1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢጣልያ እዳ እና የበጀት ጉድለት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2011

ሊጋ የተሰኘው የኢጣልያው ቀኝ ክንፍ ፓርቲ መሪ የኢጣልያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዮ ሳልቪኒኒ ህብረቱ ኢጣልያ ተግባራዊ እንድታደርግ የሚያስገድደው የወጪ ቅነሳ ተቃዋሚ ናቸው።በርሳቸው እምነት የወጪ ወይም የበጀት ቅነሳው ሥራ አጥነትን ያስፋፋል።የህብረቱ የበጀት ፖሊሲ ሊቀየር ይገባልም ባይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/3KByZ
EU-Finanzkommissar Pierre Moscovici
ምስል Reuters/F. Lenoir

የኢጣልያ እዳ እና የአውሮፓ ህብረት ማስጠንቀቂያ

የኢጣልያ መንግሥት ለህብረቱ ማስፈራሪያዎች እንዲህ በቀላሉ አልንበረከክም ሲል የቀየ ቢሆንም የህብረቱን ቅጣት ለማስቀረት መንቀሳቀስ ጀምሯል። ከአራት እና አምስት ዓመት በፊት በበጀት ጉድለት እና በእዳ ጫና ከአውሮጳ ህብረት ጋር የምትወዛገበው ግሪክ ነበረች።አሁን ደግሞ ተራው የኢጣልያ ሆኗል።ችግሩ የነበረ ቢሆንም ጎልቶ መውጣት የጀመረው ግን ኢጣልያ በቀኝ ክንፍ ፓርቲዎች መመራት ከጀመረች ከዛሬ አንድ ዓመት ወዲህ ነው።የአውሮጳ ህብረት እንደሚለውየኢጣልያ እዳ አሁን ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዓመታዊ ምርት 132.2 በመቶ ደርሷል።እዳዋ 2.3 ትሪልየን ዩሮ ወይም 2.6 ትሪልዮን ዶላር  ነው። ይህም ህብረቱ ለአባል ሀገራቱ ካስቀመጠው የ60 በመቶ ገደብ ከእጥፍ በላይ ነው።የህብረቱ ኮሚሽን የኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፕየር ሞሶኮቪቺ እንደሚሉት የኢጣልያ እዳ፣ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ ነው።በርሳቸው አባባል ችግሩ የሀገሪቱ እዳ መቆለሉ ብቻ አይደለም።
« ኢጣልያን በተመለከተ አሁን ችግሩ በሁለት ዘርፎች መሆኑን ነው የምንናገረው።የኢጣልያ ኤኮኖሚ  ዋነኛ ጫና የሆነው የመንግሥት እዳ ከሃገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት 131በመቶ የነበረው ወደ 132 በመቶ አድጓል።ሁለተኛው አስቸጋሪ ጉዳይ ደግሞ የበጀት ጉድለት ነው።የአውሮጳ ህብረት ባቀረበው ሃሳብ መሠረት በ0.3 በመቶ መቀነስ የነበረበት በጀት ከዚያ ይልቅ በ0.8 በመቶ ጨምሯል።ይህ በጎርጎሮሳዊው 2018 እንደነበረ አስታውሳለሁ።እንዳለመታደል ሆኖ የ2019ኝ በጀትም የባሰ እንደሚሆን ገምተን የ0.6 በመቶ ቅነሳ እንዲደረግ ጠይቀናል።የኢጣልያ ባለሥልጣናትም ባለፈው ሐምሌ ጉድለቱን ለማስተካከል ቃል ገብተዋል።በመጨረሻም በ2020 የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላዩ የሀገር ውስጥ ምርት ወደ 3.5 በመቶ ያድጋል ብለን ነው የምንገምተው።ይህም በውሉ ከተጠቀመጠው ገደብ በእጅጉ ያለፈ ነው።»
