1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቲት ሲዘከር፤ የሲኖዶሱ ውሳኔ እና የፖምፒዮ ጉብኝት

ዓርብ፣ የካቲት 13 2012

የካቲት 12 ኢትዮጵያውያን በፋሺስት ጣሊያን የተጨፈጨፉበት 83ኛው የሰማዕታት ቀን አዲስ አበባ ውስጥ ተዘክሯል፤ የኅሊና ጸሎትም ተደርጓል። በዋዜማው ደግሞ ሕወሃት የተመሰረተበት 45ኛ ዓመት በዓል በዕለተ ረቡዕ የካቲት 11 ትግራይ ውስጥ ተከብሯል።

https://p.dw.com/p/3Y4e9
Ähiopien Gedenktag Massaker Yekatit 12
ምስል DW/S. Muchie

«ነጻነት ለህዝባችን - ብልጽግና ለአገራችን!»

ሕወሃት የተመሰረተበት  45ኛ ዓመት በዓል በዕለተ ረቡዕ የካቲት 11 ትግራይ ውስጥ ሲከበር፤ በማግስቱ ደግሞ የካቲት 12 ኢትዮጵያውያን በፋሺስት ጣሊያን የተጨፈጨፉበት 83ኛው የሰማዕታት ቀን አዲስ አበባ ውስጥ ተዘክሯል፤ የኅሊና ጸሎትም ተደርጓል። የአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ግብጽን በዋናነት ባፋጠጠበት፤ ኢትዮጵያ ላይ ጫናው በበረታበት ወቅት የዩናይትድ ስቴትሱ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አዲስ አበባ ብቅ ብለው፤ ያሉትን ብለው እብስ ብለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ «የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት» መስራች ነን ያሉ ግለሰቦችን አግዷል።

Äthiopien Yekatit 12 Denkmal in Addis Abeba
ምስል DW

ወርሃ የካቲት።

ከ83 ዓመታት በፊት በ12 የአዲስ አበባ ሕዝብ በያኔው የፋሺስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል በግፍ የተጨፈጨፈበት ወቅት ነበር። የታሪክ ድርሣናት ከትበው እንዳስቀሩት ከኾነ ግራዚያኒ ላይ በተሞከረው የግድያ ጥቃት የተነሳ በተሰነዘረው የበቀል ርምጃ በዕለቱ እና በቀጣይ ቀናት በርካታ ንጹሓን ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ውስጥ በግፍ ተጨፍጭፈዋል።

አካፋ እና ዶማ ሳይቀር በተገኘው ነገር ተጨፍጭፈው የተገደሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከ30,000 እንደሚበልጡ ይነገራል። ግድያው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይቋጭ በደብረ ሊባኖስ ገዳም እና አካባቢው ላይም ፍጅት መፈጸሙ በታሪክ ሠፍሮ ይገኛል። ይኽ ዕለት በየዓመቱ ሲዘከር አንድ ክፍለ ዘመን ሊደፍን ከሩብ ክፍለ ዘመን ያነሰ ተጠግቷል።

ቢንያም ዲ ጂ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የካቲት12 በመጣ ቁጥር በፋሺሽት ጣሊያን አዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የደረሰውን እልቂት እናስታውሳለን» በማለት በእለቱ ለተሰዉ ሰማእታት «ዘልአለማዊ ክብር» ተመኝተዋል።

ፖለቲከኛው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፦ «የዛሬ 83 ዓመት ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ለነፃነታችን በከፈሉት ዋጋ ፋሺስት ግራዚያኔ የ30ሺ ኢትዮጵያዊያንን ደም በግፍ አፈሰስ- ይህ ቀን እያንዳንዱ ትውልድ የተከፈለለትን መስዋዕትነት የሚዘክርበት ቀን ነው» በማለት ትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።                                                 

