1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሞ ፓርቲዎች መግለጫና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እስር

ዓርብ፣ መስከረም 18 2011

አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ ማክሰኞ ዕለት ያወጡት የጋራ መግለጫ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከመኾን አልፎ ብርቱ ተቃውሞ አጭሯል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለእስር ተዳርገው በወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ እንደሚገኙ መዘገቡ ሌላኛው አነጋጋሪ የኾነ ነጥብ ኾኗል።

https://p.dw.com/p/35bXV
Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

አዲስ አበባን ያስጨነቀው እስርና መግለጫ

አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ነጥቦች ላይ ማክሰኞ ዕለት ያወጡት የጋራ መግለጫ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከመኾን አልፎ ብርቱ ተቃውሞ አጭሯል። ከግራም ከቀኝም የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለእስር ተዳርገው በወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ እንደሚገኙ መዘገቡ ሌላኛው አነጋጋሪ የኾነ ነጥብ ኾኗል። ሁለቱንም በስፋት ዳሰናል።

አዲስ አበባ፤ ብዙዎችን ያነጋገረው መግለጫ 

አዲስ አበባን በተመለከተ በአምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰሞኑን የተሰጠው መግለጫ በርካቶችን ያነጋግግር ያጨቃጭቅ ይዟል። ዐይ ኦፍ ኢትዮጵያ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ በእንግሊዝኛ ባሰፈረው ጽሑፉ «ከኦሮሞዎች በፊት ነዋሪዎቹ እነማን ነበሩ?» ሲል በማጠየቅ ይንደረደራል። «መልሱ እከሌ ነው ብንል እንኳ ከዛ እከሌ በፊት የነበረው ማን ነው? ከዚያስ በፊት» እያለ በመጠየቅ ይቀጥላል የትዊተር ጽሑፉ። «ዐላውቅም፤ በፕላኔታችን ማንም ቋሚ ኗሪ የሚባል የለም» የሚለው የዐይ ኦፍ ኢትዮጵያ ጽሑፍ፦ «ከአንዱ በፊት አንዱ ይኖር ነበረና» ሲል ይጠናቀቃል።

ብዙዎችን ማነጋገር የቀጠለው መግለጫ የተሰጠው ከውጭ በገቡ አራት የኦሮሞ ግንባሮች እና ቀድሞም ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ ነው። ግንባሮቹ በአጠቃላይ በጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ወደ ሀገር ገብታችሁ በሰላም መታገል ትችላላችሁ በሚለው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር የገቡ ናቸው። ከኮንግረሱ ጋር መግለጫውን የሰጡት  እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች፦ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፤ የተባበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፤ የኦሮሚያ ነጻነት አንድነት ግንባር እና የኦሮሞ ዲሞክራሲ ግንባር ናቸው።

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

የድርጅቶቹ አባባል በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በርካቶች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩ ታሪካዊ ሰነዶችን እንዲያጣቅሱ ጋብዟል። ሰነዶቹ ኦሮሞዎች አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት የነበረውን ኹኔታ ለማብራራት የሚሞክሩ አይነት ናቸው።

ደብርሀን የተሰኘው ድረ-ገጽ በትዊተር ገጹ በኩል ለንባብ ያበቃው ዘለግ ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ አዲስ አበባ ከተማ ስያሜዋ እና ባለቤትነቷ የማን እንደኾነ ባቀረበው ታሪካዊ ሰነዶች እያጣቀስ ያብራራል። የደብርሀን እንግሊዝኛ ጽሑፍ ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን በፊት የነበሩ ታሪካዊ ጽሑፎችን፤ በከርሰ-ምድር ተመራማሪዎች የተገኙ ጥንታዊ ፍርስራሾችን እና ቅርሶችን ያጣቅሳል። በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ኦሮሞዎች መኖር ከመጀመራቸው ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች ይኖሩ እንደነበርም ይተነትናል። አዲስ አበባ ትገኝበት ነበር ተብሎ በታሪክ አጥኚዎች በምትጠቀሰው «በረራ» በተሰኘችው የጠፋች ከተማ ኦሮሞዎች መኖር ከመጀመራቸው በፊት የግራኝ አህመድ ወረራ ምን ያህል ጉዳት አድርሶ እንደነበረም ይዘረዝራል።

