1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኪነጥበብ ምሽቶች ፋይዳ

እሑድ፣ ጥር 5 2011

ለቁመተ ሥጋ ምግብ ለቁመተ ነፍስ ምንባብ የሚሉ የጥበብ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚሰጡለት ጉዳይ ቢኖር በኪነጥበብ መድረኮች መታደምን እንደሆነ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያሉ መድረኮች አሁን አሁን እየተስፋፉ እና ታዳሚዎቻቸውም እየበረከቱ መሄዳቸው ይታያል።

https://p.dw.com/p/3BQQs
Äthiopien  Addis Abeba Gedicht Vorlesung
ምስል Tobya Gitem

መዝናኛ፦የኪነጥበብ ምሽቶች ፋይዳ

በተለይም ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ ሰባት የሚደርሱ የኪነጥበብ መድረኮች የየወሩን ቀናት እና ሳምንታት ተከፋፍለው የብዙዎችን የስነጽሑፍ ብሎም የፍልስፍና ጥማት ለማርካት እየሞከሩ መሆኑ ይሰማል። ወር በገባ የመጀመሪያው ረቡዕ በዜማ የታጀቡ ግጥሞችን አካቶ የተለያዩ የኪነጥበብ ቱሩፋቶችን የሚያቋድሰው ጦቢያ የጥበብ ምሽት፤ ግጥሙ፣  መነባንቡ፣ አጫጭር ወጉ እና የሕይወት ፍልስፍናው ሲቀርብበት ሰባት ዓመት ከመንፈቅ ተቆጠሩ። ለኪነጥበብ መፋፋት እና መስፋፋት ይህ መድረክ ምን ያህል አስተዋፅኦ አድርጎ ይሆን? ስንቶችንስ አሳትፏል?

ምሥራቅ ተፈራ «ልግባ ወይስ አልግባ» ስልት ለጊዜያዊ ችግሯ መላቀቂያ ገንዘብ ለማግኘት ስትል አካሏን ለመቸርቸር ተገዳ ከሕሊናዋ ሙግት የገጠመች የአንዲት ወጣትን የሕይወት ፈተና ባመላከተችበት ዘለግ ያለ ግጥሟ ትታወቃለች። ወትሮ ያን ያህል ትኩረት ይሰጠው ያልነበረው የግጥም ምሽት አሁን አሁን ግን ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችን እያስተናገደ አዳራሹም እየሞላ የሚመለሱ፤ መቀመጫ ቢጠፋ መሬት የሚቀመጡ፤ ቆመን እንታደም የሚሉ መበርከታቸውን እማኝ ናት።

Äthiopien  Addis Abeba Gedicht Vorlesung
ምስል Tobya Gitem

ኪነጥበብ ማኅበረሰብን ለማነፅ ፤ የሥነፅሑፍ ሥራዎች ደግሞ አስተሳሰብን ሳይቀር ለማረቅ የሚጠቅሙ መሆናቸውን ምሁራን ይናገራሉ። ለአንባብያን እና ተደራሲያን የሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎችም ዘመኑን የሚያንፀባርቁ እንደሆኑም ይታመናል። ኅብረተሰቡ የታፈነ ሲመስለው የሚተነፍስባቸው የጥበብ ሥራዎች መጽናናትን መጀገንን ተስፋን የማፍለቅ ኃይላቸው ሌላው አቅማቸው ነው። እንዲህ ያሉ የጥበብ ቱሩፋቶች ደግሞ ቋንቋም ሆነ ድንበር አይገድባቸውም። ዘመን ዘመናትን እጅ እጅ ሳይሉ መሻገር መቻላቸውም ሌላው መገለጫቸው ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሰላም የሚሰብከው የሃይማኖት መሪ ብቻ አይደለም፤ ፖለቲከኞቹም የጥበብን መድረክ ለዚህ እንዲውል መመኘታቸውን ገጣሚ ምሥራቅ ታነሳለች። በግጥም ምሽቱ ላይም የከተማዋን ከንቲባ ጨምሮ ፖለቲከኞችም ይታደሙበት ለኅብረተሰቡም ይበጃል ያሉትን ያስተላልፉበት ጀምረዋል።

ሸዋዬ ለገሠ