የበርካቶች አስተያየት ማጠንጠኛ ሰማእታቱን በማሰብ የዘመኑ ትውልድ ለሀገሩ ጥሩ እንዲሠራ መምከሩ ላይ ነው። የመብራት መላኩ የፌስቡክ መልእክት የብዙዎችን ሐሳብ የሚጋር ነው። «ይድረስ ለኢትዮጵያ ወጣቶች» በማለት ይንደረደራል። «የካተት 12 ቀን ከ83 ዓመታት በፊት ፋሺስት ኢጣሊያን ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፈበት ዕለት ነው ይህ ቀን በቀደሙት ዓመታት የአካፋው ሚካኤል በመባል ይጠራ ነበር፡፡ ቀደምት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩልንን አገራችን ኢትዮጵያን አንድ በመሆን ክብሯን እና ሰነደቅ ዓላማዋን እንጠብቅ» ሲል ጽሑፉ ይደመደማል።

Äthiopien TPLF feiert 45 jähriges Gründungsjubiläum in Mekelle
ምስል DW/M. Haileselassie

በሰማእታት ቀን ዋዜማ በወርሃ የካቲት 11 ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የተመሰረተበትን 45ኛ ዓመት በዓል በትግራይ በተለይ በመቀሌ በስፋት አክብሯል። በእለቱ የሕወሓት ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል በትግሪኛ ያሰሙት ንግግርም በርካቶችን አነጋግሯል። ምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ «በትግራይ ላይ ያነጣጠረ» እና «ፀረ ሕዝብ» ሲሉ የገለጡትን ንግግር የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያግድ፤ ምክር ቤቱ ይሕን ካለደረገ፣ ትግራይ «ነፃ ሐገር ናት» ብሎ እንዲያዉጅ ማስጠንቀቃቸው ተሰምቷል።

ሲያው ኤን ኤ የፌስቡክ ገጻቸው መጠሪያ ነው። በአጭሩ ፦ «ለምክር ቤቱ ትእዛዝ መስጠት ቀረኮ» ሲሉ ተሳልቀዋል። ቹቹ ቦክስተር በሚል የፌስ ቡክ ስም ተጠቃሚ የቀረበው ጽሑፍ ደግሞ፦«ይኼ የነፃነትና የመገንጠል አባዜ ለስልጣን ጥመኞቹ እንጂ ለሕዝቡ ምን ጠቅሞ ነው ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት?» በማለት ይጠይቃል።

ቶም ቶም፦ «የትግራይን እጣ ፋንታ የመወሰንም ሆነ የማወጅ ኃላፊነት የሕወሓት ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ የፈለገውን ቢወስን መብቱ ነው» ብለዋል። ይርጉ ኤርሞሎ ደግሞ፦ እሳቸውም በአጭር ጽሑፋቸው፦ «ጅራፍ ራሱን ገርፎ ራሱ ይጮሀል» በማለት ጽፈዋል። የምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ «ነፃ ሐገር ናት» ንግግር ላይ የተሰጡ አስተያየቶች በአብዛኛው አንዱን ካንዱ የሚያጋጩ እና የሚያንጓጥጡ ናቸው። የፖለቲካው ትኩሳት በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ዘንድ ሲንበለበል በአስተያየቶቹ ወገግ ብሎ ይታያል። ቅራኔ የሚያጭሩትን ትተን የተወሰኑትን ነው ያቀረብንላችሁ።

Ähiopien Gedenktag Massaker Yekatit 12
ምስል DW/S. Muchie

ሌላው በሳምንቱ አነጋጋሪ የነበረው ርእሰ ጉዳይ፦ የካቲት 11 ቀን 2012 ዓም ቅዱስ ሲኖዶስ በአደረገው ምልአተ ጉባኤ «ከሕገ ወጥ ግለሰቦች ጋር» በማበር «ሕገ-ወጥ ቤተክርስቲያን» አቋቁመዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ እና እገዳ ጉዳይ ነው።  ቅዱስ ሲኖዶሱ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እናቋቁማለን በማለት የሚንቀሳቀሱ ባላቸው ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ አባ ገብረ ማርያም ነጋሳ፣ መምህር ኃይለሚካኤል ታደሰ እና ቄስ በዳሳ ቶላ ላይ ከረቡዕ የካቲት 11 ጀምሮ ከቤተ ክርስትያን የተሰጣቸው ክህነት መያዙንና በቤተ ክርስትያኒቱ ስም ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ማገዱን ዐሳውቋል።

