1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኮሮና ተሕዋሲ ሥጋት ያቀዛቀዘው የአፍሪካ ኤኮኖሚ

ቅዳሜ፣ የካቲት 28 2012

ግዙፍ ማሽኖች፤ አልባሳት እና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ጨምሮ በርካታ ሸቀጦች ከቻይና የሚሸመቱ እንደ ናይጄሪያ፤ ዚምባብዌ እና ዩጋንዳ የመሳሰሉ አገሮች በኮሮና ተሕዋሲ ሥጋት ሳቢያ በገበያዎቻቸው እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ እየገጠማቸው ነው። የተሕዋሲው ወረርሽኝ አንጎላ ለቻይና የምትሸጠው ነዳጅ ፍላጎት ላይም ጫና አሳድሯል።

https://p.dw.com/p/3YzeP
Nigeria Coronavirus
ምስል picture-alliance/dpa/S. Alamba

የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ከቻይና ይልቅ አፍሪካ የኮሮናን ዘላቂ ጣጣ መቋቋም አትችልም የሚል ሥጋት አላቸው

ቀስ በቀስ የኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽኝ ሥጋት በአፍሪካ እያደገ ነው። የአፍሪካ አገሮች ምጣኔ-ሐብት የዛኑ ያክል መዋዠቅ ገጥሞታል። በቅጡ ያልተጠናው የኮሮና ተኅዋሲ ከሰሐራ በረሐ በታች በሚገኙ አገሮች ምጣኔ-ሐብት ላይ ምን ያክል ጉዳት ሊያሳድር እንደሚል የሚያውቅ ማንም የለም። 

ከቻይና የምግብ ግብዓቶች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና አልባሳት የመሳሰሉ ሸቀጦች ለአገሮቻቸው ገበያ የሚሸምቱ አነስተኛ ኩባንያዎች የቀውሱ ጫና እየተሰማቸው ነው።
የሩቅ ምሥራቅ ሃገራት ኩባንያዎች ሥራቸው ተስተጓጉሎ ምርት ካቆሙ ወይም ወደ ቻይና በሚጓዙ አፍሪካውያን ላይ የጉዞ ገደብ ከተጣለ ከሰሐራ በረሐ በታች የሚገኙ አገራት ሸማቾች ፈተና ውስጥ ይወድቃሉ። የአፍሪካ ምርቶችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ላኪዎችም የኮሮና ተኅዋሲ ሥጋት አልቀረላቸውም። ቻይና ድፍድፍ ነዳጅ እና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች ከአፍሪካ በመሸመት ትልቅ የግብይት አጋር ነች። 

እንደ ናይጄሪያ በቻይና ላይ ጥገኛ የሆነ ማን ነው? 

የናይጄሪያ ባለሥልጣናት በአገሪቱ የመጀመሪያው የኮሮና ተኅዋሲ ታማሚ ሳይሆን አይቀርም ከተባለ ጣልያናዊ ተገናኝተዋል ያሏቸውን 100 ገደማ ዜጎች በእግር በፈረስ እያፈላለጉ ማግኘታቸውን የጤና ኮሚሽነር አኪን አባዮሚ አረጋግጠዋል። የላፋርጌ አፍሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ (Lafarge Africa PLC) የሽያጭ ሠራተኛ ናቸው የተባሉት ጣልያናዊ በአውሮፕላን ከሚላን ወደ ሌጎስ የተጓዙት የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር። ጣልያናዊው በሌጎስ ከተማ ያባ በተባለ አካባቢ በሚገኝ ሆስፒታል ሕክምና ላይ ሲሆኑ ከሰውየው የተገናኙ ሌሎች 39 ናይጄሪያውያንም በተመሳሳይ ሆስፒታል ክትትል ላይ ናቸው።

ፋብሪካው የስሚንቶ ምርቱ አለመቋረጡን ቢያስታውቅም የወባ፣ ኩፍኝ እና የኢቦላ ወርሽኞች ያደቀቁት የጤና አገልግሎት ሥርዓት ባለበት ግዛት የኮሮና ተኅዋሲ በአሳሳቢ ፍጥነት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ሥጋት አለ። ከዚህ ባሻገር የተኅዋሲውን ሥርጭት ሊያባብስ የሚችል ሌላ ጉዳይ አለ። ናይጄሪያ በተለይ ከቻይና ጋር ያላት የግንድ ግንኙነት እጅግ ጥብቅ ነው።

Nigeria Geld Geldscheine Naira in Lagos
በርካቶች በኮሮና ሥጋት ሳቢያ መገበያያ ገንዘቦች በእጃቸው መንካት አይሹምምስል Getty Images

