1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ተኅዋሲ ክትባት በአውሮጳና ጀርመን 

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2013

የጀርመን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚለው ክትባቱን ለተቀረውን የኅብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ ወራት ይወስዳል። ምናልባትም ከሦስት እስከ አራት ወራት ሊወስድ እንደሚችል ይጠበቃል።የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ ቢያንስ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ህዝብ መከተብ እንደሚኖርበት ነው የጤና ሚኒስቴር የሚናገረው።

https://p.dw.com/p/3nL1J
Coronavirus – Impfbeginn Berlin
ምስል picture alliance/dpa/dpa Pool

የኮሮና ተኅዋሲ ክትባት በአውሮጳና ጀርመን 

27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት የኮሮና ተኅዋሲን መከላከያ ክትባት ካለፈው እሁድ አንስቶ መስጠት ጀምረዋል።ዩናይትድ ስቴትስ ብሪታንያ እና ካናዳ ክትባቱን መስጠት ከጀመሩ ከሳምንታት በኋላ አባል ሃገራት ኅብረታቸውን ለማሳየትም ጭምር በአንድ ቀን በአንድ ላይ ነው ክትባቱን ያስጀመሩት። ክትባቱ አውሮጳ ከበሽታው የምትገላገልበት አንዱ መንገድ ተደርጎ ተወስዷል።ያም ሆኖ መጀመሩ የድሉ መጀመሪያ እንጂ የወረርሽኙ ፍጻሜ ማለት እንዳይደለ የሚያሳስቡም አልጠፉም ።የክትባቱ መጀመር የሚሊዮኖችን ሕይወት ያጠፋውን  የኮሮና ተኅዋሲን በአፍና አፍንጫ ጭምብልና በሌሎችም የመከላከያ አልባሳት ሲታገሉ ለቆዩት ለጤና ባለሞያዎች ትልቅ የመንፈስ እፎይታ አስገኝቷል።ለኅብረተሰቡም ከበሽታው የመጠበቅ ብሩህ ተስፋ ተደርጎ ተወስዷል።የኮሮና መከላከያ ክትባት ባለፈው እሁድ በይፋ መስጠት የጀመረችው ጀርመን እንደ ሌሎቹ ሃገራት ሁሉ እድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ ለሆነ አዛውንትና ለኮሮና ተጋላጭ የጤና ባለሞያዎች ቅድሚያ ሰጥታለች። የመጀመሪያዎቹ የባዮንቴክና የፋይዘር ኩባንያዎች የኮሮና ተኅዋሲ መከላከያ ክትባት ለ16ቱም የጀርመን ፌደራል ግዛቶች የተከፋፈለው ቅዳሜ ነበር።በመላ ጀርመን ክትባት የጫኑ ተሽከርካሪዎች የጀርመኑ ባዮንቴክና የአሜሪካን አጋሩ ፋይዘር የሰሯቸውን ክትባቶች በፖሊስ ጥበቃ ለአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማትና  ለክትባት መስጫ ጣቢያዎች አድርሰዋል።ከትናንት በስተያ እሁድ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የመጀመሪያው ጸረ ኮሮና ተኅዋሲ ክትባት  የተሰጣቸው የ101 ዓመት እድሜ ባለፀጋ በበርሊን የአዛውንቶች መጦሪያ የሚገኙት ጌርትሩድ ሃዘ ናቸው። በመጦሪያው 9 ዓመታት የኖሩት ሃዘ የመጀመሪያዋ ተከታቢ ለመሆን ብዙ አውጥተው አውርደው ነው የወሰኑት ።
«ከመጀመሪያዎቹ መካከል መሆን የለብኝም ብዬ አሰብኩ።አሁን ይህ አያስፈልገኝም አልኩ።ከዚያ በፊት ሌሎች ስለ ክትባቱ የሚሉትን መስማት ይሻላል ብዬ አሰብኩ።ከዚያ በኋላ ግን ሃሳቤን ቀየርኩና።እኔም ከሌሎቹ ጋር እከተባለሁ አልኩ ።»
