1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ምርጫ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 20 2012

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን በምህፃሩ ኢጋድ በጎርጎሮሳዊዉ 1986 በኢትዮጵያ፣ኬንያ፣ሱዳን፣ሶማሊያ ፣ጅቡቲና ዩጋንዳ የተመሰረተ ነዉ።ቆይተዉ ደግሞ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን  ነፃ ሀገር ሲሆኑ ድርጅቱን ተቀላቅለዋል።

https://p.dw.com/p/3SE8E
IGAD Logo

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ምርጫ

ኤርትራ ከ2007እስከ 2011 ዓ/ም የሶማሊያ አክራሪ ኃይሎችን ትደግፋለች በሚል ከድርጅቱ ታግዳ የቆየች ሲሆን በ2017 ደግሞ ሀገሪቱ ከድርጅቱ ራሷን አግልላለች።
ኢጋድ መሪዎቹን በዙር የሚመርጥ ሲሆን የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከወቅቱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ሙዋይ ኪባኪ በጎርጎሮሳዊዉ 2010 ዓ/ም የሊቀ/መንበርነቱን ቦታ ተረክበዉ መርተዋል።  እሳቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ  የተኳቸዉ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሊቀመንበርነት ቀጥለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ድርጅቱን በሊቀመንበርነት እየመሩት ይገኛሉ።
በ2016 የሊቀመንበርነቱን ስልጣን ሱዳን መያዟ የሚጠበቅ ቢሆንም የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉ በመሆናቸዉ የእርሳቸው መመረጥ የሞዕራባዉያንን ድጋፍ ያሳጣል ከሚል ስጋት ሳይመረጡ መቅረታቸዉ ይነገራል።
የኢጋድ የዋና ፀሀፊነትና የሊቀመንበርነት ቦታ እጩዎች ይፋ ከተደረጉ በኋላ በዓባል ሀገራቱ በመራሄ- መንግስታትና ርዕሳነ-ብሄራት ይሁንታ ካገኘ በኋላ የሚፀድቅ ነዉ።
ድርጅቱ  ባለፉት 3 አስርተ ዓመታት ይህንን ምርጫ በስምምነት ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጌዜ ወዲህ ግን ቅሬታ እየተሰማ መሆኑን የተለያዩ ዘገባዎች ያሳያሉ።በተለይ የወቅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ዐብይ አህመድ  የቀድሞዉን የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን የድርጅቱ ዋና ፀሀፊ አድርገዉ ሊሾሙ ነዉ የሚለዉ ጭምጭምታ  ከተሰማ ወዲህ ፤በአባል ሀገራቱ ቅሬታ መፍጠሩን  ዘኢስት አፍሪካን የተባለ የኬንያ ጋዜጣ በቅርቡ ዘግቧል። ሌላዉዘኔሽን የተባለዉ የኬንያ ጋዜጣ በበኩሉ በድርጅቱ በዙር የሚደረገዉ ስልጣን ተጥሷል የሚል ወቀሳ መቅረቡን  ሰሞኑን  አንድ የሶማሊያ ዲፕሎማትን ጠቅሶ ዘግቧል።በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ ጉዳዩ እዉነት ከሆነ በአባል ሀገራቱ ጥሩ ስሜት አይፈጥርም ይላሉ።

Fahnen der IGAD-Mitgliedsländer
ምስል Yohannes G/Eziabhare

የቀጠናዉን ሀገራት በማቀራረብና በመሸምገል ረገድ ዉጤታማ ስራ አልሰራም  በሚል በአለም አቀፍ ታዛቢዎች ዘንድ የሚታማዉ ኢጋድ ፤ላለፉት 10 ዓመታት ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያን በሚመለከት  ለአስቸኳይ ጉዳዮች  ከሚደረጉ ስብሰባዎች ዉጭ መደበኛ ጉባኤዉን እያካሄደ አይደለም በሚል የሚተቹ መኖራቸዉን ጋዜጦቹ ፅፈዋል።ፕሮፌሰር ካሳሁን ትችቱ ትክክል መሆኑን ጠቅሰዉ የድርጅቱን የድክመት ምክንያቶች ይዘረዝራሉ።

«በፋይናንስ ፣በሰዉ ሀይል፣በቴክኒክ፣በሎጅስቲክና በመሳሰሉት የተጠናከረበት ሁኔታ የለም።ከዚህ አልፎ ከአህጉሩና ከክፍለአህጉሩ ዉጭ ባሉ ሀይሎች እርዳታና ድጋፍ በአብዛኛዉ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነዉ።አባል ሀገሮች በአቅማቸዉ የሚገባቸዉን እያደረጉ አይደለም።ስለዚህ በእንዲህ አይነት አቋም ላይ የሚገኝ  ድርጅት  ያስቀመጣቸዉን መርሃ-ግብሮች ወደስራ ይለዉጣል ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል።»ብለዋል።
ኢጋድ በአዲስ ጉልበትና መንፈስ ለክፍለ አህጉሩ ማበርከት የሚጠበቅበትን ስራ እንዲያበረክት አባል ሀገራቱ ለሚያወጧቸዉ ህግ ተገዥ በመሆንና ለድርጅቱ በቁርጠኝነት መስራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። 
የድርጅቱ የዋና ፀሀፊነት ቦታ ከጎርጎሮሳዉያኑ 2000 ዓ/ም እስከ 2008 በሱዳኑ ዶክተር አታላ በሽር ተይዞ የቆየ ሲሆን ከ2008 ጀምሮ ደግሞ በኬንያዉ ማህቡብ ማሊም ተይዞ ይገኛል።
ድርጅቱ በመጭዉ ታህሳስ መጨረሻ በኬንያ ስብሰባ የሚያካሂድ ሲሆን አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ሊቀመንበሩ ዶክተር ዐብይ አህመድ ቀጣዩን ዋና ፀሀፊ ለመሾም አባል ሀገራትን ያግባባሉ ተብሎ ይጠበቃል።በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

Äthiopien Abiy Ahmed, Premierminister
ምስል Getty Images/AFP/Y. Tadesse

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