1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ግኝቱ ቀደምት መረጃዎችን ያፋለሱ አዳዲስ አሃዞች ይዟል

ረቡዕ፣ መጋቢት 6 2009

ኢትዮጵያውያን ስሱ ከሆኖባቸው ጉዳዮች አንዱ የአባይ ወንዝ ነገር ነው፡፡ ሶስት ኢትዮጵያውያንን ያቀፈው የተመራማሪዎች ቡድን ከዓመታት በፊት ያወጣው የምርምር ውጤት ከዚህ ቀደም ስለ አባይ የነበረ ግምታዊ ስሌትን የሚያፈርስ ነው፡፡ ይኸው ግኝት ከዚህ ቀደም ግብጽ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ዙሪያ ስምምነት ሲፈጽሙ የተመረኮዙበትን ቁጥርም ያፋልሳል፡፡

https://p.dw.com/p/2ZFdr
Nil Fluss Luftaufnahme
ምስል picture-alliance/dpa/F.May

የኢትዮጵያዉያን ተመራማሪዎች ግኝት በአባይ ዙርያ

መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን የጂኦፊዚካል ባለሙያዎች በየዓመቱ ወደ አሜሪካዊቷ ካሊፎርኒያ ይተምማሉ፡፡ በዚያ መደበኛ ስብሰባ አላቸው፡፡ ከስብሰባቸው ጎን በቡድን ቡድን ሆነው ሲጨዋወቱ ሁሌም የማይቀር አጀንዳ ይነሳል፡፡ አጀንዳው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያንን የሚያብሰለስላቸው “ለሀገራችን ምን እንስራ?” ጥያቄ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የተካሄደው  ውይይት ግን እንዲያው ባክኖ አልቀረም፡፡ 

ከውሃ ጋር የተያያዙ ጥናቶችን የሚካሄዱ ሶስት ኢትዮጵያውያን አንድ ጥናት በትብብር ለማካሄድ ወሰኑ፡፡ ጥናቱ ከኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶች ከፍተኛውን ቦታ በሚይዘው አባይ ላይ ትኩረት እንደሚያደረግ ተስማሙና ስራ ጀመሩ፡፡ ጥናቱን የማስተባበሩን ሚና ኮሎራዶ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ገብርኤል ሰናይ ወሰዱ፡፡ የአለማያ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ የሆኑት ዶ/ር ገብርኤል ሙያቸው ከእርሻ እና ውሃ ጋር በቀጥታ የሚዛመድ ሲሆን ምርምራቸው የሳተላይት መረጃዎችን መተንተን ይጨምራል፡፡ 

ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ጥናቱን ያካሄዱት ከሁለት የሌሎች ሀገር ባለሙያዎች ጋር ተጣምረው ነው፡፡  በጥናታቸው ከሳተላይት መረጃ በተጨማሪ በአባይ ወንዝ ዙሪያ ለመቶ ዓመት ገደማ የተሰበሰቡ መረጃዎችን ተጠቅመዋል፡፡ የናሙና መረጃዎችም ለጥናቱ በግብዓትነት አገለግለዋል፡፡ የእነ ዶ/ር ገብርኤል ጥናት የአባይ ወንዝን የውሃ መጠን፣ በተለያየ ሀገር ላይ ያለውን የውሃ ፍሰት እንደዚሁም ወደ ወንዙ የሚገባውን እና የሚወጣውን የሚዳስስ ነው፡፡ እነርሱ የካሄዱት ጥናት ቀደም ሲል በአባይ ዙሪያ ከተካሄዱት ምርምሮች በምን እንደሚለየው ዶ/ር ገብርኤል እንዲህ ያስረዳሉ፡፡  

