1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሞ ተቃውሞ እና ሹም ሽሩ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26 2009

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲስ ካቢኔ ከኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ዘጠኝ ሥራ አስፈፃሚዎችን አካቷል። ሹም ሽሩ የኦሮሞ ተቃውሞ መልስ ይሆን? የአገሪቱን ከፍተኛ የስልጣን እርከን የተቆጣጠረው አዲስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውስ መፍታት ስለመቻሉ ግን ብዙዎች ጥያቄ አላቸው። 

https://p.dw.com/p/2SDWG
Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

የኦሮሞ ተቃውሞ እና ሹም ሽር

በርቀት ትምህርት አገልግሎት የሚታወቀው የደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርሲቲ (UNISA) ያለፈው ግንቦት ወር በዶክትሬት ማዕረግ ካስመረቃቸው ተማሪዎቹ መካከል ወርቅነህ ገበየሁ አንዱ ነበሩ። የቀድሞው የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊ ለዶክትሬት ትምህርታቸው ማሟያ በሰሩት ጥናታቸው ፖለቲካ በጸጥታ ጥበቃ ላይ ያለውን ተፅዕኖ ፈትሸዋል። በኹከትም ይሁን ሰላማዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግሮች ውስጥ ፖሊስ የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ አሊያም ለማሸበር እንደ መሳሪያ ማገልገሉን ወርቅነህ ገበየሁ መናገራቸውን የዩኒቨርሲቲው ድረ-ገፅ አስፍሯል። የምርቃታቸው ዕለት ከአማካሪ ፕሮፌሰሮቻቸው ጋር በቀይ ጋወን ተሽሞንሙነው የተነሷቸውን ፎቶ ግራፎች ያካተተው የዩኒቨሲቲው መጣጥፍ ኢትዮጵያዊው ሚኒስትር «እኔ የዩኒሳ አምባሳደር ነኝ» የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል።   
ወርቅነህ ገበየሁ የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች ከገጠመው ሁነኛ ተቃውሞ ማግሥት ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሾሟቸው መካከል አንዱ ናቸው።  በሕግ-መንግስቱ ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚነትሥልጣን የተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት መካከል በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ዘጠኙ ኦሮሞ ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹም ሽር በተንታኞች ዘንድ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት እንደ አዎንታዊ እርምጃ ቢወሰድም የይስሙላ ነው የሚል ትችት ይሰነዘርበታል። በብሪታኒያው ቬርሲክ ማፕል ክሮፍት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ተንታኟ ኤማ ጎርደን ኃይለማርያም ደሳለኝ በአዲሱ ካቢኔ ምሥረታ የኦሮሞ ተቃውሞን ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል የሚል እምነት አላቸው። 

«ሹም ሽሩ በተለይ የኦሮሞ ተቃውሞን ለመመለስ ያለመ ይመስላል። ከ30 የካቢኔ አባላት መካከል ዘጠኙ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አባላት ናቸው። ነገር ግን በካቢኔው ከተካተቱ 21 አባላት መካከል አዳዲስ አሊያም ከቀድሞ ሥልጣናቸው የተሸጋሸጉ ናቸው። ሃያ አንዱም ለገዢው ፓርቲ እጅጉን ቅርብ የነበሩ ናቸው። በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ገዢውን ፓርቲ ይደግፉ ነበር ወይም የሚደግፏቸው ፖሊሲዎች አሉ። ስለዚህ እነዚህ ግለሰቦች ከቀደመው መንግስት እና ሥራ አስፈጻሚ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ተቃዋሚዎች  ከሹም ሽሩ በኋላ ይህ መሰረታዊ ለውጥ ሳይሆን የግለሰቦች መቀያየር እንደሆነ ይተቻሉ።»

Äthiopien Addis Abeba Vereidigung Kabinett
ምስል Imago/Xinhua

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስር ዶክተሮች፤ ሁለት ፕሮፌሰሮች፤ ሁለት ዶክተሮች ኢንጂኔሮች የተካተቱበትን አዲስ ካቢኔ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አፅድቁልኝ ሲሉ ቃል በቃል የኦሮሞ ተቃውሞን አልጠቀሱም። ለወቅቱ የሕዝብ ፍላጎት እና የአገሪቱ የእድገት ደረጃ ትኩረት መስጠታቸውን እና በአዲሱ ካቢኔ አወቃቀር የመንግስትን ሥልጣን ይበልጥ የሕብረተሰባዊ ለውጥ መሳሪያ ለማድረግ ማቀዳቸውን ኃይለ ማርያም ለተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል። የፖለቲካ አቀንቃኙ ግርማ ጉተማ የኢትዮጵያ መንግስት ዘጠኝ የኦሮሞ ልሒቃንን በአዲሱ ካቢኔ በማካተት የኦሮሞ ተቃውሞ ጥያቄ ለመመለስ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም ሲል ይከራከራል። «የኦሮሞ ተቃውሞ ጥያቄ የኦሮሞ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ አባላት ቁጥር በአስፈፃሚ አካላት ውስጥ ወይም በምክር ቤቱ ውስጥ ይጨምር የሚል አልነበረም።» የሚለው ግርማ የኢትዮጵያ መንግስት ያልተጠየቀ ጥያቄ ለመመለስ ሞክሯል ሲል ይናገራል። 

