1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የግንባታ ግብዓቶች ገበያ እና የሥራ ተቋራጮቹ ፈተናዎች

ረቡዕ፣ ግንቦት 10 2014

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ጦርነት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና የጸጥታ መጓደል የበረታባቸው ያለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ሥራ ተቋራጮችና የግንባታ ግብዓቶች ገበያውን ተፈታትነዋል። የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ከዓለም ገበያ ለሚሸምቷቸው ግብዓቶች የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቸግራቸዋል። ከኤኮኖሚያዊ ሁኔታው የተስማማ የዋጋ ክፍያ ማስተካከያ ጉዳይም ይነሳል

https://p.dw.com/p/4BTXo
Äthiopien | Straßenszene in Addis Abeba
ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ የግንባታ ግብዓቶች ገበያ እና የሥራ ተቋራጮቹ ፈተናዎች

አንድ ኩንታል ስሚንቶ ከ1 ሺሕ 170 ብር በላይ በሚሸጥባት የጂንካ ከተማ የሚገኘው አርሴማ ብሎኬት እና ብሪክ ሥራ ማኅበር ያቋረጠውን ሥራ ገና መልሶ መጀመሩ ነው። አምስት አባላት ያሉት ይኸ ማኅበር በቀን እስከ 1200 ብሎኬቶች ያመርታል። ማኅበሩ የሚያመርታቸውን ብሎኬቶች እና ሌሎች የግንባታ ግብዓቶች ለግለሰቦች "አልፎ አልፎ" ደግሞ ለመንግሥት ተቋማት እንደሚያቀርብ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝቅአርጋቸው ታደለ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከአዲስ አበባ በ440 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በደቡብ ኦሞ ዞን በምትገኘው ከተማ ሥራውን ለመሠረተው ማኅበር ግን ያለፉት ዓመታት ፈታኝ ሆነዋል። የስሚንቶ ዋጋ መናር ያስከተለው የግንባታ መቀዛቀዝ በገበያው የብሎኬት ፍላጎት እንዲቀዘቅዝ አድርጎታል። 

አቶ ዝቅአርጋቸው ታደለ "በአሁኑ ወቅት አንድ ኩንታል ስሚንቶ የምንገዛው አንድ ሺሕ አንድ መቶ 70 ብር ነው። ዋጋ በጨመረ ቁጥር ቤት ገንቢዎች ያቆማሉ፤ ይቀንሳሉ። አሁን የሚጠቀሙት ግንባታ ላይ ያሉ ናቸው እንጂ አዲስ የሚሰራ ሰው በአሁን ሰዓት የለም" ሲሉ በሥራቸው ተጽዕኖ ያሳደረውን የገበያ ኹናቴ ተናግረዋል።

ይኸ የገበያ መቀዛቀዝ ማኅበሩ ሠራተኞቹን አሰናብቶ ከአንድ ወር በላይ ሥራውን እንዲያቆም አስገድዶታል። አቶ ዝቅአርጋቸው የሚመሩትን ማኅበር ሥራ ለማቆም ያስገደደው ግን ይኸ ብቻ አይደለም። "እኛ አካባቢ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ነበር። በዚያ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሥራ እንድናቆም ነው የተደረገው። አሁን ነው የተረጋጋው እንጂ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልነበረም። ሙሉ በሙሉ ሥራ አቁመን ነው ቁጭ ያልነው" ሲሉ የብሎኬት አምራች ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል።

አቶ ዝቅአርጋቸው የጠቀሱት "ፖለቲካዊ አለመረጋጋት" ከዞን አወቃቀር ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰ ነው። የአካባቢው ባለሥልጣናት "ልብ የሚሰብር እና ሰው ከሆነ ፍጡር" የማይጠበቅ ባሉት እና ሚያዝያ 1 ቀን 2014  በተፈጸመ ጥቃት ሰዎች መጎዳታቸውን፣ የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እና ንብረት መዘረፉን የከተማው የኮምዩንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በደቡብ ኦሞ ዞን የምትገኘው የጂንካ ከተማ ከገጠማት የጸጥታ ቀውስ የማገገም አዝማሚያ ስታሳይ እነ አቶ ዝቅ አርጋቸው ወደ ሥራቸው ቢመለሱም ይቀንሳል ያሉት የስሚንቶ ዋጋ ለውጥ አላሳየም።  የጂንካ ከተማ ከስሚንቶ አምራቾች እና የግንባታ ዕቃዎች ግብይት ከሚካሔድበት ማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል ያለው ርቀት ሌላው ፈተና ነው።  ዕቃ "በኪራይ ነው የምትጭነው። ከአዲስ አበባ ለመጫን በፈለክበት ወቅት ተሽከርካሪ አይገኝም። ሌሎች ግብዓቶች ደግሞ ከወላይታ ሶዶ ነው የሚመጡት። በዚህ ምክንያት በጣም ፈታኝ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የግንባታ ዕቃዎች ግብይቱ ዋንኛ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባም ቢሆን የስሚንቶ ዋጋ ያለፉትን ተከታታይ ወራት በቅጡ መርጋት ተስኖት ታይቷል። በአዲስ አበባ እና በዙሪያው የግንባታ ዕቃዎች በማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አስፋው አባተ የስሚንቶ ዋጋ ከዕለት ዕለት እንደሚቀያየር ይናገራሉ። ግንቦት 9 ቀን 2014 አቶ አስፋው "አንድ ኩንታል የዳንጎቴ ስሚንቶ 940 ብር ገደማ ነው የዋለው። የሙገር ስሚንቶ 930 ብር አካባቢ ነበር። ሐበሻ 890 ብር ነበር" ሲሉ የዋጋ ተመኑ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ አስረድተዋል።