Tissiat Falls, Blauer Nil, Äthiopien
ምስል CC/Mark Abel

“አባይ ላይ አውነት ነው ብዙ ጥናት ተደርጓል፡፡ ግን አንዱ የአባይም ብቻ ችግር አይደለም በተለይ አፍሪካ ላይ የመረጃ ችግር አለ፡፡ ብዙ ጥናቶች የሚደረጉት የተወሰነ መረጃ ከተወሰነ ሀገር በመውሰድ ነው፡፡ ያንን የተወሰነ መረጃ ለብዙ ቦታ ወካይ እንዲሆን እየተደረገ ካለው መረጃ በመነሳት ስለማይታወቀው እየተሰላ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ጥናቶች መጨረሻ ላይ የሚያመለክቱት ተጨማሪ መረጃ ያስፈልጋል እያሉ ነው፡፡ እኛ ይሄን ስናጠና ግን ልዩ የሚያደርገው ምንድነው የሳተላይት መረጃ አለ፡፡ ያ የሳተላይት መረጃ ሁሉንም ሀገር አንድ ዓይነት በሆነ መንገድ እና ደረጃው ባልተለያየ [መንገድ ነው]፡፡ ሳተላይት አሜሪካ የሚለካውና ኢትዮጵያ የሚለካው ደረጃው ተመሳሳይ ነው፡፡ ያ ሳተላይት መረጃ ስሙሙ የሆነ ትክክለኛ ስለሆነ ያንን በማምጣት የተሻለ ግንዛቤ ይኖረናል በሚል ነው፡፡ ልዩ የሚያደርገው የሳተላይት መረጃ ማምጣታችን ነው” ሲሉ ያብራራሉ፡፡ 

እንደ ዶ/ር ገብርኤል ሁሉ መነሻቸው ከአለማያ ዩኒቨርስቲ የሆነው ዶ/ር ዮናስ ካሳ ጥናቱን ለማካሄድ ያነሳሳቸው ሌላ ተጨማሪ ምክንያት እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ የአባይን ውሃ አጠቃቀም አስመልክቶ በግብጽ እና በሱዳን መካከል እንደ ጎርጎሮሳዊው 1959 የተፈረመው ስምምነት መሰረት ያደረገው በግብጽ አስዋን ግድብ ላይ የተለካ የውሃ መጠን እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ በነበረው ልኬት 84 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ አስዋን ግድብ ይገባል፡፡ በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ዮናስ ጥናታቸውን ለማድረግ ሲነሱ ይህን ልኬት እንደገና ለመፈተሽ እንዳሰቡ ይናገራሉ፡፡ ምክንያታቸውንም ይዘረዝራሉ፡፡ 

“ያ አካባቢ ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ብዙ ለውጦች ተካሄደውበታል፡፡ የመሬት አጠቃቀም ለውጥ አለ፡፡ የደን ምንጠራም ይሁን የከተማ መስፋፋት፣ የሰው መጨመር እና የአየር ጸባይ መቀየር አይነት ለውጦች አሉበት፡፡ በዚህ ጊዜ እንግዲህ ነገሮች እንደገና መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ቁጥሩም ተቀይሯል ወይስ አልተቀየረም የሚለው እንደገና መታየት አለበት፡፡ ይህ አንደኛው ምክንያታችን ነው” ሲሉ ዶ/ር ዮናስ ያስረዳሉ፡፡  

