1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያና የምዕራባዉያን ወዳጅነትና ልዩነት

ረቡዕ፣ ጥር 24 2015

ሚኒስቴሩ የሀገርን ጥቅም ምን ያህል እያስጠበቀ ነው የሚለው ከውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጎላ ብሎ ተጠይቋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ለዚህ ምላሽ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4MyhP
Äthiopien Annalena Baerbock zu Besuch
ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

የኢትዮጵያ የዉጪ መርሕ የገጠመዉ ፈተና

 

በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት የተፈፀመዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት በገለተኛ ባለሙያዎች እንዲመረመር የሚቀርበዉ ጥያቄ በኢትዮጵያ መንግስትና በምዕራባዉያን መካከል ልዩነት መፍጠሩን የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የመስሪያቤታቸዉን የግማሽ ዓመት የሥራ ዘገባ ዛሬ ለተወካዮች ምክር ቤት የዉጪ ጉዳይና የሕግ ኮሚቴ ሲያቀርቡ እንዳሉት የሰላም ዉል በመፈረሙ ምዕራባዉያን ደስተኞች ናቸዉ።የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በሚመረመርበት ሒደት ግን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አሁንም ልዩነት አላቸዉ።አቶ ደመቀ የሁለት ዓመቱን ዲፕሎማሲ «ከዉጪም፣ከዉስጥም በረዶ ዘንቦበት ነበር» ብለዉታል።

የሀገር ውስጥ ሰላም ከሌለ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ሥራ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩ መሠረታዊ የሥራው ማዕከል መሆኑን ገልጿል። ሚኒስቴሩ የሀገርን ጥቅም ምን ያህል እያስጠበቀ ነው የሚለው ከውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጎላ ብሎ ተጠይቋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ለዚህ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ይሄ ሁለት ዓመት በተለይ የመጀመርያው ዓመት እጅግ በጣም ከፍተኛ ፈተና በረዶ እንደወረደብን አድርገን ልንመለከተው እንችላለን"።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት መደረጉና የገለፁት ሚኒስትሩ ከሱዳን ጋር እየተስተዋለ ነው ያሉትን የግንኙነት መሻሻል በበጎ ማሳያ ጠቅሰዋል።
"ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በጋራ ጥቅሞቻችን፣ በመከባበር እና በመደማመጥ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መጠናከር አለበት"
ኢትዮጵያ አራት የኢጋድ አባል ሀገራት አባል በሆኑበት የቀይ ባህር ምክር ቤት አባል አለመሆኗ ፣ የወደብ አማራጯ መጥበብ ፣ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት ማብራሪያ ተጠይቆበታል።
"ኢትዮጵያን እውቅና ያልሰጠ እና ያላሳተፈ መድረክ ዘላቂነትም ጥቅምም እንደማይኖረው ለማሳየት እየሰራን ነው" 
የተለያዩ ክልሎች እና አልፎ አልፎ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከውጭ ሀገራት ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲያደርጉ እየተስተዋለ ነው። ይህ የሚሆነው በውጭ ገዳይ እውቅና ነው ወይ? የሚል ጥያቄም ቀርቦ ነበር። ሚኒስትሩ ምላሽ ሳይሰጡበት አልፈውታል።
ከሕወሓት ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ የምእራቡ ዓለም ደስተኛ ስለመሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን አብራርተዋል ።
ከቋሚ ኮሚቴው "የተደራጀ የደቡብ ሱዳን ኃይል እስከ 80 ኪሎ ሜትር ኢትዮጵያ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ሕዝብ ላይ ጥቃት እፈፀመ ነው" መንግሥት አጣርቶ እርምጃ ይውሰድ የሚል ሀሳብም ቀርቧል።
የውጭ ገዳይ ሚኒስቴር ብቃትን መሰረት ያደረገ አዲስ የዲፕሎማሲ አሠራርን እየተገበረ የሀገርን ሁለንተናዊ ጥቅም እንደሚያስጠብቅ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዉ.ጉ.ሚ አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር
የኢትዮጵያ ዉ.ጉ.ሚ አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋርምስል Russian Foreign Ministry Press Service/AP/picture alliance
የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግና የኢትዮጵያ አቻቸዉ ደመቀ መኮንን
የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግና የኢትዮጵያ አቻቸዉ ደመቀ መኮንን ምስል Fana Broadcasting Corporate

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