1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የእነ ኢትዮ-ቴሌኮም አጣብቂኝ 

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2011

ኢትዮ-ቴሌኮም የኢንተርኔት ግልጋሎት በመቋረጡ 204 ሚሊዮን ብር ማጣቱን በትናንትናው ዕለት አስታውቋል። የገንዘብ መጠኑ "ኔትብሎክስ" የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጧ ደርሶባታል ከሚለው ኪሳራ አኳያ እጅግ አነስተኛ ነው።

https://p.dw.com/p/3Mg1a
PK des CEO von Ethio-Telecom Frehiwot Tamiru
ምስል DW/G. Tedla

የእነ ኢትዮ-ቴሌኮም አጣብቂኝ 

ኢትዮ-ቴሌኮም ከሐምሌ 2010 እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም. ባሉት ወራት 36.3 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን ትላንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ኩባንያው እንዳለው አጠቃላይ የገቢ መጠኑ ካለፈው አመት አኳያ በሰባት በመቶ ገደማ የጨመረ ሲሆን ያልተጣራ ትርፉ ወደ 24.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ላለፉት ሶስት አመታት ሳይከፈል የቆየ 9.9 ቢሊዮን ብር ወይም 362 ሚሊዮን ዶላር እዳ መክፈሉ ከኩባንያው ስኬቶች መካከል አንዱ ተደርጎ ቀርቧል። 

አከራካሪው ጉዳይ ግን ኩባንያው የኢንተርኔት ግልጋሎት ለማቋረጥ የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እና በውሳኔው ሳቢያ አገሪቱ የምታጣው የገንዘብ መጠን ነው። በትናንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እንዳሉት በኢንተርኔት ግልጋሎት መቆራረጥ ኩባንያው 204 ሚሊዮን ብር አጥቷል። ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንተርኔት ግልጋሎትን ለማቋረጥ በወሰደው እርምጃ አገሪቱ በቀን 4.5 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች የሚለውን መረጃ አጣጥለዋል።  

ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ «ከእኛ ተቋም ባልወጣ መረጃ ኢትዮ-ቴሌኮም ኢንተርኔት በመዝጋቱ ወይም እንዲዘጋ በመደረጉ በቀን 4.5 ሚሊዮን ዶላር እያጣ ነው ብለው የዘገቡ አካላት አሉ። ስለ ተቋሙ መረጃ የሚያወጣው ተቋሙ ነው። ባለቤትነት የተሰጠው ሥልጣን ያለው ተቋሙ ነው። ከተቋሙ ባልተወሰደ መረጃ ሌሎች የሚዲያ አካላት ጨምሮ ሲያናፍሱት እንደነበረ ተመልክተናል። በድምሩ ያጣንው ወደ 204 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነው» ሲሉ ኪሳራውን አብራርተዋል። 

በተያዘው አመት ኢትዮጵያ የብሔራዊ ፈተናን ደህንነት ለማረጋገጥ የወሰደችውን እርምጃ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት የኢንተርኔት ግልጋሎትን አቋርጣለች። ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ በከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ወታደራዊ ሹማምንት ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ የአገሪቱ የኢንተርኔት ግልጋሎት ለ100 ሰዓታት ገደማ ተቋርጦ እንደነበር "ኔትብሎክስ" የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያወጣው መረጃ ይጠቁማል። በዓለም ዙሪያ የኢንተርኔትን ነፃነት እና የግልጋሎቱን አሰጣጥ የሚፈትሸው ይኸው ድርጅት ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ግልጋሎትን በማቋረጧ የደረሰባትን ኪሳራ በቀን 4.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያደርሰዋል። 

Social Media-Nutzung in Afrika
ምስል AFP/Getty Images/I. Kasamani

ወይዘሪት ፍሬሕይወት የኢንተርኔት መዘጋት ያሳደረውን ተጽዕኖ ሲያስረዱ ስሌቱ ከኩባንያው የዕለት ተለት ገቢ አኳያ ሊመዘን እንደሚገባ አስረድተዋል። የኔትብሎክስ ዳይሬክተር አልፕ ቶከር ግን ግልጋሎት በመቋረጡ የሚደርሰው ኪሳራ "ከኩባንያዎች የዕለት ተለት ገቢ አኳያ ብቻ ሊመዘን አይገባም" ባይ ናቸው። 

