1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ጥሪ፣ ተስፋና ስጋቱ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2016

ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ በተባለው ድርጅት ውስጥ የሚሰሩት አቶ ገረሱ ቱፋ የሰሞኑን የኦሮሚያ ሁኔታ በተስፋም በስጋትም እንደሚመለከቱት ያስረዳሉ።የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና አሁን በኦሮሚያም ይሁን በመላ አገሪቱ ግጭቶች የመባባስ እንጂ የመርገብ ምልክት አላሳዩም ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4f9GA
Äthiopien Unruhen in der Zone Guji im Regionalstaat Oromia in der Stadt Guji
ምስል Private

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ጥሪ፣ ተስፋና ስጋቱ

ዘላቂ መፍትሄ

በሰላም ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ በተባለው ድርጅት ውስጥ የሚሰሩትና የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ገረሱ ቱፋ የሰሞኑን የኦሮሚያ ሁኔቴ በተስፋም በስጋትም እንደሚመለከቱት ያስረዳሉ፡፡ “ከሚዲያ እንህ ያለ ነገር ተመልክቻለሁ፡፡ በጦርነት መንገድ አያዋጣም ያሉ ሰዎች ይንን ውሳኔ መውሰዳቸው መልካም ነገር ቢሆንም ግን ደግሞ ይህ የጦርነቱ ማብቂያ የመጨረሻው ምእራፍ ነው የሚል እምነት የለኝም” ነው ያሉት፡፡

 

አቶ ገረሱ አሁንምቢሆን ጦርነት ለመላ አገሪቱም ለየትኛውም ህዝባዊ ፍላጎት እልባት አያመጣም የሚል አስተያየታቸውንም አጋርተዋል፡፡ “ሁሉንም ክልል ብታይ ኦሮሚ፣ አማራ እና ሌሎችም ክልሎች ግጭት በዚያ አከባቢ ያለውን ማህበረሰብ ክፉኛ ጎድቷል፡፡ ግጭቶቹ በተራዘሙ ቁጥር ደግሞ የሚከሰተው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎች እየከፉ ነው የሚሄዱት፡፡ ስለዚህ በቅርብም ይሁን በርቀት ይህን ጦርነት የሚያበረታቱ ሰዎች ከዚህ ብቆጠቡ ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ እንወክለዋለን፤ እንታገልለታለን ለሚሉት ማህበረሰብም የሚበጅ አይስልም” ብለዋል፡፡ ለግጭቶቹ ማብቂያ ሁሉንም የፖለቲካ አመለካከት እና ማህበረሰብ ያቀፈ ግጭቶቹም እንዳይደገሙ የሚረዳ ውይይት ማድረግ ነው ሲሉም ለግጭቶቹ ዘላቂ ያሉትን የመፍትሄ ሃሳብ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ገረሱ ቱፋ የኢኒሽዬቲቭ ፎር ቼንጅ ሃላፊ
አቶ ገረሱ ቱፋ የኢኒሽዬቲቭ ፎር ቼንጅ ሃላፊምስል privat

ሌላው አስተያየት ሰጪ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ እንደሳቸውም አስተያየት አሁን በኦሮሚያም ይሁን በመላ አገሪቱ ግጭቶች የመባባስ እንጂ የመርገብ ምልክት እንዳላሳዩ በአስተያየታቸው አመልክተዋል፡፡

መረራ ጉዲና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር
መረራ ጉዲና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ምስል Eshete Bekele Tekele/DW


“እንደሚመስለኝ እንደውም ግጭቶች እየሰፉ የሚሄዱ ይመስለኛል፡፡ ከኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች በተጨማሪ የጎረቤት አገር ኤርትራ ጉዳይም አሳሳቢ መስላል፡፡ በነዚህ ሁሉ አከባቢዎች በተለይም በሶስቱ ክልሎች መልክ መያዝ ያለባቸው ብዙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን መልክ በማስያዝ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ትልቁ ኃላፊነት ያለው መንግስት እጅ ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት ብቻውን ሰላምን ማረጋጋጥ ይችላል ወይ በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሮፌሰር መረራ ትልቁ ኃላፊነት በመንግስት እጅ ነው ብለዋል፡፡ ትልቁ የቀውስ ምንጮች መሰረታዊ የሆኑ የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች አለመነካት ነው ያሉት ፕሮፈሰር መረራ፤ በነዚህ ላይ ሁሉንም የማህበረሰብ አካላት ባካተተ መልኩ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ እልባት መስጠት ዘላቂ ሰላምን ያረጋግጣል የሚል እምነታቸውን አጋርተዋል፡፡

የመንግስት ጥሪ

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ምስል Seyoum Getu/DW

ከሰሞኑ የሰላም ጥሪን ለታጣቂዎች ያቀረቡት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሺዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም እየተመለሱ መሆኑን በአዎንታዊነት ጠቅሰው፤ መንግስት በመመለስ ላይ ያሉት የታጣቂዎቹ ቅሬታ፣ ጥያቄ እና የኑሮ ሁኔታቸው ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ ወደ ሰላም የተመለሱትን የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት አካል በማድረግ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱም ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ሚና ትልቅ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በብረት የሚፈታ ችግር አለመኖሩን በመገለጽም፤ በትጥቅ የሚታገሉዋቸውን ቁጭ ብለን እንምከር በማለት ጥሪ አስተላልፈውላቸዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