Karte Nil Verlauf und Renaissance-Staudamm

አዲስ መረጃ ለመጨመር እና የተለየ ግኝት ላይ ለመድረስ አልመው የተነሱት ተመራማሪዎች በእርግጥም ያሰቡት ተሳክቶላቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጥናቶች ይጠቀሱ የነበሩ ሁለት አሃዞችን ያፋለሱ አዳዲስ መረጃዎችን አግኝተዋል፡፡ የመጀመሪያው “ከነጭ አባይ የውሃ መጠን ላይ ወደ 50 በመቶው በሱዳን ረግረጋማ ቦታ ገብቶ ይቀራል” የሚለውን የቀድሞ ጥናቶች መደምደሚያ ያስቀየረ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያኑ የምርምር ውጤት መሰረት ወደ ረግረጋማው ቦታ ገብቶ በዚያው ወደ ከርሰ ምድር የሚዘልቀው የነጭ አባይ የውሃ መጠን 85 በመቶ ይደርሳል፡፡ 
ሁለተኛውና ለኢትዮጵያ ይበልጥ የሚጠቅመው የተመራማሪዎቹ ግኝት ደግሞ ዶ/ር ዮናስ ቀደም ብለው ያነሱት ወደ አስዋን ግድብ ይገባል የተባለው የውሃ መጠን ጉዳይ ነው፡፡ ግኝቱ እንደሚያትተው ወደ አስዋን የሚገባው የውሃ መጠን ቀድሞ ከሚታሰበው ከፍ ያለ እና በዓመት 97 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚደርስ ነው፡፡ ዶ/ር ገብርኤል ያብራራሉ፡፡ 

“በወንዝ የሚያልፍ ውሃ በሁለት ዓይነት ይለካል፡፡ አንዱ ዛሬ ሄደን ስንለካው የምናገኘው ቁጥር ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በተፈጥሮ የሚፈስሰው፣ ሌላ ሰው ሳይጠቀምበት የሚፈስሰው ውሃ ማለት ነው፡፡  እኛ ‘ሱዳን ወይም ሌሎች ሀገሮች ለመስኖ ባይጠቀሙበት ምን ይሆናል?’ የሚለውን 97 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው ብለናል ፡፡ ግብፅ እና ሱዳን ግን ድሮ ሲስማሙ ሰነዱ እንደሚያሳየው መጠኑ 84 [ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ] ነው ብለው ነው፡፡ ልዩነቱ 13 ቢሊዩን ሜትር ኪዩብ ነው፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? በኪሎሜትር ሲለካ 13 ኪሎ ሜትር ኪዩብ ማለት ነው፡፡ የአዲስ አበባ የቆዳ ስፋት 520 ስኩዌር ኪሎሜትር አካባቢ ነው፡፡ ያንን ሁሉ [ሸፍኖ] አዲስ አበባን በ25 ኪሎሜትር ያጠልቃታል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ስናስበው የጣና ሀይቅ 28 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው፡፡ የዚያን ግማሽ ማለት ነው” ይላሉ ዶ/ር ገብርኤል፡፡

ተመራማሪው እስካሁን በስሌት ውስጥ ሳይገባ የቀረው የውሃ መጠን ከኢትዮጵያ ሌሎች ወንዞች መጠን ጋርም ያወዳድሩታል፡፡ የኦሞ ውሃ ፍሰት ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ገብርኤል በጥናት የተደረሰበት የአባይ ውሃ መጠን የኦሞን ሶስት አራተኛው እንደሚሸፍን ይገልጻሉ፡፡ ሸበሌ እና ገናሌ ወንዞችም ቢሆኑ ከስድስት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንደማይበልጡ ያስረዳሉ፡፡ 

Assuan-Staudamm in Ägypten
ምስል imago/Harald Lange

ዶ/ር ዮናስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገነባቻቸውን ግድቦች ውሃ የመያዝ አቅም በማንጸሪያነት ይጠቅሳሉ፡፡ የግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ አቅም 14 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ የተከዜው ግድብ ደግሞ ዘጠኝ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መያዝ ይችላል ይላሉ፡፡ ሱዳን ከአባይ የምትወስደው ውሃ መጠን 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ በየዓመቱ ወደ አስዋን ሳይታወቅ ይገባ የነበረውን የውሃ መጠን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ጥቅም ላይ ከምታውለው ውሃ ጋርም ያነጻጽሩታል፡፡

