1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«ኢትዮጵያን ችግር ለመለወጥ መንግስት ውስጣዊ አሰራሩን ያጠናክር»

ማክሰኞ፣ መስከረም 3 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው የሰላም መታጣት ችግር ለመውጣት መንግስት ውስጣዊ አሰራሩን ማጠናከርና የሕዝቡን መብትና ዕኩልነት ማስከበር እንደሚገባው ተገለጸ። ህወሓት፣ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሰላም ድርድር ከመጀመሩ በፊት፣ወደ ትግራይ ክልል ይሰጥ የነበረው አገልግሎት እንዲጀመር ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/4GnIq
USA I Blick nach New York
ምስል Lokman Vural Elibol/AA/picture alliance / AA

«ሕገ መንግስቱም መቀየር አሊያም ማሻሻል ያስፈልገዋል»

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው የሰላም መታጣት ችግር ለመውጣት መንግስት ውስጣዊ አሰራሩን ማጠናከርና የሕዝቡን መብትና ዕኩልነት ማስከበር እንደሚገባው ተገለጸ። ህወሓት፣ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሰላም ድርድር ከመጀመሩ በፊት፣ወደ ትግራይ ክልል ይሰጥ የነበረው አገልግሎት እንዲጀመር ጠይቋል።
በሞርጋን ስቴትስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣በኢትዮጵያ የሚታዩ አዳዲስ ክስተቶችን አስመልክቶ ከዶይቸ ቨለ ጋር ቆይታ አድርገዋል።  የጦርነት መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በተመለከተ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ሲናገሩ፣ከውስጣዊ ችግሮች ባሻገር ኀያላን ሀገሮች የሚያሳድሩት ተጽእኖ ቀላል አይደለም።በተለይም ኢትዮጵያን በተመለከተ፣ሃገሪቱ የምትገኝበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣የሕዝቧ ብዛትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዋ፣የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት መሆኗና የሕዝቧ ጥንካሬ የአሜሪካንን ጨምሮ የሌሎች ኀያላን መንግስታትን ስቧል ብሏል። ስለዚህም የኢትዮጵያን ወዳጅነት በመፈለግ፣በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለመቆጣጠር እንደሚፈልጉ ፕሮፌሰር ጌታቸው አመልክተው፣ይህ ካልተሳካላቸው አሁን እንደሚታየው ሃገሪቱን ለማዳከም በተለያየ መንገድ እንደሚሞክሩ አስረድተዋል።
"በመጀመሪያ በኢትዮጵያም ቢሆን ብልሹ አስተዳደር፣ያው ውሎ አድሮ ከመንግስት ምላሽ ካላገኘ፣ምሬቱን በሕጋዊ መንገድ ካልቻለ በዐመጽ መልስ ለማግኘት ይሞክራል።የመሪዎች ስነ ልቦና ለምሳሌ የስልጣን ጥማት የተሳሳቱ ዕይታዎችና ከተሳሳተ ታሪክ በመነሳት በእነዚህና በመሳሰሉት ጦርነቶች ይነሳሉ።የውጭ ሃገሮች ብሔራዊ ጥቅማቸውን የማስከበር ዘመቻ፣ እነዚህ ሁሉ እንግዲህ የጦርነት መነሾ ሊሆኑና በአንድ ሃገር ውስጥ በኢትዮጵያም ቢሆን የጦርነት መንስዔ ናቸው በታሪክም በሚታየው አሁንም ባለውም።"

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ መንግስት ጋር የሠላም ድርድር ከመጀመሩ በፊት ወደ ትግራይ ክልል ይሰጥ የነበረው መሠረታዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ጠይቋል። ቡድኑ በትላንትናው ዕለት አወጣው በተባለ መግለጫ፣የትግራይ ሕዝብ፣የሠላም ድርድር ከመደረጉ በፊት መወገድ ያለበት ሰብዓዊ ዕገዳ ስር እየኖረ ነው ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል። ይኸው መግለጫ፣ህወሓት በአፍሪክ ህብረት በሚደረገው የሰላም ሂደት ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅቼያለሁ ካለ ከአንድ ቀን በኋላ የመጣ መሆኑ ነው። 
የህወሓት አመራሮች፣ የአፍሪካ ህብረት ሰላም ስለማምጣቱ ጥርጣሬ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ከቆዩ በኋላ ነበር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ያስታወቁት። ይህንኑ የአቋም መለዋወጥ፣ፕሮፌሰር ጌታቸው የፖለቲካ ብልጣብልጥነት ሲሉ ገልጸውታል። "ይህ ሁሉ ትክክል ያልሆነ እና የብልጣብልጥነት ፖለቲካ ነው የሚጫወቱት፤መንግስት ይህን ሁሉ ጥሩ አድርጎ ለውጭ ሃገራት ማስረዳትና ተአማኒነት ያጣ ድርጅት እንደሆነ መናገርና ማስረደት ያለባቸው ይመስለኛል።የፖለቲካ ትግሉን ማጠናከርና ግፊት መፍጠር ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ነው።"

Logo Afrikanische Union
ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣በተባበሩት መንስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፣የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ግጭቱን ለማስቆም በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት መዘጋጀታቸውን በደስታ እንደተቀበሉት አስታውቀዋል። አምባሳደሯ ትናንት በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ተፋላሚ ኀይላቱ ሁከትን አስቁመው ውይይትን እንዲመርጡና ይህንን ጊዜ እንዲጠቀሙ እናበረታታለን ብለዋል። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ጌታቸውም፣መንግስት ውስጣዊ ጥንካሬውን በማሳደግ እንዲሁም የሕዝቡን መብትንና ዕኩልነት በማስከበር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው የሰላም መታጣት ችግር መፍትሔ እንዲያፈላልግ ያስገነዝባሉ።

"የአንድ ሃገር ተወካይ ነኝ የሚል ማንም መንግስት፣ማድረግ ያለበት አለ።ለምሳሌ አንደኛ ውስጣዊ ጥንካረውን ማጠናከርና ያንን የጠና ድንጊያ መመስረቱ አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል።መብቱ የተከበረለት ዕኩልነቱ የተረጋገጠ ደስተኛ ሃገሩን ወዳድ ኩሩ የሆነ ሕዝብ በተለይ ወጣቱን መኮትኮት ያለበት ይመስለኛል።ወጣቱም ሆነ ሌላው ከቦታ ቦታ እንደድሮው በነጻነት በሰፊይቱ ኢትዮጵያ እንዲዘዋወር፣ዕውቀትና ሀብት እንዲያፈራ ሰላማዊ ኑሮ የሚገፋበት ይህንንም ዕውን የሚያጀርግ ህዝባዊ መንግስት መመስረት የግድ ይላል።" ኢትዮጵያ ውስጥ የወል የሆነ ዕይታ እንዲመጣ ጥረት መደረግ እንደሚኖርበትና፣ሕገ መንግስቱም መቀየር ወይም አሊያም ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አስረድተዋል።

ታሪኩ ኃይሉ 
አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