ይኽን ጉዳይ አስመልክቶ በርካታ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው ተሰንዝረዋል። ፍቅር ያሸንፋል በሚል የፌስቡክ ስም የዶይቸ ቬለ ገጽ ላይ የቀረበ አስተያየት እንዲህ ይነበባል፦ «እኔ የምለዉ አንድን ነገር ለማግኘት ሁለት ነገር መስጠት ብልህነት ይመስለኛል፤ የኦሮሚያ ቤተክህነት ተጠሪነቷ ለፓትርያርኩ ከሆነ ቢፈቀድላቸው ምን ችግር አለዉ? በነሱ እሰጥአገባ ምእመኑ ከሚደናገር ቁጭ ብሎ መወያየቱ የተሻለ አይሆንም ወይ?» በማለት።  

አባቦራ በተባለ ስም የትዊተር ተጠቃሚ በሰጡት አስተያየት፦ «አሜሪካን ሀገር የነበረው ሲኖዶስና ኢትዮጵያ የነበረው ሲኖዶስ በተለያየ ወቅት ሲወጋገዙ የከረሙ ነበሩ። ያመጣው ውጤት ቢኖር የምእመናንን መከፋፈል ነበር። የእነቀሲስ በላይ ጉዳይም ውጤቱ ከዚህ የተለየ አይሆንም» ብለዋል።

ምሕረት መርሻ የሰጡት አጠር ያለ አስተያየት ደግሞ፦ «ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖቴ ጥቂት እኩያን በቋንቋ ካባ ተሸፍነው ስውር የፓለቲካ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ ሊያደርጉሽ አይችሉም» የሚል ነው። «የኦሮሚያ ቤተ ክህነት በኦሮምያ የማይቋቋም ከሆነ በኦሮምያ ዉስጥ ቤተ ክርስትያንም አያስፈልግም ማለት ነዉ?»  ጠያቂው ሐሰን ከድር በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው።

Äthiopien Addis Abeba | Pressekonferenz der äthiopischen orthodoxen Kirche:  Patriarch Aab Mathias
ምስል DW/S. Muche

አደባባይ የተሰኘው ሚዲያ በፌስቡክ ገጹ ባቀረበው ጽሑፍ፦ «‘ኦሮሞ በመሆኔ ተባረርኩ‘ በሚል የራሳቸውን ቡድን በማደራጀትና ‘በቅ/ሲኖዶስ የተባረከ ፈይሳ አዱኛ የተባለ ጽላት‘ አለን በሚል እንቅስቃሴ የጀመሩትና ከእስልምና እና ከፕሮቴስታንት አጋሮቻቸው ባገኙት ድጋፍ የልብ ልብ የተሰማቸው ቀሲስ ሳሙኤል አስቀድሞ የተላከላቸውን ጥያቄ ከቁብ ሳይቆጥሩ ሳይቀበሉት የቀሩ ሲሆን፤ ሁለተኛውንም ይቀበሉት አይቀበሉት እንደሆነ የሚታይ ይሆናል» ሲል ይነበባል።   