“[በጎርጎሮሳዊው] 2016 የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ያወጣው ገዘባ አለ፡፡ በ2016 ኢትዮጵያ 10.5 ቢሊዩን ሜትር ኪዩብ ውሃ ተጠቅማለች፡፡ ከዚያ ውስጥ 85 በመቶ ለመስኖ ነው፡፡ ሰባት በመቶው ለቀንድ ከብቶች የሆነ ነው፡፡ ስምንት በመቶው ደግሞ ለመጠጥ እና ለኢንዱስትሪ የሚሆን ነው፡፡ እንግዲህ የአባይ ውሀ ውስጥ ጠፋ የሚባለው ውሃ 13 ቢሊዮን ነው፡፡ የኢትዮጵያን ይህን ሁሉ የውሃ ፍላጎት የሚያሟላ ነው፡፡ ከዚያም በላይ ይተርፋል” ይላሉ ዶ/ር ዮናስ፡፡  

ከአምስት ዓመት በፊት በታዋቂ የምርምር መጽሔት ላይ የወጣው ይህ የተመራማሪዎቹ ጥናት አዲስ ነገር ይዞ ቢመጣም ኢትዮጵያ ተጠቅማበት እንደው እንደማያውቁ ሁለቱ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ ዶ/ር ገብርኤልጥናታቸው በኢትዮጵያ ስላገኘው ተቀባይነት እና ፋይዳው ተከታዩን ብለዋል፡፡ 

Wirtschaft Ägypten Wasserkraftwerk Assuan-Staudamm
ምስል imago/ARCO IMAGES

“ይሄ የጥናት ወረቀት እንደታተመ ኢትዮጵያ ላሉ ጓደኞቻችን ልከንላቸው ነበር፡፡ በስራ አጋጣሚ ኢትዮጵያም ስሄድ እንደዚሁ ጓደኞቼን አግኝቼ የጥናት ወረቀቱን እንዳነበቡት [ነግረውኛል]፡፡ እንደውም ያሉት ምንድነው? ‘ለነገሩ እኮ ግብጽ ከኮታዋ በላይ እንደምትወስድ ይታወቃል፡፡ አማካሪዎች የሰሯቸው አንዳንድ ዘገባዎችም አሉ፡፡ ግን ይህ የጥናት ወረቀት ያስቀመጠው አንደኛ በትክክል ምን ያህል እንደሆነ፤ ደግሞስ እንዴት ሆኖ ይህ ትርፍ መጠን ከየትእንደመጣ ጥሩ አድርጋችሁ አስቀምጣችሁታል’ ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ እንዴት ነው የሚጠቅመው ስናስበው ለድርድር ይመስለኛል፡፡ አባይ ዓለም አቀፍ ወንዝ ስለሆነ ሀገሮች ተገናኝተው መደራደር፣ መስማማት ሲጀምሩ የመጀመሪያው ጥያቄ ‘ምን ያህል ውሃ አለ?’ የሚል ይሆናል፡፡ ውሃውን ለማስተዳደር የምንችለው የውሃውን መጠን ካወቅን በኋላ ነው፡፡ በተሳሳተ ቁጥር ለአስተዳደርም ሆነ ዕቅድ ማድረግ አይቻልም፡፡ [ጥናቱ ] ለአስተዳደርም፣ ለመደራደር እና ለስምምነት ይጠቅማል ብለን ነው የምናስበው” ይላሉ ተመራማሪው፡፡  

ተመራማሪዎቹ ጥናታቸው ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ያምናሉ፡፡ እስካሁን በጥናታቸው ዙሪያ በማንኛውም የኢትዮጵያ መንግስት መስሪያ ቤትም ሆነ ባለስልጣን ማብራሪያ አለመጠየቃቸውንም ይገልጻሉ፡፡ የኢትዮጵያውያኑ ተመራማሪዎች ተስፋ ግን አሁንም አልነጠፈም፡፡ ሀገራቸው ወደፊት በአባይ ዙሪያ ለድርድር ስትቀመጥ ከውሃ ክፍፍሉ ተገቢውን ድርሻዋን ለማግኘት ጥናታቸውን እንድትጠቀም ይመኛሉ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