አልፕ ቶከር «የኢንተርኔት መዘጋት የንግድ ሥራዎችን ሲያስተጓጉል ሁለተኛ ችግር እንዳለ ትመለከታለህ። ለአንድ ጊዜ የሚደረግ እና ለጥቂት ሰዓታት የሚቆይ የግልጋሎት መቋረጥ ሥራቸው በኢንተርኔት ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥራዎችን ለኪሳራ ሲዳርግ በአንድ ጊዜ በአስር ሺሕዎች፤ በመቶ ሺሕዎች አሊያም በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች የአገልግሎት መስተጓጎል በአንድ አገር ንግድ እና ቢዝነስ ላይ ተፅዕኖው እንደሚከፋ ትገነዘባለህ። በተለይ ከሰሐራ በታች ያሉ አገራትን የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ለማስላት የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ኮምዩንኬሽን ቴክኖሎጂ ፖሊሲ (CIPESA) የተባለ የዩጋንዳ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያዘጋጀውን ልዩ ሞዴል እንጠቀማለን። ይኸ የኢንተርኔት መቋረጥ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሚያሳድረውን ምጣኔ-ሐብታዊ ተፅዕኖ ለመገምገም ያስችላል። ይኸ በአገራት በይፋ ባልተመዘገቡ ነጋዴዎች፣ እጅ በእጅ በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች፣ በኢ-መደበኛው የምጣኔ-ሐብት ዘርፍ እና በመዋዕለ-ንዋይ ላይ የሚያሳድረውን የረዥም ጊዜ ተፅዕኖ ለማጤን ያስችላል። ይኸ ደግሞ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገሮች እጅጉን ጠቃሚ ነው» ብለዋል። 

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ኢንተርኔት በመቋረጡ በደረሰው የኪሳራ መጠን ረገድ ከኔትብሎክስ ጋር ባይስማሙም ተፅዕኖው የከፋ መሆኑን ግን አልሸሸጉም። ተቋማቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ኢንተርኔት ለማቋረጥ የተገደድነው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ነው ሲሉ ለማስረዳት ሞክረዋል። 

የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥ ለኪሳራ የተዳረገችው አፍሪካዊት ሀገር ግን ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም። ቻድ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የጣለችውን ገደብ ያነሳችው በዚህ ሳምንት ነው። ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 2018 ጀምሮ ፌስቡክ እና ትዊተርን የመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች እና የመልዕክት መለዋወጫዎች ከግልጋሎት ውጪ ሆነው ቆይተዋል። "ኔትብሎክስ" በሰራው ስሌት የቻድ መንግሥት በወሰደው እርምጃ አገሪቱ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጥታለች። 

የአፍሪካ አገሮች የኢንተርኔት ግልጋሎትን በማቋረጣቸው አሊያም በመገደባቸው በዚህ አመት ብቻ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ማጣታቸው ይገመታል። እስከ ዛሬ ድረስ በዚሁ እርምጃ ሳቢያ ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰባት የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን ነች።

እንደ አልፕ ቶከር ከሆነ የኢንተርኔት ግልጋሎት መቋረጥ በአግባቡ የሚሰራ የፖስታ ወይም የስልክ አገልግሎት በሌላቸው ከሰሐራ በረሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ኪሳራው የከፋ ሊሆን ይችላል። የኢንተርኔት ግልጋሎትን በሚያቋርጡት መንግሥታት ጠባይ የተነሳ ተፅዕኖው ግን ከምጣኔ-ሐብቱ የተሻገረ ሊሆን ይችላል። "የኢንተርኔት ግልጋሎት ተቋርጦ የሰው ሕይወት ከጠፋ ወይም የምርጫ ውጤት ከተሰረቀ በምጣኔ-ሐብቱ ላይ በሚያሳድረው ተፅዕኖ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ከማሳጣቱ የከፋ ችግር ይፈጠራል" ሲሉ አልፕ ቶከር ያስጠነቅቃሉ። 

Infografik Restriktionen Internet Kosten Afrika EN

ነገሮች ለቴሌኮም ኩባንያዎች ውስብስብ የሚሆኑት ይኼኔ ነው። ምክንያቱም የኢንተርኔት ግልጋሎት እንዲቋረጥ ትዕዛዝ የሚያስተላልፉት መንግሥታት ናቸው። በአፍሪካ ግዙፉ የቴሌኮም ግልጋሎት አቅራቢ ኤምቲኤን ግሩፕ በሱዳን በተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተባብሯል ተብሎ ይወቀሳል። የኩባንያው የሱዳን ቅርንጫፍ የሚያቀርበውን የኢንተርኔት ግልጋሎት ያቋረጠው ከወታደራዊው የሽግግር ምክር ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ነበር። 

