1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእናት ጡት ወተት ባንክ በዩጋንዳ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 12 2010

የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ እናት ጡት ወተት እንደሚያስፈልግ የዓለም የጤና ድርጅት ይመክራል። ምክሩ እናቶቻቸው ለሚያሳድጓቸው ሊጠቅም ብቻ ሳይሆን ሊቀልል ይችል ይሆናል። እናቶቻቸውን ላጡ ወይም ደግሞ ተወልደው ለተጣሉት እውን የሚሆንበት ዕድል አዳጋች ነው።

https://p.dw.com/p/31mQU
Symbolbild Adoption Afrika Lesbisches Paar
ምስል dapd

የጡት ወተት ለልጆች ጤና ወሳኝ ነው

Flüchtlingskind in Darfur
ምስል AP

እንዲህ ያሉት ልጆች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት እንደሚጋለጡ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። በዚህ ምክንያትም ዩጋንዳ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሀኪም ቤት እንዲህ ላሉ ሕፃናት የሚሆን የእናቶች ወተት የሚከማችበት ባንክ አቋቁሟል። በዋና ከተማዋ ካምፓላ በሚገኘው ናሳምባያ ሀኪም ቤት ውስጥ 10 ያለ ጊዜያቸው የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት እንዲህ ላሉ ልጆች ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚደረግላቸው ክፍል ውስጥ በሕይወት ለመቆየት ይታገላሉ። እዚያ የሚገኙት ነርሶች የሕፃናቱ ሕይወትበ እንጭጩ እንዳይቀጭ የማያቋርጥ ክትትል ያደርጋሉ። ዶክተር ቪክቶሪያ በየወሩ እንዲህ ያሉ ለመኖር የእናት ጡት ወተት ባስቸኳይ የሚያስፈልጋቸው 200 የሚሆኑ ጨቅላዎች ወደ ዚህ ክፍል እንደሚመጡ ያስረዳሉ። 
«የእናት ጡት ወተትን ለማግኘት ፈቃደኞቹ እንደ ኤች አይቪ፤ ሄፒታይተስ ቢ ወይም ከሌሎች ተያያዥ በሽታዎች ነፃ መሆናቸውን እንመረምራለን። ይህን ምርመራ አድርገው እናቶቹ ወተት ከለገሱ በኋላ አፍልተን እናቀዘቅዘዋለን ሌላ ተሐዋሲ እንዳይኖርበት ርግጠኛ ለመሆን። እነዚህ ልጆች የእናት ጡት ወተት ከማጣታቸው በተጨማሪ ለሌላ ተሐዋሲ ሊጋለጡ ይችላሉ።»
የዘጠኝ ወር ልጅ ያላት የቴሌቪዥን ጋዜጠኛዋ ዳማሊ እናቶች የጡት ወተት መለገሳቸውን አስመልክታ አንድ ዝግጅት ለማቅረብ ፈልጋ እንደነበር ትናገራለች። የጉዳዩን ምንነት በወጉ ሳትገነዘበው ግራ የሚያጋባ እና አፀያፊ አድርጋ አስባው እንደነበር በኋላ ግን ራሷም ለመለገስ መገፋፋቷን ታስረዳለች።  
«ታሪኩን እየሰራው ሳጋምሰው እራሴም መለገስ እንዳለብኝ ተሰማኝ። ምክንያቱም የሁለት ልጆች እናት ነኝ በዚያም ላይ አጠባለሁ፤ ልጄ ከሚያስፈልገው በላይ ነው ያለኝ ወተት። በዚያ ላይ እንዲህ ያለውን ርዳታ የሚፈልጉ እናቶች እያሉ ራስህ የማታደርገውን መስበኩም ትርጉም አልሰጥ አለኝ። 
