1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስረኞች መፈታት ቀጥሏል

ሐሙስ፣ ግንቦት 23 2010

አቃቤ ሕግ ክሳቸውን ያነሳላቸው እስረኞች ፍቺ ቀጥሏል። በዛሬዉ ዕለትም ከአንድ መቶ የሚበልጡ ከኦነግ እና ከግንቦት ሰባት ንቅናቄዎች ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው እስር ቤት የቆዩ መፈታታቸውን ጠበቆቻቸው ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።  ክሳቸው መቋረጡ ቢነገርም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ያልተለቀቁ መኖራቸዉንም ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2yjQV
Symbolbild Deutschland Justiz
ምስል picture-alliance/dpa/U. Deck

«ከአንድ መዝገብ ገሚሱ እየተፈታ የሚቀሩም አሉ»

ኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ የፖለቲካ ውይይትን ለማሳፋት እስረኞችን እንደሚፈታ ከገለጸ አምስት ወራት ተቆጠሩ። በእነዚህ ጊዜ ዉስጥም ታዋቂ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ በተለያዩ ወህኒ ቤቶች የቆዩ እስረኞች እየተለቀቁ ነው። በዛሬዉ ዕለትም ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል እና የአማራ ሕዝብ ንቅናቄ የተባለ ድርጅት ለማቋቋም አሲራችኋል ተብለው በተለያዩ መዝገቦች የተከሰሱ ታሳሪዎች መለቀቃቸውን ከጠበቆቻቸው እና ከጉዳዩ ባለቤቶች ለመረዳት ተችሏል። ከተፈቱት መካከል አጋዬ አድማሱ፤ ነጋ የኔነው፤ ዘርዓያቆብ አዝመራው ይገኙበታል። የአቶ ዘርዓያቆብ ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ደንበኛቸው ማዕከላዊ በቆዩበት ወቅት የተፈጸመባቸው ስቃይ ለከባድ የጤና ችግር አጋልጧቸው እንደነበር አንስተዋል።

«የሽብር ተግባር ላይ ተሳትፈሃል በሚል ከሌሎች ዘጠን ግለሰቦች ጋር ሆነው ነው ክሱ የተመሰረበተበት፤ ማዕከላዊ ከአራት ወር በላይ በምርመራ ወቅት አሳልፏል እና፤ በተለይ በዚያ በምርመራ ወቅት በነበረበት ጊዜ በጣም ከባድ የሆነ የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞበት ነበር በኤሌክትሪክ ጭምር እንዲመረመር ተደርጎ ነበር እና ራሱን መቆጣጠር አቅቶት ይንቀጠቀጥ ነበር ለረዥም ጊዜ፤ የነርቭ ችግር ተፈጥሮበት ነበረ።»

በእንዲህ ሁኔታ ፍርድ ቤት ሲመላለሱም አቃቤ ሕግ በተጠረጠሩበት ክስ ምስክር አምጥቶ ሊያሰማ እንዳልቻለም ገልጸዋል። በ2008ዓ,ም ሐምሌ ወር ጎንደር ላይ እነኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ በተደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት መታሰራቸውን የሚናገሩት አቶ ዘርዓያቆብ አዝመራው አንድ ዓመት ከአምስት ወር ማዕከላዊ እና ቂሊንጦ ተይዘው መቆየታቸውን ያስረዳሉ። በማዕከላዊ የእስር ቆይታቸው በምርመራ ሂደት በተፈጸመባቸው ከፍተኛ ስቃይ  ለጤና እክል መዳረጋቸውንም እንዲሁ።

«ከጎንደር እንደመጣን ያው ምርመራ ጀመርን በሁለተኛው ቀን ያው ቀጥታ ዱላ ነው። ቶርች እሚባለውን እግርን ወዳላይ በመስቀል ወደታች ዘቅዝቀው በመምታት ያው በኤልክርቲክ ሾክ ሆንን፤ ከዚያ በኋላ ያው ራሴን ስቼ አልቻልኩትም ስቃዩን አንድ ወር ሆስፒታል ነው የቆየሁት። እንግዲህ የሚደርሰውን ስቃይ ይሄ ነው ብዬ ልገልጽልሽ አልችልም። ሙሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሞተበት እና የተቀበረበት ቦታ ማለት ማዕከላዊ ነው።»

