1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት እና ሳንካዎቹ

ማክሰኞ፣ ጥር 16 2015

የዩናይትድስቴትስን የውጭ ፖሊሲ የሚያዘጋጀው ዋይት ሐወስ ብቻ አይደለም። ኮንግረሱ፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማህበረሰብና በውጭ የሚኖሩም ጭምር ናቸው። በቅርብ ጊዜ ዩናይትድስቴትስ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ በርግጥ በጣም መከፋፈል የሚታይበት ነው። ዋሽንግተን ውስጥ ያለው የተወሰነ አካል ነገሮችን የሚያይበት መንገድ በጣም የተለየ ነው።"

https://p.dw.com/p/4Mdbh
USA Präsident Biden Chips Act
ምስል Brendan Smialowski/AFP/Getty Images

በኢትዮጵያና በአሜሪካ ያለው ግኑኝነትና ሳንካዎቹ

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መኻከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ ከመቶ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ሲል የቆየው ይኼው ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት፣ አሁን ውሉ ገና ባልለየለት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነው የሚነገረው። ለዚህምው፣አንድም ልዕለ ኀያላኑ ሃገራት በምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ የሚያካሂዱት ፉክክር፣ሌላም አሜሪካ ትከተለዋለች የሚባለው የረጅም ጊዜ ስልት የሌለውና በአስገዳጅነት መርህ ላይ የተመሠረተ ዴፕሎማሲያዊ መንገድ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያዊነት የተሰኘው ድርጅት ሰሞኑን ያካሄደው ጉባኤ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊው ዘመን አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ፣በተለይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ፣በኢትዮጵያና በአሜሪካ መኻከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ክስተቶችን የፈተሸ ነበር። ዶይቨ ቨለ ስለጉባዔው ያነጋገራቸዉ ዶክተር ዕርቁ ይመር፣የኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ድርጅት መስራችና የቦርድ አባል ናቸው።

"እንግዲህ አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በሗላ፣ ጦርነቱን ተከትሎ በተለያየ ጊዜ የዓለም አቀፍ ጋዜጦች፣የምዕሩቡ መንግስታትም በአጠቃላይ በኢትዮያ ላይ ጥሩ አመለካከትና ጥሩ ግንዛቤ አልነበራቸውም።እና ያ ኹኔታ፣ በተለያየ ጊዜ የተናገሩትንና የኢትዮጵያ መንግስት የከሰሱበት መንገድ፣በሌሎች በጥናት ላይ የተደገፈ አልነበረም። ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ አልነበረም።በተለያየ ጊዜ ጋዜጠኞች፣ጥናት አጥኚዎች፣የዩኒቨርስቲ ምሁራን ነገሩን ተከታትለው እንደተባለው እና እንደክሱ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፤እና ይኼ ለምን ኾነ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው።"

በዚህ ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት፣ የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በኢትዮጵያ የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር ቲቦር ናዥ፣አሜሪካ በኢትዮጵያ አኳያ የምትከተለው ፖሊሲ፣ዋሽንንግተን ያለውና የተከፋፈለ ያሉት አስተያየት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ተናግረዋል።

"በአንድ ፖሊሲ ላይ ዋሽንግተን አንድ ነው ወይስ የተከፋፈለ፣ምክንያቱም የዩናይትድስቴትስን የውጭ ፖሊሲ የሚያዘጋጀው ዋይት ሐወስ ብቻ አይደለም።ኮንግረሱ፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማህበረሰብና በውጭ የሚኖሩም ጭምር ናቸው።በቅርብ ጊዜ ዩናይትድስቴትስ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ በርግጥ በጣም መከፋፈል የሚታይበት ነው።ዋሽንግተን ውስጥ ያለው የተወሰነ አካል ነገሮችን የሚያይበት መንገድ በጣም የተለየ ነው።"

የኢትዮጵያንና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዕድሎችና ተግዳሮቶች የፈተሸው የዚህ የበይነ መረብ ጉባኤ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎች መኻከል፣ ክቡር ልዑል ኤርምያስ ሳህለ ሥላሴ ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የሚኖራት ወዳጅነት፣በህዝቧ ልብና አዕምሮ ላይ የተመሠረተ ሊኾን ይገባዋል ባይ ናቸው ልዑሉ።

"ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የሚኖራት ግንኙነት፣ አሜሪካ እንዴት መሆን እንዳለበት የምትመራው ብቻ መሆን የለበትም፣ይልቁንም ኢትዮጵያ በራሷ የምትወስንበት ሊሆን ይገባዋል።"  በዚኹ ጉባዔ ላይ፣ ሌሎችም ምሁራንና ባለሙያዎች፣የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካ በመገምገም ወደፊት ሊወሰዱ በሚገባቸው ርምጃወች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።


ታሪኩ ኃይሉ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