Äthiopien Oromia | Zementfabrik
በጂንካ ከተማ አንድ ኩንታል ስሚንቶ ከአንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር በላይ እንደሚሸጥ ብሎኬት በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ የከተማው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ በአንጻሩ አንድ ኩንታል ስሚንቶ ከ890 እስከ 930 ብር ይሸጣል።ምስል Seyoum Getu/DW

የስሚንቶ ግብይቱ ላይ የታየውን ያክል አይሁን እንጂ ጠጠር፣ አሸዋ እና የግንባታ ድንጋይን የመሳሰሉ ግብዓቶችም ጭማሪ አሳይተዋል። "በ2013 የዛሬ አመት አካባቢ አንድ ሜትር ኪዩብ የ02 ጠጠር ዋጋ እስከ 580 ብር ሊሆን ይችላል። ዛሬ ግን በሜትር ኪዩብ ከ650 እስከ 800 ነው የሚሸጠው" ሲሉ የግንባታ ግብዓቶች ነጋዴው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የግንባታ ዕቃዎች ገበያ በዋናነት ከፈተኑት መካከል ቀዳሚው አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ ከዓለም ገበያ የምትሸምታቸው ግብዓቶች ዋጋ ነው። የብረታ ብረት፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ለመንገድ ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተመን ጭማሪ ማሳየቱን ዶይቼ ቬለ ከነጋዴዎች እና ከኮስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ለመረዳት ችሏል። የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ኩባንያዎች በአንጻሩ የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቸገራቸው ፈታኝ ሆኖባቸዋል። “ብዙ ኮንትራክተሮች ንብረታቸውን ሸጠው መቶ በመቶ ፈርሰዋል" የሚሉት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝደንት ግርማ ሀብተማርያም (ኢንጂኔር) "ይኸ አምስት ዓመት ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና የሆነ እና በተለይ በግንባታው ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አድርሷል" ሲሉ ተናግረዋል።  

"የእነዚህ ፕሮጀክቶች መዘጋት፤ የእነዚህ ኩባንያዎች ከገበያ መውጣት በአገሪቱ ላይ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሥራ ፈትነትን ፈጠረ ማለት ነው። ሁለተኛ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ አሁን ፕሮጀክቶች ቀንሰዋል። በጀት የለም። በዚህም ፕሮጀክቶች ተቀንሰዋል። በአብዛኛው የሚታየው ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ነው። የግል ኩባንያዎች አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን መዘርጋት አይችሉም። በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው የኤኮኖሚ ሳቦታጅ ቀደም ብለው የገቡትን የፊኒሺንግ ማቴርያሎች ይደብቃሉ። ዋጋ እስከሚንርላቸው ድረስ ይጠብቃሉ። ዋጋ ሲንርላቸው ይሸጡታል። የአርማ ብረት አንድ ጊዜ ከፍ ያደርጉታል፤ አንድ ጊዜ ዝቅ ያደርጉታል። ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ በወጣ መልኩ የኮንስትራክሽን ገበያውን በመረበሻቸው አገር ውስጥ ያሉትን ፕሮጀክቶች ብልጭ ድርግም እንዲሉ ያደርጓቸዋል” ሲሉ ጫናውን የምኅንድስና ባለሙያው ይዘረዝራሉ።

Äthiopien Awassa
የኢትዮጵያ መንግሥት በሚሊዮን ዶላሮች ወይም በቢሊዮን ብሮች ለሚያስገነባቸው ዕቅዶች ጨረታ ሲያወጣ የአገሪቱ የኮስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ከቻይና ኩባንያዎች ትከሻ መጋፋት ይጠበቅባቸዋል። የፈረጠመ የገንዘብ አቅም፣ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ያሏቸው የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባንኮች የዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻዎች ግንባታን ተቆጣጥረዋል። ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የኮቪድ-ወረርሽኝ፣ ጦርነት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የጸጥታ መጓደል የበረታባቸው ያለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች እና የግንባታ ገበያውን በኃይል ተፈታትነዋል። ይኸ በተለይ በኢትዮጵያ 45 ዩኒቨርሲቲዎች የነበሩ የግንባታ ውጥኖች ላይ በተጨባጭ የታየ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝደንት ግርማ ሀብተማርያም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሚሊዮን ዶላሮች ወይም በቢሊዮን ብሮች ለሚያስገነባቸው ዕቅዶች ጨረታ ሲያወጣ የአገሪቱ የኮስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ከቻይና ኩባንያዎች ትከሻ መጋፋት ይጠበቅባቸዋል። የፈረጠመ የገንዘብ አቅም፣ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ያሏቸው የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባንኮች የዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻዎች ግንባታን ተቆጣጥረዋል። በርካታ የመንገዶች፣ የኃይል ማመንጫዎች እና መሰል የመሠረተ-ልማት ግንባታዎችም የቻይና ኩባንያዎች እጅ ይገኛሉ። ወደ 2 ሺሕ 400 ገደማ አባላት ያሉትን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር በፕሬዝደንትነት የሚመሩት የምኅንድስና ባለሙያው ግርማ ሀብተማርያም ውድድሩ ፍትኃዊ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የኮስትራክሽን ግብዓቶች ገበያም ሆነ ተቋራጮች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ዘርፉ ያለበትን የውጭ ምንዛሪ ተግዳሮት መፍታት አንዱ ሊሆን እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ግርማ ሀብተማርያምም ቢሆኑ በዚህ ይስማማሉ። ይሁንና ይኸ ብቻውን ችግሩን የሚፈታው አይመስልም። የምኅንድስና ባለሙያው መፍትሔ ያሿቸዋል የሚሏቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ የከተማ እና የመሠረተ ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚለከታቸው መስሪያ ቤቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግንው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