሲውን መከላከያ  ክትባት ማሰራጨት ጀምራለች።ያም ሆኖ የክትባቱ ውጤታማነት፣ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዲሁም ክትባቱ  በሚፈለገው መጠን አለመገኘት አሁንም ድረስ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ለክትባት ያለው የተሳሳተ ግንዛቤም ሌላው ችግር  መሆኑ ይነገራል።
በህክምናው ዘርፍ ሳይንስ ካበረከታቸው ግኝቶች መካከል የመከላከያ ክትባቶች  የሰው ልጆችን ህይወት ከመታደግ አኳያ ግንባር ቀደም የምርምር ውጤት  ነው።ያም ሆኖ  በክትባቶች ላይ እንደየ ማኅበረሰቡ አኗኗር፣ ባህል፣ ዕምነት  ወይም የግንዛቤ ደረጃ  ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው የተዛቡ አመለካከቶች በየ ዘመኑ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።በኮቪድ-19 ክትባቶች ላይም የጎንዮሽ ጉዳቶች ጋር በተያያዘ ፤ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸውና ኅብረተሰቡ በክትባቶቹ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ መረጃዎች ሲሰራጩ ይታያል።በአንፃሩ በክትባቱ ላይ በመተማመን መዘናጋትም ሌላው ችግር መሆኑ ይነገራል።በኦሃዮ ስቴት ዩንቨርሲቲ የግሎባል ዋርሚንግ  ኢኒሸቲቭ የምስራቅ አፍሪቃ ተጠሪና የመድሃኒት ምርምር ባለሙያ ዶክተር ጌትነት ይመር ግን የመከላከያ ክትባት ማለት መቶ በመቶ በሽታ መከላከል እንዳልሆነ ያስረዳሉ። 
በሌላ በኩል ከተዋህሲው ራሱን የመለዋወጥ ባህሪ ጋር ክትባቶቹን አስማምቶ የመቀጠል ችግርና በክትባቶቹ ላይ በየጊዜው የሚመዘገቡ የጎንዮሽ ጉዳቶችም ፈተና ሆነው ቀጥለዋል።
ክትባቶቹ መጠነኛ ራስምታት፣ትኩሳት፣የተወጋበት አካባቢ እብጠትና ና ሌሎች ዘላቂ ጉዳት የማያስከትሉ  በጥናት የተረጋገጡ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳላቸው ሲገለፅ ቢቆይም ፤በአውሮፓ የመድሃኒት አስተዳደር ያለፈው ጥር ማረጋገጫ ያገኘው የአስትራ ዜኒካ ክትባት የደም መርጋት ችግርን የመሳሰሉ ለሞት የሚያበቁ ከባድ የጤና ችግሮችን አምጥቷል በሚል ጀርመንና ፈረንሳይን ጨምሮ በተለያዩ ሀገሮች ክትባቱ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል።
 የአውሮፓ የመድሃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ ከአስር በላይ  የህብረቱ አባል ሀገሮች የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ የኮሮና ክትባትን ካገዱ በኋላ በትናትናው ዕለት በሰጠው ምላሽ ክትባቱ የደም መርጋት መንስኤ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አለማግነቱን አመልክቷል ፡፡ 
ዋና ዳይሬክተሯ ኤመር ኩክ  እንደተናገሩት ኤጀንሲው አሁንም ቢሆን የአስትራዚኔካ ክትባት ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ህመምና የሞት አደጋን የመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።
የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የአስትራዜኔካ ክትባቱ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን እና በክትባቱ እና በተገለፀው የደም መርጋት ችግር መካከል ምንም ግንኙነት እንደሌለ አመልክቷል።፡ ያም ሆኖ በክትባቱ ላይ  አመኔታን እንደገና መመለስ ቀላል አይመስልም። 
ከዚህ ጋር ተያይዞም በመደበኛ ሁኔታ የመከላከያ ክትባትን ለማበልፀግ በአማካኝ ከአስር ዓመት በላይ የሚወስድ ሲሆን የኮሮና ወረርሽኝ አሳሳቢነት አፋጣኝ መፍትሄን  የሚጠይቅ በመሆኑ ክትባቶቹ ከዓንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ መዘጋጀታቸው ለችግሩ መነሻ ነው የሚሉም አሉ።ዶክተር ጌትነት ይመር ግን አይስማሙም።እንዲያውም የኮቪድ19 ክትባት  አዲስ የምርምር በር ከፍቷል ባይ ናቸው።
ኮቫክስ ከተባለው ኩባንያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የአስርራዜኒካ ክትባት ሰሞኑን የተረከበው የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር በበኩሉ በክትባቱ ላይ የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት መኖሩን ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ እስካላገኘ ድረስ ክትባቱን ማሰራጨቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።የመድሃኒት ባለሙያው ዶክተር ጌትነትም  ማንኛውም የመከላከያ ክትባትም ይሁን መድሃኒት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው አስታውሰው፤ ይሁን እንጅ ጉዳቱ መመዘን ያለበት ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር መሆኑን ይገልፃሉ።ከዚህ አንፃር የአስትራዜኒካ ክትባትም ይሁን ሌሎቹ ክትባቶች በዓለም ላይ በተዋህሲው ሳቢያ ህይወታቸውን ከሚያጡ ሰዎች ጋር ሲነፃጸር የተመዘገበው የጎንዮሽ ጉዳት ዝቅተኛ ነው ይላሉ።ያም ሆኖ በክትባቱ የተነሳ በሚመዘገቡ ጉዳቶች ላይ የነቃ  ክትትል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 
የክትባቶቹ  ውጤታማነትም ይሁን  የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳት ምንም ይሁን ምን በተለይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ ጉዳት ለመቀነስ  ህብረተሰቡ ከመዘናጋት ይልቅ  የመከላከያ መንገዶችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ባለሙያው መክረዋል።

Schweden Malmo | Coronavirus | AstraZeneca Impfung
ምስል Joahn Nilsson/TT News Agency/AFP/Getty Images
Niederlande EMA |
ምስል Robin Utrecht/dpa/picture alliance
Weltspiegel 15.03.2021 | Corona | AstraZeneca-Impfstoff
ምስል Dado Ruvic/REUTERS

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 
ፀሀይ ጫኔ 
እሸቴ በቀለ