የአደባባይ ሚዲያ የፌስቡክ ጽሑፍ፦ ዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙት ቀሲስ ሳሙኤል ብርሃኑ በዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት በኩል የወጣውን የመጨረሻ ጥሪ ደብዳቤ አያይዞም ጽፏል። «ከአቶ በላይ መኮንን ጋር ያበሩት ቀሲስ ሳሙኤል ብርሃኑ ዛሬ የመጨረሻ ጥሪ ቀረበላቸው» በሚል በሰፈረው ጽሑፍ፦ ቀሲስ ሳሙኤል እስከ የካቲት 22/2012 ዓ.ም ድረስ «ራሱን ‘የኦሮሚያ ቤተ ክህነት‘ ከሚለው ቡድን ጋር ስላላቸው ግንኙነት እንዲያብራሩ» መታዘዛዘችውን ጽሑፉ ጠቅሷል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ማይክ ፖምፒዮ የኢትዮጵያ ጉብኝትም ሌላው የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የመነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ነበር። ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ በቆይታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ሀገራቸው ማድረግ ስለምትፈልገው ስምምነት ቢጠቃቅሱም ዋነኛ ጉዳያቸው ግን ግብጽ፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳንን ያወዛገበው የ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ» ጉዳይ ነው ሲሉ በርካቶች ጽፈዋል። ግድቡን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ የእንግሊዝኛ ንግግር፦ «የስምምነቱ በርካታ ነጥቦች ወደ አግባቢ ፍጻሜው እየተቃረቡ ነው» ሲሉ ይደመጥበታል።  

Symbolbild Twitter
ምስል Imago/xim.gs

በርካቶች የተቀባበሉት እና ብዙ አስተያየቶች የቀረቡበት የአቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የትዊተር ጽሑፍ «የታላቁ የሕዳሴ ግድብ»ን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ የቀረበላትን ስምምነት አለመቀበሏን ይጠቅሳል። የአቶ ዘመዴነህ እንግሊዝኛ ጽሑፍ፦ «ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ ብርቱ ጫና ብታደርግባቸውም ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ጥቅም አያስከብርም ብለው ያመኑበትን የሕዳሴ ግድብ ስምምነቱን መፈረሙን አልተቀበሉም» ይላል። ማዲ አስማረ በትዊተር ገጹ፦ «የምር እውነት ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ» ሲል ለአቶ ዘመዴነህ መልስ ሰጥቷል።

የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት በፌስ ቡክ ገጹ ስለ ውጭ ጉዳዩ ባቀረበው ጽሑፍ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ፦«የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ አጠናክሮ ስለ ማስቀጠል ከመምከራቸውም ባሻገር በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ስላለው ሁለንተናዊ ለውጥ በዝርዝር ተወያይተውበታል» ብሏል። ጽሑፉ ስለ ግድቡ ባይጠቅስም «በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ መደገፍን በተመለከተም፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የመዋዕለ-ነዋይ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱን የተግለጸ ሲሆን፣ ድጋፉን አስመልክቶ ስምምነት ላይ ተደርሷል» ሲልም ይነበባል። ጽሑፉ ዝርዝር ጉዳዮች ግን አልቀረቡበትም።

Mike Pompeo  in Äthiopien
ምስል Getty Images/A. Caballero-Reynolds

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የዩናይትድ ስቴትሱ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ማይክ ፖምፔዎ አዲስ አበባ በገቡበት እለት ከኢትዮጵያውያን ጋር ኢትዮጵያ የምትገነባውን የሕዳሴ ግድብ የተመለከተ ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚደራደረው ኮሚቴ አባላት፤ የቴክኒክ ባለሞያዎች፤ ምሑራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለ ድርሻ አካላት እና ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተዘግቧል። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ማይክ ፖምፒዮ አዲስ አበባ በገቡበት ዕለት በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ቀጣዩን በአጭሩ ጽፈዋል።

ጽሑፉ መደቡ ብሩኅ አረንጓዴ ቀለም የኾነ የኢትዮጵያ ካርታ ተያይዞበታል። እንዲህ ይነበባል። «ነጻነት ለህዝባችን - ብልጽግና ለአገራችን!» በሦስት ቋንቋዎች ነው የተጻፈው፦ በአማርኛ፤ በኦሮሚኛ እና በእንግሊዝኛ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