ኔትብሎክስን ጨምሮ ወደ ሀያ ገደማ የሲቪል ማኅበራት መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገውን የኤምቲኤን ኩባንያ የሱዳን ቅርንጫፍ የወሰደውን እርምጃ በመውቀስ ግልፅ ደብዳቤ ፅፈዋል። ማኅበራቱ በደብዳቤያቸው የኢንተርኔት ግልጋሎትን የሚያቋርጡ ኩባንያዎች የመረጃ ፍሰትን በመግታት እና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን በመገደብ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ በደብዳቤያቸው ወቅሰዋል። 

ኪጎዳ የተባለው አማካሪ ተቋም ኃላፊ ማይክ ዴቪስ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለወረቶች በመንግሥታት ውሳኔ የኢንተርኔት ግልጋሎት መቋረጥ ሊያሳድርባቸው የሚችለውን ጫና ልብ ሊሉ እንደሚገባ ያስጠነቅቃሉ። 
ማይክ ዴቪስ "በትርፍ እና በሥራቸው ላይ ጫና እንዳለው ሁሉ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ስም ሊያጠፋ ይችላል። የኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጥ የመንግሥታት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ስለዚህ ኩባንያዎቹ እጃቸውን ከፍ አድርገው ኃላፊነት የለብንም ሊሉ አይችሉም" ብለዋል። 

ባለፈው ወር በሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ትዕዛዝ መሠረት የኢንተርኔት ግልጋሎት ያቋረጡ ኩባንያዎች አብዱልአዚም አል-ሐሳን የተባሉ ጠበቃ በኤምቲኤን ኩባንያ ላይ ክስ ሲመሰርቱ ድንጋጤ ውስጥ ገብተው ነበር። ፍርድ ቤቱ ክሱን ተመልክቶ ጠበቃው የኢንተርኔት ግልጋሎት እንዲያገኙ ውሳኔ አስተላልፏል። በመላው ሱዳን ለአንድ ወር ከሳምንት ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎትም ዘግይቶ ተመልሷል። 

በአፍሪካ የቴሌኮም ግልጋሎት አቅራቢዎች ከመንግሥታት በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ኢንተርኔት በማቋረጣቸው ፍርድ ቤት ሲቆሙ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፈው ጥር የዚምባብዌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ ተቃውሞ ባያለበት ወቅት የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ "የኢንተርኔት ግልጋሎትን የማቋረጥ ሥልጣን የላቸውም" ሲል ውሳኔ አሳልፏል። ኢንተርኔትን ጨምሮ የዲጂታል እና የቴክኖሎጂ መብቶች እንዲከበሩ በሚሟገተው "አክሰስ ናው" በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በጥብቅና ሙያ የሚያገለግሉት ፒተር ማይክ እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ወደፊት በተደጋጋሚ ሊታዩ እንደሚችሉ እምነት አላቸው። 

ፒተር ማይክ «የቴሌኮም ኩባንያዎች የሚሰሩበት አካባቢ እየተለወጠ እንደሆነ ታዝቤያለሁ። ኩባንያዎቹ እስከ ችሎት የሚያደርሳቸው ትዕዛዝ እየደረሳቸው ነው። ፍርድ ቤቶች በበኩላቸው አገልግሎት ለማቋረጥ የሚሰጡ ትዕዛዞች ተገቢ አይደሉም፤ ኩባንያዎቹም ትዕዛዞቹን ሊያከብሩ አይገባም እያሉ ነው። ስለዚህ የቴሌኮም ኩባንያዎች ከመንግሥታት የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመመከት የሚያስችል አቅም ሊኖራቸው ይገባል። ኩባንያዎቹ ራሳቸው ክስ ከመሰረቱ ፍርድ ቤቶች ይደግፏቸዋል»ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። 

በተለያዩ አገሮች ለኢንቴርኔት አገልግሎት መቋረጥ የቴሌኮም ኩባንያዎችን እና መንግሥታትን በፍርድ ቤት የሚሞግቱ ደንበኞች ቁጥር እየጨመረ ነው። ለእንዲህ አይነት የዜጎች ግፊት እንደ አክሰስ ናው ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ሲያደርጉ ይታያል። 

ቺፖንዳ ሶሎሞን/እሸቴ በቀለ 
ተስፋለም ወልደየስ