ጥናታዊ ጽሑፎች በአዲስ አበባ

በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሐርትቪግ ብሬተርኒትስ ትብብር የተጻፈው፦ «በረራ የ15ኛው ክፍለ-ዘመን የነገሥታቱ ከተማ እና ኢትዮጵያ ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን በፊት» የተሰኘው ጽሑፍ ከደብርሀን የትዊተር ጽሑፍ ጋር እንደማጣቀሻ  ተያይዟል። የማጣቀሻ ጽሑፉ ገጽ 215 ላይ አረብ ፋቂ የተሰኘው የግራኝ አህመድ ዜና መዋል ጸሐፊ «ፉቱህ አል ሐበሻ» በተሰኘው መጽሐፉ ያሰፈረውን እንዲህ ያብራራል። «የግራኝ ዘመቻን በተመለከተ አረብ ፋቂ እንዲህ ዜና መዋዕሉን ጽፎታል። አህመድ ከበረራ በላይ እንደደረሰ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሥ ናዖድ ንብረት በነበረው እጅግ ሐብታም ቤተክርስቲያን በኩል አለፈ። የግራኝ ተከታዮችም ወርቅና ንብረቱን መዘበሩት።»

ንጉሥ ናዖድ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1494 እስከ 1508 ድረስ ኢትዮጵያን የገዙ ንጉሥ ነበሩ። ጽሑፉ በረራ በየረር ተራሮች እና ወጨጫ ጉብታዎች መካከል እንደምትገኝ ፍራ ማውሮ በተሰኘው የጥንት ማፕ ሠሪ ካርታ ላይ እንደምትገኝም ይጠቅሳል።

አገኘሁ አሰግድ በትዊተር ጽሑፉ፦ «ታሪክ ከግማሽ አይጀምርም» ብሏል። «ኦሮሞዎች ወደ ሰሜን ወደ አቢሲኒያ ግዛት መንቀሳቀስ የጀመሩት የአዳል ሱልጣን (ማለትም ግራኝ አህመድ) እና የክርስቲያን ሰለሞናዊ ስርወ-መንግሥት ባደረጉት ውጊያ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ሁለቱም ከተዳከሙ በኋላ ነው፤ ያም ኦሮሞዎች ወደ ሥፍራዎቹ እንዲዘዋወሩ መንገዱን ከፍቶላቸዋል» የሚለውን የሬኔ ዌምሊንገር ጽሑፍ አጣቅሷል።

Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምላሽ

የአምስቱ የኦሮሞ ድርጅቶች የጋራ መግለጫ በውል ባይጠቅስም «ጠላቶቻችን» ሲል አንዳንድ ቡድኖችን ይፈርጃል።  በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፎች የተቃውሞው ዋነኛ ምክንያት የኾነው ግን አዲስ አበባን በተመለከተ «ትናንትም፣ ዛሬም ወደፊትም  የኦሮሚያ አካልና የኦሮሞ ሕዝብ መኖሪያ ናት» ሲሉ ጽኑእ እምነት እንዳላቸው በመግለጫቸው ማተታቸው መኾናቸው የአስተያየት ሰጪዎቹ ሐሳብ ማጠንጠኛ ያመለክታል። መግለጫው መዲናዪቱ «በታሪክም በሕግ አግባብም የኦሮሞ ሕዝብ ናት» ይላል። ለመግለጫው ድጋፍ ከሰጡ ሰዎች መካከል ኡቡ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ ይገኝበታል።

ኡቡ ትዊተር ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «አዎን ኦሮሞዎችም ኢትዮጵያውያንም ነን» ይላል። «በጣም ቀላል ነው» ሲልም ይቀጥላል ኡቡ፦ «የእኔ ኦሮሞነት የአንተን ኢትዮጵያዊነት ሥጋት ላይ የሚጥል ከኾነ ያኔ ለአንተ ኢትዮጵያ ማለት ምን እንደኾነ ልትሠራበት ይገባልስለገባህበት ውዥንብር ላግዝህ አልችልም። ኢትዮጵያ ሁሉንም ቀለማቷን ስታሳይ ውብ ናት» ሲል ጽሑፉን አጠናቋል ኡቡ።

ባላሚ የተባለ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽሑፉ፦ «ኦሮሞዎች በአንድ ጊዜ ሁለት ጦርነቶችን» እያከናወኑ ነው ሲል ይንደረደራል። ቡድኖቹንም «ሕወሃት እና የዓጼ ፊውዳል ርዝራዦች» ሲል ይገልጣቸዋል። «ኦሮሞዎች ሕወሃትን ለማሸነፍ በተደጋጋሚ ተሰልፈዋል። በአንድነት ካምፕ ዙሪያ የተሰባሰቡ የጥንቱ የዘውድ ርዝራዦች ግን በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የበላይ ለመኾን እየሠሩ ነው» ሲል ጽፏል።