ሞሶኮቪች እንዳሉት በዚህ መነሻነት ህብረቱ በካሄደው ጥናት መሠረት ኢጣልያ የህብረቱን የእዳ መጠን መስፈርት እንዳላከበረች ደምድሟል።እዳን መሠረት ያደረገው የኢጣልያ ከመጠን ያለፈ የበጀት ጉድለትም ማስጠንቀቂያ እና ቅጣት ሊያስወስን ወደ ሚችለበት ደረጃ ተሸጋግሯል።በጉዳዩ ላይ ለመወሰንም የ28ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት ባለሥልጣናት ዛሬ እና ነገ ይነጋገራሉ። የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው ኮሚሽኑ እዳ የተጫነባቸው ሃገራት እዳቸውን ደረጃ በደረጃ እንዲቀንሱ እድል ይሰጣል።አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለኢጣልያ እንዳደረገው ወጪን የሚፈቅድበትም ጊዜ አለ ።
ሊጋ የተሰኘው የኢጣልያው ቀኝ ክንፍ ፓርቲ መሪ የኢጣልያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዮ ሳልቪኒ የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ለመንግሥታቸው ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ኢጣልያ በማንም መረዳት የማትፈልግ ሆኖም የዜጎችዋ የመስራት መብት እንዲጠበቅላት የምትሻ መሆኑን ተናግረው ነበር። 
«በየጋዜጣው የምናነበው እዳ ለማመን የሚያስቸግር ነው። አውሮጳ ደብዳቤ ይልክልሃል፣አውሮጳ ይነዘንዝሀል፣አውሮጳ ይከታተልሀል፤ የሌሎች ገንዘብ እንዲሰጠን አውሮጳን መጠየቅ አንፈልግም።የስፓኞችን የጀርመኖችን ወይም የፈረንሳዮችን ገንዘብ አንፈልግም።ከአውሮጳ መጠየቅ የምንፈልገው ክብራችንን እና የኢጣልያኖችን የመሥራት መብት ነው።የኢጣልያውያንን ገንዘብ ለኢጣልያውያን መዋል እንፈልጋለን።ማንም እዳችንን እንዲከፍልልን አንፈልግም።ሆኖም ኢጣልያኖች ካልሰሩ እዳቸው ያድጋል።ይህን ለመረዳት ሳይንቲስት አያስፈልግም።»
ሳልቪኒ ህብረቱ ኢጣልያ ተግባራዊ እንድታደርግ የሚያስገድደው የወጪ ቅነሳ ተቃዋሚ ናቸው።በርሳቸው እምነት የወጪ ወይም የበጀት ቅነሳው ሥራ አጥነትን ያስፋፋል።የህብረቱ የበጀት ፖሊሲ ሊቀየር ይገባልም ባይ ናቸው። ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ፓርቲያቸው 28 መቀመጫዎችን ያሸነፈው ሳልቪኒ ከድሉ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ውጤቱ የበጀት ፖሊሲ ለውጥን ጨምሮ ሌሎች ለህዝቡ ቃል የገቡዋቸውን ጉዳዮች ለመተግበር እንደሚረዳቸው ተናገረው ነበር።
«ከኔ ጀርባ ሊተነተን እኛን ሊያገለግል እኔንም እንደ ሊጉ ዋና ጸሀፊነቴ ሊያገለግል የሚችል የተረጋገጠ እና የተጨበጠ ውጤት አለ።ይህምም ለኢጣልያ ህዝብ ሚዛኑን ለማስተካከል፣ የአውሮፓ የበጀት ፖሊሲዎችን ለመቀየር የገባነውን ቃል ለመጠበቅ ይረዳናል።ሌሎች አውሮጳውያን በሰጡት ድምጽም በግልጽ ሥልጣን ሰጥተውናል። ወጪ የሚቀነስባት እና ሥራ አጦች የበረከቱበት አውሮጳ ተሸንፏል። አሌክሲስ ሲፕራስ በግሪክ፣አንጌላ ሜርክል፣ኢማኑዌል ማክሮ እና ቴሬሳ ሜይ ተቀባይነት አላገኙም።በመላው አውሮጳ አለመረጋጋት እና ሥራ አጥነት ተቀባይነት አላገኘም።» 
የኢጣልያ መንግሥት እንደሚለው ከ10ሩ አንዱ ኢጣልያዊ ሥራ አጥ ነው። መንግሥት ወጪውን በመጨመር ሥራ አጥነት ለመቀነስ የድሀውን የህብረተሰብ ክፍል ህይወት ለመለወጥ እንዲሁም ውረታን ለማስፋፋት እንደሚፈልግ ይናገራል።ይህ ደግሞ የአውሮጳ ህብረት እንደ ኢጣልያ ላሉ እዳ ለተቆለለባቸው ሃገራት የማይፈቅደው አሰራር መሆኑን የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ያስረዳል።