በሰሜናዊ ናይጄሪያ ካዱና ከተማ የሚገኘው የነጋዴዎች ማኅበር ቃል አቀባይ አልሐጂ መሐመድ ዳን አውታ እንደሚሉት በአፍሪካ እንደ ናይጄሪያ የቻይናን ሸቀጥ የሚሸምት የለም። አልሐጂ መሐመድ ዳን አውታ «የቻይና ሸቀጦች ብዙውን ጊዜ በሁሉም የናይጄሪያ አካባቢዎች ይገኛሉ» ይላሉ።  የውጭ ጉዳይ ምንዛሪ ቢሮ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ባለፉት ጥቂት ቀናት ኪሳራ ገጥሞታል። «ማንም ወደ ቻይና መጓዝ ስለማይሻ ሰዎች ወደ የውጭ ምንዛሪ ቢሮ እየመጡ አይደለም። ብዙዎች ተኅዋሲው እንዳይዛቸው ስለሚሰጉ የመገበያያ ገንዘቦች እንኳ በእጃቸው መንካት ይጠየፋሉ» ብሏል ቢሮው።
በርካታ የግዛቲቱ ነጋዴዎች ወደ ውጭ አገራት የሚያጉዝ የንግድ ዕቅዳቸውን ሰርዘዋል። የኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ናይጄሪያ ከቻይና የምትሸምተው ሸቀጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ድንገተኛ የሸቀጦች እጥረትም መከሰቱ አልቀረም።

ለቻይና አማራጭ የሚሹት ዩጋንዳ፣ ሞዛምቢክና ኒጀር

በዩጋንዳ ያለው ነባራዊ ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ዩጋንዳ ከውጭ ከምትሸምተው አንድ አራተኛው ከወደ ቻይና ነው። በርካታ የቻይና ፋብሪካዎች ምርት በማቆማቸው ሳቢያ የሸቀጦች አቅርቦት ለሳምንታት ተስተጓጉሏል። ጨርቃ ጨርቅ፣ የኤሌክትሮኒክስ ወይም የቤት ዕቃዎች የሚቸረችሩ አነስተኛ ነጋዴዎች ችግር ውስጥ ወድቀዋል። 

የካምፓላው ነጋዴ ኦማር ካይራ ከቻይና የሚጫኑ በርካታ ሸቀጦች በዩጋንዳ ጠፍተዋል ሲሉ ያማርራሉ። ሌሎች አማራጮችም የሉም። «ሕንዳውያን አስመጪዎች አሉ። ነገር ግን እኔ የምሸጣቸው ምርቶች የሏቸውም። በአሁኑ ወቅት ቻይናውያኑን በሌላ አማራጭ መተካት ፈፅሞ አይቻልም» ይላሉ ካይራ።

ሸቀጥ ወደ ዩጋንዳ በማስገባት ሥራ ላይ የተሰማሩት እስማኤል ክዬዩና «የምንፈልጋቸውን ሸቀጦች ከሕንድ አሊያም ከዱባይ ለመሸመት እንሞክራለን። ነገር ግን በዚያም ተመሳሳይ ችግር ይገጥመናል። ምክንያቱም የዱባይ ነጋዴዎችም ዕቃ የሚሸምቱት ከቻይና ነው» ሲሉ ያክላሉ። 

Nigeria Temperaturkontrolle am Flughafen Lagos
የኮሮና ተኅዋሲ ቁጥጥር በሌጎስ አውሮፕላን ማረፊያምስል AFP/U. Ekpei

የቻይና ሸቀጦች የሞዛምቢክ ገበያዎችንም ተቆጣጥረዋል። በርካታ ነጋዴዎች በአገራቸው ገበያ የቻይና ምርቶች እጥረት በቅርቡ ይከሰታል ብለው ይጠብቃሉ። ብራዚል እና ፖርቹጋልን ከመሳሰሉ አገሮች የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች መግዛት እችል ይሆናል» የሚሉት አልዛይራ ሲምቤ የተባሉ የማፑቶ ነጋዴ የቻይና ጉዟቸውን ከሰረዙ ከራረሙ። ለወትሮው ወይዘሮዋ በዓመት ለበርካታ ጊዜያት ወደ ቻይና እያቀኑ ጨርቃ ጨርቅ፣ የመዋቢያ ውጤቶች እና የፀጉር ደህንነት መጠበቂያዎችን ይሸምቱ ነበር። አሁን ግን ያ የሚሆን አይደለም። 
በኒጀር አንዳንድ የቻይና ሸቀጦች ከንግድ መደብሮች መጥፋት በመጀመራቸው የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የአገሪቱ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሙሳ ሲዲ መሐመድ ይናገራሉ። «በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ከገበያው እየጠፉ ነው» ሲሉም ያክላሉ። ለወትሮው ደጋግመው ወደ ቻይና የሚጓዙ በርካታ ነጋዴዎች በአገሪቱ በተጣለ ገደብ ሳቢያ የሚፈልጓቸውን ቁሳቁሶች መግዛት አልቻሉም። 

ዚምባብዌ: ምጣኔ-ሐብታዊው ቀውስ ጠና

ዚምባብዌ በገበያዋ የሸቀጥ እጥረት ታይቶባታል። «የኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ከቻይና የተወሰኑ ሸቀጦች አዝዤ ነበር። ይሁንና ያዘዝኳቸው ዕቃዎች ሐራሬ አልደረሱም። ደንበኞቻችን ደግሞ በዚህ ተቆጥተዋል።» ይላሉ ክሊፎርድ ታቼ የተባሉ የዚምባብዌ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ነጋዴ። «ይኸ መቼ መፍትሔ እንደሚያገኝ የሚያውቅ የለም።» ሲሉ ያክላሉ።

ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ከምዕራቡ ተኮራርፋ ወደ ምሥራቅ ያዘነበለችበትን ፖሊሲ ገቢራዊ ማድረግ ከጀመረችበት ከጎርጎሮሳዊው 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የዚምባብዌ ዜጎች ሸቀጥ ፍለጋ ወደ ቻይና አብዝተው ይጓዙ ነበር። አሁን ግን አብዛኞቹ ነጋዴዎች አማራጭ ፍለጋ ወደ ታንዛኒያ ለመጓዝ እያቀዱ ነው። 
ቀውስ የሚንጠው የዚምባብዌ ኤኮኖሚ በርካሽ የቻይና ሸቀጦች ላይ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ገበያ በሚያቀርበው ምርትም በቻይና ላይ ጥገኛ ነው። ዚምባብዌ 900 ሚሊዮን ዩሮ የሚገመት የብረት አፈር እና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች ወደ ቻይና ትልካለች። ቻይና ዋናዋ የዚምባብዌ የንግድ አጋር ነች። ደቡብ አፍሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ሕንድ እና ዛምቢያ ራቅ ብለው ቻይናን ይከተላሉ። ዚምባብዌ ለቻይና ጥሬ ዕቃ በመነገድ ላይ ጥገኛ ከሆኑ 21 የአፍሪካ አገሮች አንዷ ነች። 
ከአንዱ የቻይና ጥግ ከውኻን ግዛት ባለፈው ታኅሳስ የተቀሰቀሰው የኮሮና ወረርሽኝ የዚምባብዌ ምጣኔ-ሐብት የነበረውን የማገገም ተስፋ እንዳሟጠጠው የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ተናግረዋል።  
የነዳጅ ግብይት የተቀዛቀዘባት አንጎላ 

Ölbohrplattform aus Angola zu Instandsetzungsarbeiten in Walvis Bay in Namibia
አንጎላ ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘው ገቢ በአስደንጋጭ ፍጥነት ቀንሷልምስል Getty Images/AFP/G. Guercia

አንጎላም በኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽኝ ሳቢያ በቀጥታም ባይሆን ለጉዳት ተዳርጋለች። የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት እና የገንዘብ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የነዳጅ ዘይት ንግድ ጥገኛ ናቸው። በተኅዋሲው ወረርሽኝ ሳቢያ ከቻይና የነበረው ንግድ በመቀዛቀዙ ቀድሞም መንገታገት ለበረታበት የአንጎላ ምጣኔ-ሐብት ሌላ ራስ ምታት መሆኑን ፕሬሲዮሶ ዶሚንጎስ የተባሉ የአገሪቱ የኤኮኖሚ ባለሙያ ይናገራሉ። ባለሙያው «ቻይና የአንጎላን ነዳጅ የምትሸምት ዋንኛዋ አገር በመሆኗ የኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽን በዋጋው ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው። የነዳጅ ዋጋ መጨመር የምርት መጠኑን ለመጨመር እና የመዋዕለ ንዋይ ሥራዎችን ለማሳደግ የመርዳቱን ያህል የዋጋው መቀነስ በአንጻሩ እንደ አንጎላ ችግር ውስጥ ለወደቀ ኤኮኖሚ መርዝ ነው» ብለዋል። 

ከቻይና ተነስቶ አሜሪካ እና አውሮጳን እያዳረሰ የሚገኘው እና በሴኔጋል፣ ናይጄሪያ ካሜሩን የተገኘው የኮሮና ተሕዋሲ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ምጣኔ-ሐብት ላይ የከፋ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ሥጋት አይሏል። እስካሁን በአውሮጳ እና በአሜሪካ የአክሲዮን ገበያዎች ዋዥቀዋል። በግብይት ማዕከላት የምግብ ግብዓቶችን ጨምሮ የሸቀጦች እጥረት እንደ አፍሪካ ሁሉ አውሮጳ እና አሜሪካም ታይቷል። መንግሥታት፤ ማዕከላዊ ባንኮች እና የገንዘብ ተቋማት ሥርጭቱ ሊያደርስ ለሚችለው ኤኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መላ ፍለጋ ላይ ናቸው።  
የምጣኔ-ሐብት ባለሙያው ፕሬሲዮሶ ዶሚንጎስ እንደ ቻይና ብርቱ ኤኮኖሚ የገነቡ አገሮች ተፅዕኖውን መቋቋም ቢችሉም አፍሪካ ላይሳካላት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። 
«የኮሮና ተኅዋሲ ወደፊት ከቻይና ይልቅ እንደ አንጎላ ላሉ አገሮች አስከፊ ነው። የቻይና ኤኮኖሚ ከአፍሪካ አገሮች በተሻለ እንዲህ አይነት ቀውሶችን መቋቋም ይችላል። የኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽኝ ከዚህ የበለጠ ሊያሳስበን ይገባል» ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። 

አንቶኒዮ ካስካይስ/እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