1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከተሜነት መስፋፋት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 12 2015

አብዛኛው አፍሪቃዊ የገጠር ነዋሪ ነው። አሁን ግን ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እጅግ ተበራክቷል። በዚሁ ከቀጠለም በመጪዎቹ አስርት ዓመታት የአፍሪቃ ከተሞች በእስያ እንደታየው ያለ መስፋፋት እንደሚያጋጥማቸው ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/4Rayb
South Africa's 'silent revolution' as those with cash go solar as power crisis worsens
ምስል Shafiek Tassiem/Reuters

የአፍሪቃ ከተሞች

አብዛኛው አፍሪቃዊ የገጠር ነዋሪ ነው። አሁን ግን ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እጅግ ተበራክቷል። በዚሁ ከቀጠለም በመጪዎቹ አስርት ዓመታት የአፍሪቃ ከተሞች በእስያ እንደታየው ያለ መስፋፋት እንደሚያጋጥማቸው ይጠበቃል። እንዲህ ያለው የከተሞች መስፋፋት አፍሪቃ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰሜን አሜሪካም ተመሳሳይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በተመድ መረጃዎች መሠረት በሰሜን አሜሪካ 82 በመቶው ሕዝብ የከተማ ነዋሪ ነው። አውሮጳ ውስጥ ደግሞ 74 በመቶ ደርሷል፤ አፍሪቃ ውስጥ ግን አሁንም 43 በመቶው ብቻ ነው በከተሞች የሚኖረው። መረጃዎች የሚጠቁሙት ግን ይኽ በቅርቡ እንደሚለወጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከተሞች ውስጥ የሚገኘው ነዋሪ ካለው የዓለም ህዝብ ቁጥር 55 በመቶው ነው። ሁኔታውን የሚከታተለው የመንግሥታቱ ድርጅት እንደሚለው በጎርጎሪዮሳዊው 2050 ዓም በመላው ዓለም ካለው የህዝብ ቁጥር ውስጥ ከሁለት ሦስተኛ የሚበልጠው የከተሞች ነዋሪ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ አፍሪቃ እና እስያ ውስጥ ያለው የከተሞች መስፋፋት ቀዳሚውን አስተዋጽኦ የማድረግ ሚና አለው።

ዛሬ ባለንበት ሁኔታም ድንገት 100 የከተማ ነዋሪዎች በአንድ ስፍራ ቢሰባሰቡ ከመካከላቸው ቢያንስ 13ቱ አፍሪቃውያን ይሆናሉ። በቀጣይ ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ይኽ ቁጥር በሦስት እጥፍ እንደሚጨምር ይገመታል። እንዲህ ቢባልም ግን ዛሬም በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ያለው ነባራዊ ሁኔታ የተለየ መሆኑን ልብ ይሏል። እንደ ኒዠር፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፤ እና ማላዊ ያሉት የአፍሪቃ ሃገራት አብዛኛው ዜጋቸው ዛሬም በገጠሩ ክፍል ነዋሪ ነው። በእነዚህ ሃገራት ከአምስቱ አንዱ ነው በከተሞች አካባቢ የሚኖረው። ምንም እንኳን ግዙፍ ከተሞች ቢኖሯትም 95 ሚሊየን የሚሆነው የናይጀሪያ ህዝብም ኗሪነቱ በገጠር አካባቢ ነው። ይኽም 85 ሚሊየን ዜጋዋ በገጠር ከሚኖረው ምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ሀገር ኢትዮጵያ ጋር ይቀራረባል። የናይጀሪያ የሕዝብ ብዛት ከኢትዮጵያ በእጥፍ እንደሚበልጥ ግን ይታሰብ።

ወደ ከተሞች የሚደረገው ፍልሰት ሲታይ ግን የዛሬ አስር ዓመት ያለውን የከተሞች መስፋፋት ተከትሎ በርካቶች የከተማ ነዋሪ እንደሚሆኑ ይገመታል። በዚህም የአፍሪቃ የከተማ ነዋሪ ኅብረተሰብ በጎርጎሪዮሳዊው 2050 ወደ 60 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።

Infografik Urbane Bevölkerung bis 2035 in Afrika EN

አፍሪቃ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከተሜነት በቀዳሚነት የተስፋፋባት ሀገር ደቡብ አፍሪቃ ናት። የሰሜን እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሃገራትም በቀጣይነት ሲከተሏት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራትም ወደዚያው ለመድረስ በፍጥነት ከተሜነት እየተስፋፋባቸው ነው። ምዕራብ አፍሪቃ ናይጀሪያንም ያካትታል፤ ትልቁ ከተማዋ ሌጎስ በአፍሪቃ ሰፊውን የከተማ ነዋሪ የያዘ ነው። ማዕከላዊ አፍሪቃ ውስጥ በጣም ሰፊዋ ሀገር ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ብቻዋን ከዛሬ 25 ዓመታት በኋላ 126 ሚሊየን ህዝቧ የከተማ ነዋሪ እንደሚሆን ከወዲሁ ተገምቷል።

በሌላ በኩል አፍሪቃ ውስጥ የሚታየው የከተሞች በፍጥነት መስፋፋት ለአስተዳደራዊ ቁጥጥር አመቺ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው። የከተሞች መስፋፋት አዎንታዊም አሉታዊም ጎን እንዳለው የሚገልጹ ወገኖች በተለይ ከቁጥጥር ውጪ በሚሆነው የግንባታ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት ለውጥን በማባባስ አደጋዎችን እንደሚያስከትል ይታመናል።   

በኮንጎ ትልቁ ከተማ ኪንሻሳ፣ በሳህል ኒያሚ እና ኒጃሚና፣ ወይም በኮትዴቩዋር ትልቅ ከተማ አቢጃን የሚገኙ ነዋሪዎች ጎርፍ ደጋግሞ ቤታቸውን ሳይቀር ጠራርጎ በመውሰድ ስላደረሰባቸው ከፍተኛ ውድመት የሚናገሩት ብዙ ታሪክ አለ። በብሪታንያ የውጪ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኘው የአፍሪቃ ከተሞች የምርምር መድረክ እንደሚለው ከሆነ ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት ያለው የከተሞች ነዋሪ 60 በመቶው የሚኖረው ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ተጋላጭ በሆነ የመኖሪያ አካባቢ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