1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦ. ኤም. ኤን ቴሌቪዥን ይፋዊ ምረቃ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

ሐሙስ፣ ሐምሌ 12 2010

በቅርቡ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የከፈተው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ቴሌቪዥን ጣቢያን በይፋ የማስመረቅ ስነ-ስርዓት የፊታችን ሐምሌ 29 በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ዛሬ ተገልጿል። የምረቃ ስነስርዓቱን ለማስተባበር የተዋቀረው ኮሚቴ አባላት ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ የመገናኛ አውታሩ በህዝብ እንዲደገፍ ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/31m2j
Addis Ababa  - OMN TV
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

የኦ. ኤም. ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ይፋዊ ምረቃ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

በራስ ተነሳሽነት መዋቀሩ በተነገረለት ኮሚቴ ውስጥ ምሁራን፣ የፖለቲካ አቀንቃኞች እንዲሁም አባገዳዎች መካተታቸው ተነግሯል። ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የሚመሩት ኢንጂነር አየለ ደጋጋ ናቸው። የምረቃ ስነ ስርዓቱ ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ከነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ እና ትግል መታሰቢያ ጋር የተያያዘ እንዲሆን መደረጉን አቶ አየለ በጋዜጣዊ መግለጫው ተናግረዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት ሐምሌ 30 በመላው ኦሮሚያ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዶ እንደነበር ያስታወሱት የኮሚቴው ሰብሳቢ ወቅቱ ብዙ የህይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት በመሆኑ ዕለቱን ህዝቡ አስቦ እንዲውል ከምረቃው ጋር እንዲቀናጅ መደረጉን አብራርተዋል። 

በጎርጎሮሳዊው ጥር 2014 ዓ. ም. የተመሰረተው ኦ.ኤም.ኤን መንግስታዊ ያልሆነ የሚዲያ ተቋም መሆኑን የተናገሩት የጣቢያው የአዲስ አበባ ስራ አስኪያጅ አቶ ቶሌራ ፍቅሩ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ለየት የሚያደርገው “ህዝብን ያማከለ ጋዜጠኝነት መከተሉ ነው” ይላሉ። በበርካታ የኦሮሞ ምሁራን መስራችነት እንደተቋቋመ የተነገረለት ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያን አሁን በዋና ኃላፊነት የሚመሩት አቶ ጃዋር መሐመድ ናቸው። መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት አቶ ጃዋር በአዲስ አበባው የምረቃ ስነ ስርዓት እንደሚገኙ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል።

መግለጫውን የተከታተለው የአዲስ አበባው ወኪላችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ያጠናቀረውን ሙሉ ዘገባ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።    

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