ሃዘ በሚጦሩበት ሥፍራ ከሚገኙት 90 አዛውንቶች አብዛኛዎቹ እሁድ ተከትበዋል።በመጦሪያው በሐኪምነት የሚሰሩት ኢርምጋርድ ላንድግራፍ እንደሚሉት አዛውንቱ ከመከተባቸው በፊት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።ተጧሪዎቹም መከተባቸው በበሽታው እንዳንያዝ ይላከልልናል ብለው ያስባሉ።
«ሁሉም ነገር በደንብ ነው ዝግጅት የተደረገበት።አዛውንቱ ለመከተብ ደስተኛ ናቸው።የመጀመሪያዎቹ በመሆናቸውም ኩራት ተሰምቷቸዋል።ሁሉም በክትባቱ ተጨማሪ ጥበቃ እንደሚያገኙ ስለሚያውቁ አድንቀዋል።»
ዶክተር ላንድግራፍ የኮሮና መከላከያ ክትባት ፣ብዙዎች የበሽታው ሰለባዎች በሆኑባቸው አዛውንቶች በሚጦሩባቸው ስፍራዎች በቅድሚያ እንዲሰጥ መደረጉን ያደንቃሉ። በርሳቸው አስተያየት ይህ መደረጉ በዚህን መሰል ተቋማት የሚገኙ ሰዎችን ከበሽታው ለመጠበቅ አንዱ ዘዴ ነው። 
«በአሁኑ ጊዜ ኮሮና በአዛውንቶች መጦሪያ እጅግ እየተስፋፋ ነው። እጅግ አሰቃቂ ነው።እናም የኛ ተቋም የመከላከያ ክትባቱን በማግኘት የመጀመሪያው በመሆኑ ደስተኞች ነን።በዚህ እርምጃም ይህን ከባድ ወረርሽኝ ከመጦሪያውና ከበሽተኞቻችን ለማስወገድ አንድ ተጨማሪ መንገድ ይሆናል።»
።የዛሬ ዓመት  በጥር ወር ነበር የኮሮና መነሻ ከሆነው ከቻይናው ዉሃን ግዛት የመጡ ሁለት ቻይናውያን ባልና ሚስት  በስፓላንዚ ኢጣልያ ተኅዋሲው እንደተገኘባቸው የተረጋገጠው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ስፓላንዛኒ የምትገኝበት ሎሞባርዲ   የአውሮጳ የኮሮና ማዕከል ሆነች።በኢጣልያ ኮሮና ከገደላቸው አንድ ሶስተኛው ከሎምባርዲ ናቸው።በሽታው በኢጣልያ ቁጥሩ 72 ሺህ የሚጠጋ ሰው ገድሏል።ይህም ኢጣልያን ከአውሮጳ በኮሮና በሞቱ ሰዎች ብዛት ቀዳሚውን ስፍራ እንድትይዝ አድርጓል።በ27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ቢያንስ 16 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ተኅዋሲ ተይዘዋል።ከ336 ሺህ በላይ ደግሞ በተኅዋሲው ምክንያት ሞተዋል።የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚሉት ግን  ትክክለኛው የተኅዋሲው  ሰለባ ቁጥር ምርመራዎች ውስን በመሆናቸው ምክንያት በትክክል አይታወቅም።በኢጣልያ እሁድ ክትባቱ የተጀመረው በአውሮጳ በኮሮና ተኅዋሲ የተያዙ የመጀመሪያዎቹ የተባሉ ሰዎች በተገኙባት በስፓላንዛኒ ነው።
በርሊንን ከቦ በሚገኘው በብራንድቡርግ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ግሮስሬሸን የተባለችው የ100 ሺህ ህዝብ መኖሪያ በየቀኑ 500 ሰው በኮሮና ተኅዋሲ የሚያዝባት ከተማ ናት።በዚህች ከተማ የሚገኙ የአዛውንቶች መጦሪያ ተቋማት ጥብቅ መመሪያዎችን ተግባራዊ አድርገዋል።አዛውንቶቹን እንዲጠይቁ የሚፈቀድላቸው የቅርብ ዘመዶቻቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም ቢሆን ከኮሮና ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ሊሆን ይገባል።ያም ሆኖ በዚህ የአዛውንቶች መጦሪያ ኮሮና ከመሰራጨት ያገደው ነገር የለም።እናም በዚህ ከተማ የክትባቱ መምጣት በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቷል።በክትባቱ ተስፋ ከሚያደርጉት አንዷ የ87 ዓመቷ ሩዝ ሃይዘ ናቸው።