Äthiopien Kaliti Gefängnis
ምስል DW/Y. Gebregziabher

በምርመራ ወቅት ተፈጸመብኝ ያሉት ስቃት ያስከተለባቸው የጤና እክል ገና ክትትል እንደሚያስፈልገው አቶ ዘርዓያዕቆብ እሳቸው ቢወጡም ገና ሌሎችም ስቃይ ላይ ናቸው ይላሉ። እስር ቤት ቀርተዋል ካሏቸው መካከል ዘመነ ጌቴ የሚባሉት በተመሳሳይ በምርመራ ወቅት በተፈጸመባቸው ድብደባ የጥርስ ጉዳት ደርሶባቸው ለከፍተኛ ህክምና እንዲሄዱ ታዝዞላቸው እርዳታውን ሳያገኙ እስር ቤት እንዳሉም ዘርዝረዋል። በርከት ላሉ ሌሎች ታሳሪዎች ጥብቅና የሚቆሙት አቶ አለልኝ ምህረቱ በበኩላቸው እሳቸው ከሚወክሏቸው እስረኞች 26ቱ ዛሬ እንደተፈቱ ገልጸውልናል።

«እኔ ከምከራከርላቸው ሰዎች መካከል የተወሰኑ ሰዎች ክሳቸው ተቋርጦ በዛሬው ዕለት ተለቀዋል። ዛሬ ክሳቸው ከተቋረጠው መካከል ደግሞ ያልተለቀቅ አሉ። የተለቀቁት አሁን 26 ሰው ነው ክሳቸው የተቋረጠው።»

ፍርድ ቤት የፍቺ ትዕዛዝ የሚያስተላልፈው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የመንግሥትን ውሳኔ መሠረት አድርጉ  የእነማንን ክስ እንዳቋረጠ ሲጽፍለት መሆኑን ያስረዱት ጠበቃ አለልኝ የአፈታታቸውን ሁኔታ በተመለከተ አክለው ሲናገሩ፤ «በፊት የነበሩት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በሁለት ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረው ነበር፤ ከሁለት ወር አልፎ አሁን አምስት ወርም እያለቀ ነው። አሁንም ድረስ ግን በአንድ መዝገብ ውስጥ በተመሳሳይ ክስ ተከሰው ክሳቸው ያልተቋረጠ፤ ለምሳሌ ከ14 ሰው አሁን አንድ ሰው ብቻ የቀረ አለ፤ ከ17 ሰው ሁለት ሰው ተነጥለው የቀሩ አሉ። እንዲህ እንዲህ ያለ በየክሱ እየተቆራረጡ ይቀራሉ። ፍርድ ቤቱም ለአንድ ሰው ብሎ ሥራ ይፈታል። እኛም ለአንድ ሰው ብለን ሥራ እንፈታለን። ለምን እንደሆነ ግን አልገባኝም። ማለት እኛ ምክንያቱንም አናውቀዉም መስፈርቱን።»

በሌላ በኩል ክሳቸው እንደተቋረጠ ተነግሮ ዛሬ ይፈታሉ ተብለው የሚጠበቁ መኖራቸውንም ሰምተናል። ከእነዚህ መካከልም በኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር አባልነት ተጠርጥረው በደረሰባቸው ጫና ወደኬንያ ቢሰደዱም ከዚያ ታግተው ወደ ሀገር ቤት ተወስደው ላለፉት 11 ዓመታት በእስር የቆዩት ኢንጂነር መስፍን አበበ አንዱ መሆናቸን ቤተሰቦቻቸው ገልጸውልናል። ወለጋ ውስጥ አርጆ አውራጃ ኖኖ ቆምባ በመንገድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ቆይተው ወደ አዲስ አበባ በሥራ እድገት መሄዳቸውን የሚናገሩት ቤተሰቦች፤ ከኬንያ ተይዘው መጥተው በቀረበባቸው የሽብርተኝነት ክስ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው እንደነበርም አመልክተዋል።   

 ሸዋዬ ለገሠ 

አርያም ተክሌ