እውነትነው እኔ ማድረግ ስችል  የሰው ህይወት ሳላድን እጅግ ግሩም ታሪክ ይዤ ወደቢሮዩ መምጣቴ ፍትሀዊ አይሆንም። እናም በየጊዜው ለመለገስ ወስኜ ገባሁበት። እናም አሁን በየቀኑ እለግሳለሁ።»
እሷ እንደምትለውም በሂደቱ የልገሳው ተጠቃሚ የሆነውን ልጅ መውደድ እና አድጎ የማየት ጉጉት አድሮባታል። ሌላዋ ለጋሽ ማውሪን ናቱኩንዳ ለዚሁ በጎ ተግባር ወደ ሀኪም ቤቱ መጥታለች፤ የጤና ምርመራዋ ውጤት እስኪታወቅ በትዕግሥት ትጠባበቃለች።
«የምርመራው ውጤት ሁሉ ከበሽታ ነፃ መሆኔን የሚያመልክት ከሆነ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፤ ምን በወጣው ይህ ሕፃን ወተት በማጣት ይሰቃይ ሌላዋ እናት ጋ እጅግ የተትረፈረፈ ወተት እያለ?»
እንዲያም ሆኖ ግን ሁሉም እናቶች አይደሉም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆኑት። ፊዮና ናሚሮ በሥጋ ለሚዛመዳት ካልሆነ በቀር ለማንም ልጅ ይህን ርዳታ ማድረግ አትፈልግም። ለእሷ ልጅም ቢሆን በተመሳሳይ የደም ዝምድና ትሻለች ለዚህም ምክንያት የምትለው አላት። 
«ከተለያየ የሕይወት አውድ የመጡ ልጆች እናቶቻቸውን  ባህርይ ይወርሳሉ፤ እኔ ለልጄ የሌላ እናት ወተት ብመግብ እሷ እንደእናት በመሆኗ ያላትን ባህርይ ሁሉ ታስተላልፋለች። በዚህ ምክንያት አልቀበለውም። ጋጠወጥ ወይም ሌባ ልትሆን ትችላለች እናም ልጄ እርሷን ወተት ሲጠባ መጥፎ ባህርይዋንም ይላመዳል።»
ዶክተር ቪክቶሪያ ለሕጻናት ከጡት ወተት የተሻለ ምንም ዓይነት ወተትም ሆነ ምግብ የለም ነው የሚሉት። ከጡት ወተቱም ሕፃኑ ከበሽታዎች የሚከላከልለትን በተፈጥሮ የተዘጋጀ ጠቃሚ ነገር እንደሚያገኝም ያስረዳሉ።
«ላም ስትወልድ የላም ወተት ይኖራል፤ ፍየልም ስትወልድ እንዲሁ ግልገሏ የፍየል ወተት ታገኛለች። ሰብአዊ ሰው ሲወልድም እንዲሁ ሕፃኑ የሰው ወተት ነው መመገብ ያለበት። ከጡት ወተቱ ለሕፃኑ ጤና የሚጠቅሙ የተለያዩ ንጥረነገሮች አሉ። በተለይ ለጨቅላ ሕጻናት ባክቴሪያዎችን የሚያጠፉላቸው ኤንዛየሞች በዚህ ወተት ውስጥ ይገኛሉ። ሌላ ወተት ስንሰጣቸው ቢታመሙ ለመዳን አይችሉም ፤አንዳንዴ የእናቲቱ የጡት ወተት በቂ ሳይሆን ሲቀር ተጨማሪ የጡት ወተት እንሰጣቸዋለን፤ ለዚህም ነው የማከማቻ ባንክ ያዘጋጀነው።»
በዚህ ጥረትም በናሳምባያ ሀኪም ቤት ውስጥ እንዲህ ያለው ክትትል ከሚደረግላቸው ሕጻናት ሞት በጣም መቀነሱ ነው የተነገረው። ለዚህም በበጎ ፈቃደኝነት ወተት የሚለግሱትን እናቶች ዶክተር ቪክቶሪያ ያመሰግናሉ። ይህ ተግባርም ዩጋንዳ ውስጥ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው። በቀጣይም የሌሎች ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ወደሌሎች አካባቢዎች ሊያስፋፉት ይፈልጋሉ።
ሸዋዬ ለገሠ/ ፍራንክ ይጋ

Afrika World Aids Tag tanzende Kinder
ምስል AP

አርያም ተክሌ