በተከታታይ ተቃውሞዎች የተናጠው የኢትዮጵያ መንግሥት የገጠመውን ፈተና  በጥይት እና በኃይል ለመፍታት ሞክሯል የሚል ትችት ይቀርብበታል። የመንግሥት ባለስልጣናቱ እና መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ የተቃውሞ አራማጆች የፖለቲካውን ቀውስ ለመፍታት በሚያቀርቧቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀራረብ አይታይባቸው። ተቃዋሚዎቹ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከጥገናዊ ለውጥ የዘለለ ፋይዳ የላቸውም ሲሉ ይተቻሉ። የተቃውሞ ፖለቲካ መሪው ዶ/ር መረራ ጉዲና የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎቻቸው በገዢው ፓርቲ ሲሾሙ ተመልክተዋል። ዶ/ር መረራ አሁን የተሾሙት አዳዲስ የካቢኔ አባላት ለፖለቲካዊው ቀውስ መፍትሔ ያበጃሉ የሚል እምነት የላቸውም። ገፋ ሲልም ሹማምንቱ መንግስት ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር በወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ እጃቸው የነበረበት፤ ከወጣቶች ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ ናቸው ሲሉ ይወነጅላሉ።

በርካታ የፀጥታ ተንታኞች የኢትዮጵያ መንግሥት የገጠመውን ተቃውሞ ፈታኝ እንደሆነ ይስማማሉ። ተንታኞቹ ቀውሱ ሁነኛ መፍትሔ እንደሚያሻው በተደጋጋሚ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናትም ፈተናቸው እንዲህ በቀላል የሚሻገሩት እንዳልሆነ በሚያደርጓቸው ንግግሮች መጠቆማቸው አልቀረም። የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ጥቆማ ቢሰጡም ለውጡ እንዲህ በፍጥነት የሚመጣ አይመስልም። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው በቀሰስተኛው ፖለቲካዊ መሻሻል ረክተው የመቀመጣቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በኖርዌይ በትምህርት ላይ የሚገኘው ግርማ ጉተማ ሹማምንቱን በመቀያየር የሚመጣ ለውጥ የለም ሲል ፍርጥም ብሎ ይናገራል። 

ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተመረጡ ማግስት በዕለተ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም  ያቋቋሙትን ካቢኔ በዓመቱ አፍርሰውታል። ኢትዮጵያም ከዘመነ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ አንድ ተመልሳለች። የፌዴራል ጉዳዮች እና የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የመሩት ዶ/ር ሽፋራው ተ/ማርያም ወደ ትምህርት ሚኒስትርነት ተሸጋሽገዋል። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ የሚል ሹመት ተሰጥቷቸዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕ/ር ይፍሩ ብርሐነ፤ ባሕልና ቱሪዝም ላይ የተሾሙት ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያምን የመሳሰሉ አዳዲስ ፊቶችም ታይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከቀደሙት ሹማምንቶቻቸው የተወሰኑት ባስመዘገቡት ውጡት ተመዝነው በያዙት የመንግስት ስልጣን እንዲቀጥሉ የተቀሩት እንዲሸጋሸጉ መደረጉን ይግለጡ እንጂ መስፈርታቸውን አልገለጡም። የህግ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ሹም ሽሩ ግርታ ፈጥሮብኛል ባይ ናቸው። አቶ ሙሉጌታ ሌላ ጥያቄም አላቸው። ኃይለማርያም ከዓመት በፊት ያቋቋሙትን አፍርሰው በአዲስ ሲተኩ ምን እያሉን ነው? ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሁን የተሻሩትን ሹማምንት አምና ሲሾሟቸው «ብቁ ናቸው፤ ሕዝባዊ ወገንተኝነት እና ክህሎት አላቸው» መባሉን የሚያስታውሱት የሕግ ባለሙያው «በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ምን ስለተፈጠረ ነው እነዚህ ሰዎች እንዲቀየሩ የተደረገው?» ሲሉም ይጠይቃሉ።

Äthiopien Neubildung Kabinett
ምስል DW/Y. Gebergziabeher

የጤና ጥበቃ ሚኒሥትር ሆነው የተሾሙት ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሐነ የወረዳ ጤና ፅ/ቤት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትርነት የተሾሙት አቶ ታገሰ ጫፎ እና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶ/ር አምባቸው መኮንንም በወረዳ አመራርነት አገልግለዋል። የፖለቲካ አራማጁ ግርማ ጉተማ አሁን የተሾሙት የካቢኔ ሚኒስትሮች የሚታወቅ የትምህርት ትጋት የነበራቸው አይደሉም የሚል አስተያየት አለው።

በአዲስ አበባ ከተማ የማስፋፊያ እቅድ መነሾ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ኦሮሚያን ተሻግሮ እስከ አማራ ክልል ዘልቋል። ከዓመት በላይ በዘለቀው ተቃውሞ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሑዩማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይገልጣሉ። 

እሸቴ በቀለ 
አዜብ ታደሰ