ገበያው እንደሚለው ይህ ኢጣልያ አካሄድ የዩሮ ተጠቃሚ ሃገራትን ኤኮኖሚ ችግር ውስጥ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ኢጣልያን ተጣምረው የሚመሩት ቀኝ ክንፉ ሊግ እና ነባሩን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚቃወመው፤ባለ አምስት ኮከቡ ንቅናቄ ሃገራቸው ከአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ለተሰጣት ማስጠንቀቂያ በሚሰጡት መልስ ላይ እስከ ትናንት ድረስ የተለያየ አቋም ነበር የያዙት። ትናንት የሁለቱ ፓርቲዎች መሪዎች ህብረቱ ሊወስድ የሚችላቸውን እርምጃዎች ለማስቀረት በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ከኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ከተወያዩ በኋላ አስታውቀዋል።እንደ ኢጣልያም ባይሆን ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራትም አሉ።ፈረንሳይ ቤልጂግ እና ቆጵሮስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከብራሰልስ ቢነገራቸውም የሚያካሂዷቸው ማሻሻያዎች በቂ ሆነው በመገኘታቸው ብዙም ግፊት አልተደረገባቸውም።ኮሚሽኑ ለኢጣልያ ማስጠንቀቂያ በሰጠበት እለት የኢጣልያ እጣ ሊገጥማት የነበረውን ስፓኝን የመንግሥት ወጪን አስተካክላለች ሲል ከማስጠንቀቂያ እና ከቅጣቱ ሂደት በይፋ አስወጥቷታል።እናም ኢጣልያ ኮሚሽኑ ትኩረቱን በርስዋ ላይ ብቻ በማድረጉ ቅሬታዋን ማሰማቷ አልቀረም። ኢጣልያ የህብረቱን ደንቦች ባለማክበር ከቀጠለች እና ህብረቱ ማስጠንቀቂያ እና ቅጣቱን ካጸደቀ ከ3 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ቅጣት ሊጣልባት ይችላል።የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን የኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፕየር ሞሶኮቪቺ በቅጣት እንደማያምኑ ተናግረው ህግ ግን መከበር እንዳለበት አስገንዝበዋል። 
«ላለፉት 5 ዓመታት ማንንም ቀጥቼ አላውቅም።በዚህም ደስተኛ ነኝ።ምክንያቱም ማዕቀብ ለሚቀጡትም ሆነ ተግባራዊ ለምናደርጋቸው ደንቦችም ውድቀት ነው ብዬ ነው የማስበው።ሆኖም ደንቦቹን ሙሉ በሙሉ ካላከበሩ የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን እና የአውሮጳ መንግሥታት ሃላፊነታቸውን መወጣታቸው አስፈላጊ ነው።አውሮጳ የጋራ ባለቤትነት ነው።ሁሉም ሊያከብራቸው የሚገቡ ደንቦች አሉ።የምትቃወም አንድ ሃገር ብቻ ልትኖር አትችልም።ለአሁኑ የኔ ሃሳብ ውይይት ውይይት ውይይት ነው።አሁን ከኢጣልያኖች ጋር የማደርገውም ይህንኑ ነው። »
በኢጣልያ የበጀት ጉድለት እና የእዳ ጫና ላይ ላይ ብራሰልስ የሚካሄደው ውይይቱ ነገም ይቀጥላል።ኢጣልያ የተጠየቀችውን ተግባራዊ ለማድረግ ካልተስማማች ምን ይጠብቃት ይሆን? 

Rom Pressekonferenz Ministerpräsident Giuseppe Conte
ምስል Imago Images/Insidefoto
Italien Matteo Salvini in Mailand
ምስል AFP/M. Medina

ሙሉውን ዘገባ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ማዳመጥ ይችላሉ

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