1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴያትር መቶ ዓመት በሰሜን አሜሪካ ተከበረ

እሑድ፣ መስከረም 23 2014

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴያትር መቶ ዓመት ሞላው::የሃገር ቤቱን ክብረ በዓል ተከትሎ ካናዳን ጨምሮ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የቴያትር ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴያትር የተጀመረበትን መቶኛ ዓመት በዋሽንግተን ዲሲ አክብረዋል:: ይኸው ልዩ ክብረ በኃል የተካሄደው ሲልቨርስፕሪንግ ሜሪላንድ በሚገኘው ሞንቶጎመሪ ኮሌጅ የቴያትር ማዕከል ውስጥ ነበር::

https://p.dw.com/p/41COJ
Äthiopien National Theater feiert 60-jähriges Jubiläum Tekle Desta
ምስል Tekle Desta

መዝናኛ

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴያትር መቶ ዓመት ሞላው::የሃገር ቤቱን ክብረ በዓል ተከትሎ ካናዳን ጨምሮ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የቴያትር ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴያትር የተጀመረበትን መቶኛ ዓመት በዋሽንግተን ዲሲ አክብረዋል::እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር መስከረም 19 ቀን 2021 የተከበረው ይኸው ልዩ ክብረ በኃል የተካሄደው ሲልቨርስፕሪንግ ሜሪላንድ በሚገኘው ሞንቶጎመሪ ኮሌጅ የቴያትር ማዕከል ውስጥ ነበር::

የመዝናኛ ዝግጅታችን የበዓሉን አከባበር ይቃኛል::

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴያትር የተጀመረበትን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተቀዛቀዘውን የሃገሪቱን ቴያትር እንዲያንሰራራ ለማስቻል "ስለቴያትር"የሚል እንቅስቃሴ የተጀመረው ሃገር ቤት ባሉ ከያንያንና ዓላማቸውን ደግፈው ከጎናቸው በተሰለፉ ጥበበኞች ነው::የሰሜን አሜሪካው ክብረ በዓል የዚሁ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ አንጋፋው አርቲስት ተስፋዬ ሲማ ይናገራል::

"ሁላችንም የኢትዮጵያው ቴያትር ጥበብ እንዲያድግ እንዲበለጽግ በበጅሮንድ ተክለኃዋሪያት ተክለማሪያም ወደሃገራችን የገባው ፈረንጅ ቅርፅ ላይ የተመሠረተው ቴያትራችን እጅግ በጣም አድጎ በተለይም በሰባዎቹና በሰማንያዎቹ እጅግ የጎመራበትና ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት በርካታ ባለሙያዎች የፈሩበት ቴያትር ቤቶች በጥሩ ሁኔታ ዝግጅታቸውን የሚያቀርቡበት በርካታ ቴያትር ቤቶች አሉን እና እንዲሁም በርካታ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ደሚመረቁ ተማሪዎች ከሶቭየት ህብረትና ጀርመን የሚመጡ ተማሪዎች እንዲሁም በስልጠና እዚያው እያደጉ የመጡ ተማሪዎች እጅግ በጣም ያየሉበት እና ክበባትም የበለፀጉበት ጊዜ በመሆኑ የተነሳ ከፍተኛ ዕድገት ያሳየበት ዘመን ነው::አሁን ያ ቀርቶ ቴያትር ቤቶቹ በሙሉ እንደእነ ራስ ቴያትር ያሉት ሆን ብሎ መንግሥትም ቴያትር ባለበት ቀን ለስብሰባ እንዲውል በማድረግ እየተዳከመ እንዲሄድና የታክሱም ራሱ ከአልኮል መጠጦች በላይ ነው ታክስ የሚደረገው ኑሮ እየተወደደ በሄደ ቁጥር ቤተሰቦች እንዲገዙ የሚደረገው የትኬት ሽያጭ እንኳን እንዳለ ነው::ሌላው የምግብ የመጠጥ እያደገ ይሄዳል የትያትር ግን በዚያው ሂሳብ ነው አሁንም ሰው የሚገባው::እነዚያ እነዚያ ነገሮች እየተስተካከሉ እንዲመጡ ነው::እኛም ሙሉ እገዛችን ኢትዮጵያ ላለው የቴያትር ዕድገት ነው::በእርግጥ እኛም ባለንበት ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመት 25 ዓመታት ውስጥ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል::በጣይቱ ማዕከል መላውን አሜሪካ እንዲሁም ካናዳን መላውን አውሮፓ እስከ አፍሪካና በዚሁ ተጉዘናል::በርካታ ስራዎችን ለመስራ ሞክረናል::እኛም የዛው አካል ነን::"

