1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

በኦሮሚያ ክልል የጸጥታው መደፍረስ እና ዳፋው

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2016

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚስተዋለው የጸጥታ አለመረጋጋት አሁንም አለመስከኑ እየተነገረ ነው። በዚህም የማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ችግር ላይ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ።

https://p.dw.com/p/4eJnB
ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ
የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ችግር የነዋሪዎቹ ስጋትነቱ ቀጥሏል። ፎቶ፤ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አካባቢምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ችግር

 

በመንግሥት ሠራዊት እና ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ ውጊያ

በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን ዋደራ ወረዳው አስተያየት ሰጪ በአከባቢያቸው ሲከፋ እንጂ ስረግቢ የማይስተዋለው የሰላም መደፍረስ እሳቸውን ጨምሮ ማኅበረሰቡን በእጅጉ እንደሚፈትን ያስረዳሉ። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት አስተያየት ሰጪ እንደውም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጸጥታ ይዞታው ውስብስብነት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው ይላሉ። «አሁን በስልክ እያወራሁ ባለሁበት ሰዓት በዚህ ወረዳችን አሁን እኔ በምገኝበት ሃምቦ-ሀሮ ቀበለ ቦኮ በሚባል ስፍራ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ነው የምሰማው። የመከላከያ ሠራዊቱ እና የታጠቁ አማጺያን መካከል ውጊያ የሚደረግብት አከባቢ ነው ይህ ስፍራ። ከባድ መሳሪያዎች ጭምር ጥቅም ላይ የሚውሉበት ውጊያ ነው የሚካሄደው። በዚህ ውስጥ ትልቁ ፈተና ለነዋሪው ነው የተረፈው። አንዱ ሌላውን በመደገፍ ከጠረጠረህ እስከ ሕይወት መስዋእትነት የሚያስከፍል እርምጃ ነው የሚከተለው። በዚህ ሁለት ሳምንት እንኳ በዚህ መልኩ የተገደሉ ሁለት ሰዎች በአካባቢዬ መኖራቸው ምሳሌ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው» ብለዋል።በኦሮሚያ ክልል የደራ ወረዳ ጥቃት

ውጊያው ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፈተና

የጉጂ ዞን ዋደራ ወረዳ ነዋሪ ይህ ለአራት ዓመታት ገደማ በአካባቢያቸው ያለማቋረጥ ቀጥሏል ያሉት አለመረጋጋትና የሰላም እጦቱ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብር በእጅጉ መፈተኑን ያስገነዝባሉ። «ማኅበረሰቡ ከገጠር ከተማ ከከተማ ወደ ገጠር መሄድ ፈተና ሆኖበታል። ወዲያ ወዲህ የሚጓዝ ሰው አትመለከትም። አሁን የመንግሥት ሠራዊት ወደ አካባቢው ገጠራማ ስፍራዎች በመውጣት ጠንካራ ውጊያ ታጣቂዎች ላይ በመክፈቱ በዚህ ጦርነት ውስጥ ሰውም የቤት እንስሳትም ይጎዳሉ። ይህ ወቅት አሁን አርሶ አደር ለበልግ እና ለቀጣይ መኸር ምርት ማሳውን የሚያለሰልስበት ወቅት ነበር። ግን አርሶ አደሩ በቀዬው ሰላም ኖሮት ይህን ማድረግ ባለመቻሉ መሥራት አልተቻለም» ይላሉ።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አካባቢ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አካባቢ ምስል Seyoum Getu/DW

በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ በአዋሳኝ የአማራ ክልል ከፀጥታ ይዞታው መደፍረስ ጋር ተያይዞ የማኅበረሰቡ ፈተና ከፍቷል ይላሉ። የሰዎች መታገት እና የንብረት ዘረፋውም አላባራም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከምዕራብ ጉጂ ዞን ከሚገኝ ቀበሌ ወደ ኮሬ ዞን መሸሻቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ

አስተያየት ሰጪው አክለውም አሁን የግብርናው ወሳኝ ወቅት ቢሆንም ለበርካቶች ይህን ማድረግ አይቻላቸውም ይላሉ። በአካባቢያቸው የተሻለ ሰላም ኖሮ በሚያመርቱ ቀበሌያት እንኳ የጸጥታ ይዞታው ያደበዘዘው የማጓጓዣ ችግሩ ምርታቸውን ከቦታ ቦታ ወስደው መሸጥን ፈታኝ እንዳደረገባቸውም አክለዋል።

ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ አስተያየታቸውን ያጋሩንም የኪረሙ ወረዳ ነዋሪ ዓመታትን እያስቆጠረ ላለው የጸጥታ መደፍረስ አሁንም እልባት አልተበጀም ባይ ናቸው። «አሁን ቅዳሜ ዕለት ከዚህ ሀሮ ከሚባል አካባቢ ከብቶች ገዝተው የሚሄዱ አርሶ አደሮች ተዘርፈዋል። በዚህ የማይዘረፍ የለም» ሲሉ አሁንም ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ እልባት አለማግኘታቸውን አስረድተዋል።ነቀምቴ የእንቅስቃሴ ዕገዳ እና የህዝቡ ምሬት

ለደፈረሰው ጸጥታ እልባት

በአካባቢው በፀጥታ ሃይሎች ስምሪት ስር ያለው የጸጥታ ይዞታው ማኅበረሰቡ መካከል በሚፈጠር እርቅ ወደ ዘለቄታዊ መረጋጋት ይመለሳል የሚል ተስፋ ቢኖርም አሁንም ድረስ አርሶ መብላትም ሆነ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ነግዶ ማትረፍ ከአቅም በላይ እንደሆነ ነው ብለዋል። ዶቼ ቬለ ስለነዋሪዎቹ አስተያየት እና በመንግሥት ስለተቀመጠው ቀጣይ የመፍትሄ ሃሳብ ለመጠየቅ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ጥረቱ አልሰመረም። ይሁንና ከሰሞኑ በተደጋጋሚ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ላይ ተከታታይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱን የሚገልጸው የአገሪቱ መከላከያ በየአካባቢዎቹ ሰላም ለማስፈን እየሠራ መሆኑን ያስረዳል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