ከሚገኙበት የአዛውንቶች መጦሪያ ክትባቱን የተሰጣቸው የመጀመሪያዋ ሰው ናቸው ሃይዘ።የተከተቡትም ከክፍላቸው በተሽከርካሪ ወንበር ወጥተው በርካታ ጋዜጠኞች ፊት ቀርበው ነው።ወይዘሮዋ ክትባቱ ሊያስከትል ይችላል የሚባሉትን ተጽእኖዎች ከማይፈሩት ሰዎች አንዷ ናቸው። እርሳቸው በሚጦሩበት ስፍራ 70 አዛውንት አሉ።ከመካከላቸው 12ቱ ብቻ ናቸው በመጀመሪያው እለት ለመከተብ ፈቃደኛ የሆኑት።ይህ ክትባቱን በሚመለከት የጤና ባለሞያዎች ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ ነው ። የብራንድንቡርግ ቀይ መስቀል ሃላፊ ሁቤርቱስ ዲመር ሰዎች በክትባቱ እምነት አድሮባቸው እንዲከተቡ ማድረግ ይገባል ይላሉ። የመጦሪያው ሠራተኞች ግን የመከተብ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው።ከመካከላቸው ግማሽ ያህሉ ለመከተብ አመልክተዋል።ስለ ኮሮና መከላከያ ክትባት ቀላል የማይባል ጥርጣሬ እንዳለ የአዛውንቶቹ መንከባከበያ ቤት ሃላፊ ነርስ ብያንካ ሴቢሽካ ክላውስ ያስረዳሉ።እርሳቸው እንደሚሉት አንዱና ዋነኛው ችግር ስለ ክትባቱ መረጃ መሰጠት የጀመረበት ጊዜና ክትባቱ የጸደቀበበት ወቅት መራራቁ ነው። 
«አዎ ትልቅ ጥርጣሬ አለ።ይህ ትክክል ነው።ክትባቱ እስከ ጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 21 ድረስ አልጸደቀም ነበር።እኛ ስለ ክትባቱ መረጃ መስጠት የጀመርነው ደግሞ ክትባቱ ሳይጸድቅ ነው።»
ሴቢሽካ ክላውስ የሰዎችን ጥርጣሪ የምር አድርጎ ከመውሰድ በፊት ትንሽም ቢሆን መታገስ ያስፈልጋል ይላሉ።የብራንድንቡርግ ክፍለ ግዛት የጤና ሚኒስትር ኡርዙላ ኖንማኽር በሴባሽካ ክላውስ ሃሳብ ይስማማሉ ሰዉን መጫን እንደማያስፈልግ ፣በውሳኔያቸው ላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲወያዩበት ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው የሚናገሩት።  
«ያ ማለት፣ክትባቱ ትናንት ነው የመጣልን፤ እንደመጣም በሺህዎች የሚቆጠሩትን በአስቸኳይ መከተብ ተጀምሯል።ይህ ጉዳይ ቅድሚያ ዝግጅት ይፈልጋል።በእድሜ የገፉት አዛውንቱ ስለ ክትባቱ ከዘመዶቻቸው ጋር መነጋገር እንዳለባቸው አስቀድሞ ግልጽ ሊደረግላቸው ይገባል።አንዳንድ ጊዜ ይህን በመሰለ ውሳኔ ላይ የነርሱ ወኪሎች መስማማት ይኖርባቸዋል።የመጀመሪያዎቹ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ተከታቢዎች ዘመዶቻቸው በተገኙበት ነው ክትባቱ የተሰጣቸው።እናም እነዚህ ሁሉ የአዛውንቶች መጦሪያዎች በጥንቃቄ ሊያቅዷቸው የሚገቡ ቅድመ ዝግጅቶች ናቸው።»
የጀርመን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚለው ክትባቱን ለተቀረውን የኅብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ ወራት ይወስዳል። ምናልባትም ከሦስት እስከ አራት ወራት ሊወስድ እንደሚችል ይጠበቃል።የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ ቢያንስ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ህዝብ መከተብ እንደሚኖርበት ነው የጤና ሚኒስቴር የሚናገረው።በርካታ የክትባት ማዕከላት ሥር ለመጀመር ተዘጋጅተዋል።