በዋሽንግተን ዲሲ የተከበረው የኢትዮጵያ ቴያትር መቶኛ ዓመት ስለኢትዮጵያ ቴያትር ወቅታዊ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ በባለሙያዎች ውይይት ተካሄዶበታል::የኢትዮጵያ ቴያትር በዘመኑ በገጠሙት ፈተናዎችና በነገ ተስፋዎቹ ላይም መክሯል::የቴያትርና ስነፅሑፍ ባለሙያ አለማየሁ ገብረህይወት ስለውይይቱ ተከታዩን አካፍሎናል::

"ባለሙያዎቹ ብቻ የተካፈሉበት የትያትር መቶኛ ዓመት ቴያትራችን ምን ይመስል ነበር ጉዞው የሚል አንድ እንዲሁም ላለፉት አምስት ስድሳት ዐመታት ቴያትራችን ተቀዛቀዘ ተዳከመ ስለሚባል ምን ማለት ነው የሚለውን እንደዚሁ መጀመሪያ ፓናሊስቶች የመነሻ ሃሳብ ያቀርቡና ውይይት ነበር የነበረው ሌላው የቴያትር መቶኛ ዓመት ቢሆንም እዚህ ደግሞ በሰሜን አሜሪካ ያለን ኢትዮጵያውያን የኪነጥበብ ባለሙያዎች መንቀሳቀሳችን አልቀረም::መጀመሪያ ከስደት ጌዜ በደርግ ጊዜ ጀምሮ እነ ኃይማኖት ዓለሙ እዚህ ሃገር በነበረበት የሰራቸው ሥራዎች አሉ::ሌሎች ደግሞ ከሃገር ቤት እየመጡ እያሳዩ የሄዱባቸው ነገሮች አሉ::ከዛ በኃላ ግን መልክ ባለውና በተደራጀ ሁኔታ የተገኙት ጣይቱ የትምህርትና ባህል ማዕከል ሌሎች ደግሞ ስማቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል ዜማና ብዕር ሚኔሶታ አለ አትላንታ አሉ ካናዳ ውስጥ አሉ::ስነግጥም ላይ ያተኮሩ ቢሆንም ቴያትር የሚሠሩ ቡድኖች ተቋቁመው የቴያትር እንቅስቃሴ ያደርጋሉ::እኛ ግን እዚህ ላይ ፎከስ ያደረገ ውይይት አድርገናል::መጨረሻ ላይ ደግሞ እንደመነሻ ሐሳብ የቀረበው ወደፊት ምን እናድርግ ምን ማድረግ ይቻላል ከዚህ ሆነን ተቀዛቀዘ የተባለውን የኢትዮጵያ ቴያትር እንዴት አድርገን ሰፖርት እናድርግ እንደግፍ ሁለተኛ በሙያችንስ እንዴት መስራት እንችላለን ይህን ያህል የሰው ኃይል ካለን እና አብረን በተደራጀ መልኩ  የምንሰራበት ነገር እንንነጋገር የሚል ሐሳቦች ተነስተዋል::

የኢትዮጵያ ቴያትር መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል ዲሲ ደምቆ እንዲከበር ካደረጉ ዝግጅቶች መኻከል በታላላቅ የመድረክ ፈርጦች የቀረበው የቴያትር ድግሥ ነበር::ተመርