1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ንግድ

የኮሮና ስጋት የፈጠረው የምግብ ዋጋ ንረት

ዓርብ፣ መጋቢት 18 2012

በድሬደዋ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የአስተዳደሩ ንግድ ፣ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በአርባ ሰባት ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ የድሬደዋ ነዋሪዎች በቅርቡ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስጋት ተከትሎ በከተማዋ በተለይ በምግብ ፍጆታዎች እና ሌሎች ሸቀጦች ላይ አግባብ ያልሆነ ጭማሪ መደረጉን ተናግረዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/3a89t
Äthiopien Dire Dawa City
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የኮሮና ቫይረስ ስጋት ያስከተለው የምግብ ዋጋ ንረት

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ የተረጋገጠውን የኮሮና ቫይረስ ስጋት ተከትሎ በአብዛኖቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች በምግብ ፍጆታ እና ሌሎች መሰረታዊ ዕቃዎች ላይ አንዳንድ ነጋዴዎች የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እየተደረጉ ይገኛል ፡፡ በድሬደዋ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የአስተዳደሩ ንግድ ፣ኢንደስትሪ እና  ኢንቨስትመንት  ቢሮ በአርባ ሰባት ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ለDW አስተያየት የሰጡ የድሬደዋ ነዋሪዎች በቅርቡ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስጋት ተከትሎ በከተማዋ በተለይ በምግብ ፍጆታዎች እና ሌሎች ሸቀጦች ላይ አግባብ ያልሆነ ጭማሪ መደረጉን ተናግረዋል ፡፡ለችግሩ መከሰት ነጋዴው እና ሸማቹ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡የአስተዳደሩ ንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ለDW በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ከዚሁ አግባብ  ያልሆነ የዋጋ ማናር ጋር በተያያዘ እስካሁን አርባ ሰባት በሚሆኑ የንግድ ሱቆች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ኃላፊው አንዳንድ ነጋዴዎች በምግብ ሸቀጦቹ አቅርቦት ላይ እጥረት መኖሩን በሚመለከት የሚያነሱትን ቅሬታ መነሻ በማድረግ በንግድ ድርጅቶቹ ማከማቻ መጋዘኖች ላይ ፍተሻ ተደርጎ እርምጃ መወሰዱን ገልፀው በቀጣይም መሰል እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ፡፡በተወሰነ መልኩ እርምጃውን ተከትሎ ለውጥ መኖሩን የተናገሩት ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ይህንን ወቅታዊ ችግር መነሻ በማድረግ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋገት መንግስት የጀመረውን እርምጃ ማጠናከር እንዲሁም የሸማቾች እና የጋራ ህብረት ስራ ማህበራትን ተሳትፎ ይበልጥ ሊጠቀም ይገባል ብለዋል ፡፡በተመሳሳይ በህሪ ክለል የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ተከትሎ የክልሉ ንግድ ፅ/ቤት በስድስት የተለያዩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን የፅ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ አብራሂም አለጋዜጠኞች ተናግረዋል ፡፡ ለምግብ ፍጆታነት የሚውሉ ሸቀጦችን በብዛት ገዝቶ የመያዝ ልምድ በሌለበት የምስራቁ ሀገሪቱ አካባቢ ዕለት ዕለት በሸቀጦች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ኑሮን አስቸጋሪ እያደረገ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

መሳይ ተክሉ

ታምራት ዲንሳ