1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የአምነስቲን ዘገባ አጣጣለ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11 2012

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ግንቦት ይፋ ያደረገው ዘገባ “ጥቂትና ተዓማኒነት የጎደላቸው ምስክርነቶችን” በመያዝ የተዘጋጀ ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወቀሰ። አምነስቲ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን የመረመረበት ዘገባ እውነት ያልሆኑ መረጃዎችን አካቷል፤ በገሐዱ ዓለም የሌሉ ምሥክሮችን ስም እና ኃላፊነት እየጠቀሰ አቅርቧል ሲል ከሷል።

https://p.dw.com/p/3fX3G
Amnesty International Protest Wahlen in Malin 2013
ምስል picture-alliance/dpa/W. Kumm

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን በመመርመር ባለፈው ግንቦት ይፋ ያደረገውን ዘገባ “ገለልተኝነት የጎደለው” ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ወቀሰ። የአምነስቲ ዘገባ “ጥቂት እና ተዓማኒነት የጎደላቸውን ወይም ወገንተኛ የሆኑ ምስክርነቶችን በመያዝ እጅግ ውስብስብ በሆኑ ግጭቶችና የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ የተሳሳቱ መደምደሚያዎች ላይ የሚደርስ ነው” ብሏል።  

የፌድራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች በተቋቋመ አጣሪ ቡድን “በሪፖርቱ ይዘት የተዘረዘሩ የመብት ጥሰቶችን ማጣራቱን ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫ አስታውቋል።  

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዘገባ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ አስከባሪዎች ግድያ፣ የጅምላ እስር እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽመዋል ሲል ከሷል። ዘገባው እስካለፈው ታህሳስ ወር ድረስ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ያለውን ነባራዊ ኹኔታ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመረመረበት ነው። 

“የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መንግስት ሕግ ለማስከበር የሚወስደውን እርምጃዎች ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድርጎ የማጠልሸት ዝንባሌ የሚስተዋልበት፣ በአብዛኛው ገለልተኝነት የጎደለው፣ የማስረጃ ምዘና ችግር ያለበት፣ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና ዓውድ ያላገናዘበ” ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነቅፏል።

“በከፊልም ቢሆን ተዓማኒነት ያላቸው እና በዘገባው ውስጥ ከተካተቱት የመብት ጥሰት ወቀሳዎች በርካቶቹ ጉዳዮች ሪፖርቱ በአምነስቲ ከመውጣቱም በፊት በመንግሥት ታውቀው ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የምርመራ ስራ ሲከናወንባቸው የነበሩ” መሆናቸውን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ ይጠቁማል።  

የአምነስቲ ምርመራ እና ውጤቱ የቀሰቀሰው ውዝግብ

ዘገባው “ጥቂት እና ተዓማኒነት የጎደላቸውን ወይም ወገንተኛ የሆኑ ምስክርነቶችን በመያዝ እጅግ ውስብስብ በሆኑ ግጭቶችና የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ የተሳሳቱ መደምደሚያዎች ላይ የሚደርስ” ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኮንኗል።  

“በሕግ ማስከበር ሒደት በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ሁሉ የመብት ጥሰት አድርጎ ለማቅረብ ባደረገው ጥረት መሬት ላይ የሌሉ ጉዳዮችን እንዳሉ በማስመሰል የሚያቀርብ” ነው ያለው መግለጫው የታጣቂ ቡድኖች ሚና አለመካተቱን ጠቅሷል።

“የታጠቁ እና በሕቡዕ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተለይም በጉጂ ዞን በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ እየፈፀሙ የነበረውን ወንጀል እና ጥቃት አልገለጸም” ያለው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እውነት ያልሆኑ መረጃዎችን አካቷል፤ በገሐዱ ዓለም የሌሉ ምሥክሮችን ስም እና ኃላፊነት እየጠቀሰ አቅርቧል በማለት ባለፈው ግንቦት የወጣውን ዘገባ ተዓማኒነት አጣጥሏል።  

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዘገባው ተፈጥረዋል ያላቸው ግድፈቶች “የአጋጣሚ ስሕተት ሳይሆን አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሪፖርቱ ጸሃፊዎች ከዚህ ቀደም በስልጣን ላይ የነበሩና አሁን ለውጡን ለማደናቀፍ እየሰሩ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የነበራቸው የሚታወቅ ንቁ ተሳትፎ ጋር ተያይዞ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው” ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።  

“አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቀጣይ ከመንግስት ጋር ለሚኖረው በጎ ትብብር እና የሥራ ግንኙነት ሲባል የዚህን ሪፖርት አዘገጃጀት በተመለከተ የውስጥ ምርመራ” እንዲያደርግ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥሪ አቅርቧል።