የክትባቱን አከፋፋዮችም ክትባቱን ለማከፋፈል ዝግጁ ናቸው። ይሁንና እስካሁን በቂ የሚባል ክትባት እንዳልተከፋፈለ ነው የሚነገረው። በጀርመን ክትባቱን ማከፋፈሉ ከባድ ተግዳሮቶች አሉት። ክትባቱ አዲስ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም መሆኑና መቀመጥ ያለበትም ከዜሮ በታች 70 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ቅዝቃዜ ውስጥ መሆኑ ከባድ ፈተና ሆኗል።ክትባቱ በተገቢው ቅዝቃዜ ውስጥ መቆየቱ ጥሪጣሪ ውስጥ በከተታቸው ሰሜን ባቫርያን በመሳሰሉ አንዳንድ የጀርመን አካባቢዎች ክትባቱ እንዲዘገይ ተደርጓል።እነዚህ ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆነው አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተሰሩት በነዚህ ክትባቶች ላይ ኅብረተሰቡ ያደረበት ጥርጣሬ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ችግር ማስጋቱ አልቀረም። ይህን ለማስቀረት ይመስላል የጤና ባለሥልጣናት ሰዉ የተገኘው የክትባት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይገፋፋሉ። የበርሊን መስተዳድር የጤና ሚኒስትር ዲልከ ካላዪክ አንዱ ናቸው ናቸው። 
«ብዙ ሰዎች ይከተባሉ ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ።ምክንያቱም ይህ በዚህ አስከፊ ወረርሽኝ ወቅት የተገኘ ትልቅ እድል ነው። በ10 ወራት ውስጥ ክትባት ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም።ስለዚህ ብዙ ሰዎች ምክንያታዊ ሆነው ይከተባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»
ክትባቱ በ21 ቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ ነው የሚሰጠው።ሶሻል ዴሞክራቱ የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ካርል ላውተርባህ እንዳስረዱት እስከ መጋቢት 2021 ዓም አጋማሽ ከህዝቡ 5 በመቶውን ለመከተብ ነው የታቀደው።ይህ እንዲሳካም የክትባቱ ምርት እንዲጨምር አቅርቦቱም እንዲፋጠን ይጠይቃሉ። ጊዜው እየሄደ ነው የሚሉት ላውተርባህ፣ብዙ ሰዎች ጸረ ኮሮና ክትባት ማግኘታቸው በተለይ ባህርይው በመለዋወጥ ላይ የሚገኘውን የኮሮናን ሥርጭት ለመከላከል ይጠቅማል።በርሳቸው አስተያየት  ብዙ ሰዎች በአንዴ በመከተብ፣ ክትባቱ ራሱን ለመቋቋም ሌላ ዘዴ ሳይፈጥር ለመቅደም ይረዳል።ሌላው ትልቁ ተስፋ ደግሞ የአውሮጳ ኅብረት ሞደርና የተባለው ኩባንያ ያመረተውን ሌላ ክትባት ሊጸድቅ እየተቃረበ መሆኑ ነው።የሞደርና ጥቅሙ የባዮንቴክ ክትባት ከሚያስፈልገው የቅዝቃዜ መጠን ባነሰ ማቀዝቀዣ መቆየት መቻሉ ነው።

England  Biontech/Pfizer-Impfstoff
ምስል Danny Lawson/empics/picture alliance
Mexiko Coronavirus Testlauf für Impfungen
ምስል Claudio Cruz/APF/Getty Images
Impfstart in Europa - Italien
ምስል Massimo Pinca/REUTERS
Coronavirus - Argentinien - Impfungen
ምስል telam/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