1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዊዉ የጥቂት ቀናት የጀርመን ቆይታ

ሰኞ፣ ሐምሌ 23 2010

ለጊዜ ያላቸዉ ግንዛቤ በጣም ከፍ ያለ መሆኑን ብዙ ሰዉ የሚያዉቀዉ ነዉ። በጣም ጥንቁቅ ናቸዉ። ቋንቋዋቸዉ ትንሽ አስቸጋሪ ስለሆነ በጣም ተቀራርቦ ፤ ተነጋግሮ እርስ በርስ ለመፈታተሽ እንዲህ ነዉ፤ ለማለት ቢከብድም ጊዜ ላይ ግን ጥብቅና ሰዓት አክባሪ፤ በጣም የሚገርም አይነት የጊዜ ባህል ነዉ ያላቸዉ።

https://p.dw.com/p/329Hk
Deutschland Yordanos Seifu
ምስል Privat

ወጣቱ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያ

«በጀርመን የነበረኝ ቆይታ በሁለት ትናንሽ ከተሞች ዉስጥ ብቻ በመሆኑ በአጠቃላይ ስለጀርመናዉያን መናገር ይከብዳል። ግን እኔ ከነበረኝ መስተጋብር ተነስቼ መናገር የምችለዉ፤ ከጀርመናዉያን ጋር ለመግባባት ጊዜ ይወስዳል፤ ከተግባባኻቸዉ በኋላ ግን በጣም ጥሩ ሰዎች ናቸዉ። ሌላ ደሞ ለጊዜ ያላቸዉ ግንዛቤ በጣም ከፍ ያለ መሆኑን ብዙ ሰዉ የሚያዉቀዉ ነዉ። በጣም ጥንቁቅ ናቸዉ። ቋንቋዋቸዉ ትንሽ አስቸጋሪ ስለሆነ በጣም ተቀራርቦ ፤ ተነጋግሮ እርስ በርስ ለመፈታተሽ እንዲህ ነዉ፤ ለማለት ቢከብድም ጊዜ ላይ ግን ጥብቅና ሰዓት አክባሪ፤ በጣም የሚገርም አይነት የጊዜ ባህል ነዉ ያላቸዉ። ይህን የባቡር ወይም የከተማ ባስ የሚጠብቅ ሰዉ ያዉቀዋል። እኔ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ስጓዝ መዉረጃዬ ሲደርስ እወርድ የነበረዉ የከተማዉን ስም አንብቤ ሳይሆን ሰዓቱ መድረሱን አይቼ ነበር። 10:45 ባቡሩ እዚህ ቦታ ይደርሳል ከተባለ ያ ባቡር ባላት ሰዓት ጣብያዉላይ ይደርሳል፤ መዉረድ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ አብሪያቸዉ የቆየሁት ብዙ ጀርመኖች በጣም ታማኞች ናቸዉ፤ ብዙ ሲዋሹ አይገኙም፤ እዉነት እዉነቱን ነዉ የሚናገሩት።»    

ወጣት ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ይባላል ፤ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያና ፀሐፊ ነዉ። የአዉሮጳ ኅብረት ስደትን ለመቀነስ በሚያካሂደዉ ሥራ ግብዓት የሚሆን በፍልሰት ላይ ያተኮረ ትልመ ጥናት ወይም «ፕሮፖዛል» ለማቅረብ ነበር አጠር ላለ ጊዜ ወደ ጀርመን የመጣዉ። የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዉ ወጣት ዮርዳኖስ «ፍሪድሪሽ ኤበርት ሽቲፍቱንግ» የተሰኘዉ የጀርመን የጥናት ተቋም መንገደኛ የተሰኘዉንና ባለፈዉ ዓመት ለአንባቢ ይፋ ያደረገዉን መጽሐፉን ወደ እንጊሊዘኛ እያስተረጎመ እንደሆነና በቅርቡ  አንባብያን እጅ እንደሚደርስም ነግሮናል። ወጣት ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ «መንገደኛ» የተሰኘዉ መጽሐፉ በዋነኝነት  ከኢትዮጵያ ተነስተዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚጓዙ የወጣት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ማኅበራዊ፤ ባሕላዊ ፤ ኤኮኖምያዊ እና በመንገድ ያሳለፉት ሕይወትን የሚያስቃኝ መጽሐፍ ነዉ። በሳምንቱ መጀመርያ ወደ ሃገር ቤት የተመለሰዉን የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዉ ወጣት ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉን ወደ ሃገር ቤት ከመመለሱ በፊት አግኝተን ስለጀርመን ቆይታዉ እና ተሞክረዉ አነጋግረነዉ ነበር ።

Buchcover Wayfarers
ምስል Friedrich-Ebert-Stiftung Ethiopia

ወጣት ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ በስደተኞች ጉዳይ የተለያዩ ጥናቶችን አድርጓል፤ በጀርመን ግዙፍ የማኅበራዊ ሳይንስ ዩንቨርስቲ ወደሚገኝበት የጀርመንዋ ከተማ ቢለፌልድ እንዲመጣ ሙሉ ድጋፍንም ያገኘዉ ከዚሁ ዩንቨርስቲ እንደሆነ ተናግሮአል።  

ዮርዳኖስ ጀርመን ቢለፌልድ በቆየባቸዉ አራት ወራት ያህል ጊዜ ዉስጥ ከኢትዮጵያ ወደ አዉሮጳ የሚሰደደዱ ወጣቶች ሕይወት ምን ይመስላል የሚለዉን ጥናት ለመጀመር ትልመ ጥናት ወይም ፕሮፖዛል ለማቅረብ ዝግጅት ላይ እንደነበር ተናግሮአል።  

«ፍሪድሪሽ ኤበርት ሽቲፍቱንግ» የተሰኘዉ የጀርመን ጥናት ተቋም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ለወጣቶች የአመራር ስልጠናን ይሰጣል። ወጣት ዮርዳኖስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተቋሙ ለአምስተኛ ጊዜ በሰጠዉ ስልጠና ላይ ተሳታፊ እንደነበር ተናግሮአል። ተቋሙ በስደተኞች ጉዳይ የፃፈዉን «መንገደኛ» የተሰኘዉን መጽሐፉም ወደ እንጊሊዘኛ እንዲተረጎም አድርጎአል። የትርጉም ሥራዉ ተገባዶአል። በቅርቡ አንባብያን እጅ እንደሚደርስ ተስፋዉን ተናግሮአል።

በጀርመን ዩንቨርስቲዎች ለመግባት የሚከለክል አጥርም ሆነ ዘበኛ አለመኖሩ ዮርዳኖስን ሌላ ያስቀናዉ ነገር እንደሆን የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ዋና በር አልፎ ሌላ በር እና ጠባቂ ከዱላ ጋር መኖሩን በማስታወስ ተናግሮአል፤ ሌላም አለ አለ በመቀጠል፤ ከፖለቲካ ምህዳር ሌላ ስለ ማኅበራዊ ምህዳር መስፋት ቢታሰብብት ጥሩ ነበር ሲል፤ በጀርመን ያዜነዉ የማኅበራዊ ግንኙነት ምህዳር ስፋት ያስቀናል ብሎአል።  

ዮርዳኖስ ጀርመኖች የሚያስቀና ብቻ ሳይሆን የማያስቀና ከኛ ጋር መወዳደር የማይችሉበትም ነገር አግኝቶባቸዋል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