1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካሜሩን ውዝግብ

ሐሙስ፣ ጥር 25 2009

በካሜሩን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው ሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ግዛት የሚኖረው  ሕዝብ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢ ተፅዕኖ ከፍ እያለ በሄደበት አንፃር ተቃውሞውን አጠናከረ። ይህን ተከትሎ መንግሥት በዚሁ አካባቢ በኢንተርኔት መረጃ የሚቀርብበትን አሰራር አቋርጦዋል።

https://p.dw.com/p/2Wpad
Tastatur Symbolbild
ምስል picture-alliance/empics/D. Lipinski

Kamerun Proteste - MP3-Stereo

የካሜሩን መንግሥት እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነው የሃገሪቱ አካባቢ  የሚኖረው ሕዝብ ግዛቱን ለመገንጠል ወይም ፌዴራዊ ስርዓት እንዲፈጠር ለመቀስቀሻ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ይጠቀማል በሚል ምክንያት ነው የኢንተርኔት አገልግሎትን ያገደው። ይህ ርምጃው የመገናኛውን እና የገንዘቡን ዝውውር አሰራር  አስተጓጉሎዋል። በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰራተኞች ደሞዝ መክፈል አልተቻለም። ስራቸውን ለማከናወን በኢንተርኔት የሚጠቀሙ ተቋማት መንግሥት እገዳውን እስኪያነሳ ድረስ በየቤታቸው እንዲቆዩ አዟል። ያውንዴ ፀረ መንግሥት የምትለውን  ቅስቀሳ ለማስፋፋት በማህበራዊ መገናኛ የሚጠቀሙ ሰዎችን እንደምታስር በማስታወቅ፣ በተለይ ለሙያ ማህበራት መሪዎች በአጭር የስልክ መልዕክት ማስጠንቀቂያ መላኳን ቀጥላለች፣  ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚሰሩ ጋዜጠኞችም ስለውዝግቡ መረጃ እንዳያቀርቡ መንግሥት አሳስቧል። በሰሜን ምዕራብ ካሜሩን ዋና ከተማ ባሜንዳ የኢንተርኔት ካፌ ያላቸው ለተማሪዎች እና ተመራማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡት የ34 ዓመቱ  ንጎራን ኤፍሬም የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ እሳቸው እና ሰባት ሰራተኞቻቸው ስራ እንዳጡ ገልጸዋል። ኤፍሬም እንዳሉት፣ መንግሥት አንዳችም ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልሰጠም። 
« ሁኔታው ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው። ተማሪዎች የምርምር ስራቸውን መቀጠል አልቻሉም።  ባንኮች እና የግነዘብ ዝውውር ስራን የሚያከናውኑ ፊናንስ ተቋማትም እንዲሁ ችግር አጋጥሟቸዋል። ለኅልውናቸው በኢንተርኔት ላይ ጥገኛ የሆኑ ሰዎች ስራቸውን መስራት አልቻሉም፣ በተለይ በዚሁ ዘርፍ ላይ በብዛት የተሰማሩት ወጣቶች ስራ አልባ ሆነዋል። በጣም አስከፊ ነው። »
የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች በዚሁ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አካባቢ ተቃውሞ እየተጠናከረ በመሄዱ ይህንኑ አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ መታዘዛቸውን የካሜሩን የፖስታ እና ቴሌኮምዩኒኬሽን ሚንስትር ሊባም ሊሊኬን አስታውቀዋል። 
« አንድ ሰው የሆነ መረጃ ቢልክልህ እና ይህንንም ለሌሎች እንድታካፍል ቢጠይቅህና ይህን ብታደርግ፣ በህግ ልትጠየቅ እንደምትችል እወቅ። የካሜሩን ዜጎች ይህን መደበቅ የሚችሉ ይመስላቸዋል። ግን፣ ይህን ዘርፍ በመከታተል መቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎች እንዳሉ ነው ያስታወስናቸው። ስለዚህ ቢያዙ እና ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ቢጠየቁ፣ አላወቅንም ሊሉ አይችሉም። ስለዚህ ይህ ማስጠንቀቂያ እንጂ ዛቻ አይደለም። »
በካሜሩን በወቅቱ የተፈጠረው ውዝግብ የተጀመረው በፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ስር የነበረችው ካሜሩን ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የአሁን ሰሜን ምዕራባዊ እና ደቡብ ምዕራባዊ የካሜሩን አካባቢ ሕዝብ ከዚችው ሃገር ጋር በተዋኃደበት ጊዜ ነበር። እርግጥ፣ በዚሁ ጊዜ  ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ የሃገሪቱ ሁለት  ብሔራዊ ቋንዎችም እንዲሆኑ ተወስኗል። ይሁን እንጂ፣ በሰሜን ምዕራባዊ እና ደቡብ ምዕራባዊ የካሜሩን ግዛት አስተዳደር፣ የትምህርት እና የፍትሑ ስርዓት የትልቁ የፈረንሳይኛ ተናጋሪ አካባቢ እና  ቋንቋ ተፅዕኖ አርፎበታል። ይህ ሁኔታ ቅር ያሰኘው የአካባቢው ሕዝብ ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ተቃውሞውን በአደባባይ መግለጽ ጀምሯል። ዳኞች እና መምህራን ሕጎችና መማሪያ መጻሕፍት በእንግሊዝኛ እንዲተረጎሙ ፣ እንግሊዝኛም የማስተማሪያ ቋንቋ እንደሆነ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።   በዚህ መልክ የተጀመረው ተቃውሞ ባለፉት ጊዚያት የመገንጠሉን ጥያቄ ማንሳት ከያዘ ወዲህ ውዝግቡ  እየተባባሱ ሄደዋል። የካሜሩን መንግሥትም ወታደሮች በመላክ ተቃውሞውን ለማስቆም በወሰደው የኃይል ርምጃ ቢያንስ ሶስት ተቃዋሚዎች የተገደሉበት እና ብዙዎች የታሰሩበት ድርጊት ውዝግቡን አዲስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶታል።
 

Infografik Englisch und Französisch in Kamerun ENG
Westafrika CFA-Franc BEAC
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