ማኅሌት በላቸው እዛው ትዊተር ላይ ቀጣዩን ጽሑፍ አስፍራለች። «5 የኦሮሞ ድርጅቶች ያወጡትን መግለጫ ተመለከትኩ። አዲስ አበባ እና ምናምን ለድርድር የማይቀርቡ ...ጠንካራ ጥያቄ የሚነሳባቸው ጉዳዮች ላይ አንደራደርም ማለት ምንድነው? በነዚህ ኦሮሞ ድርጅቶች እና በህወሀት መካከል ምን ልዩነት አለ ??» ስትል ጠይቃለች።

እንዳለ አደም፦ «አዎ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖርያ ዋና ከተማ ናት። ማንም ቀዠታም እየተነሳ የእኔ ናት የሚላት ከተማ አይደለችም ፣ መጥነን እናስብ ።» ብሏል በፌስቡክ ጽሑፉ።

«አዲስ አበባ የአዲስ አበባውያን ናት» ያለው ደግሞ አብርሃም ይስሐቅ ነው በፌስቡክ ጽሑፉ። «በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከሁለት ብሄሮች ወይንም ከዚያ በላይ የተወለዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን የአያት ቅደመ አያቶቻቸው እትብት ጭምር የተቀበረባት ዋና ከተማ ናት» ሲልም አክሏል። «አዲስ አበባ የኦሮሞ፣ የአማራ፡ የጉራጌ፣ የደቡብ ብሄሮች ተወላጅ የሆኑ፣ ወዘተ፣ ኢትዮጵያዊያንም የሚኖሩባት» ከተማ መኾኗን በመግለጥ  «በማህበረሰቦች መካከል ከአብሮነት ይልቅ መነጣጠልን፡ ከመቀራረብ ይልቅ ጥርጣሬና ቅራኔን የሚያፋፍም ፣ የጋራ መግለጫ ለማውጣት ለምን አስፈልገ የሚል ጥያቄ መጠየቅ የግድ ይላል» ብሏል።

Äthiopien - Addis Abeba - City Churchill Road
ምስል DW/Y. Geberegziabehr

የአዲስ አበባ አፈሳ

አዲስ አበባን በተመለከተ የአምስቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫ የብዙዎች መነጋገሪያ ከመኾኑ አስቀድሞ አዲስ አበባ በሌላ አስጨናቂ ጉዳይም ተይዛ ነበር። ነዋሪዎቿ በተለይም በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በገፍ የመታሰራቸው ዜና ብዙዎችን አስጨንቋል።

ሩት ሩት ቬሮኒካ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «ሰላማዊ ሰው ነው የታፈሰው። ሌላ ቀርቶ ለታክሲ ወረፋ ተሰልፎ የነበረ ሀሉ አልቀራቸውም፤ ወያኔ እንዲህ አደረገ ሠራ ቆረጠ ፈለጠ ሲሉ እንዳልነበሩ እራሳቸው ቁጥር አንድ ገዳይ ሆነዋል፤ ታይቶም አይታወቅም እንደዚ አይነት የመብት ጥሰት» ሲል ይጠናቀቃል።

ፍትኅ‏ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ በአጭሩ ያሰፈረው ጽሑፍ ደግሞ፦ «...ቦንብ ያፈነዳውን ይይዛሉ ብለን ስንጠብቅ ሺሻ ያፈነዳውን ይዘናል ይሉናል እንዴ...የጉድ ሀገር» ሲል ይነበባል።  አብርሃም ኤቢ፦ «በትልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በቢልየን የሚቆጠር የአገሪቱ ብር ተመዝብሮ የቱንም አካል ተጠያቂ ማድረግ ያልቻለ መንግስት በየትኛው የሞራል ሎጂክ ነው የአዲስአበባ ወጣቶችን የማስረው ከስርቆት ጋር ባላቸው ግንኙነት ነው ሊል የቻለው?» ሲል ጠይቋል።

ስጋት እና ጭንቀት ከዋጣቸው የማኅበራዊ መገናኛ ጽሑፎች መካከል በቀልድ የሚያዋዙም አልታጡም። ኢትዮጵያ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ የእስሩን ኹኔታ እንዲህ በቀልድ አዋዝቶ አስፍሮታል። «እየተከታተላቹ ያላችሁት ጦላይ ኤፍ ኤም 2011 ነው…ሰሞኑን ታፍሰው ከመጡ ወጣቶች መካከል «እሺ ወንድሜ አንተስ እንዴት እና መቼ ነው ወደ ሱስ የገባኸው?»

«ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ከተባለ ቀን ጀምሮ።» 

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ሸዋዬ ለገሰ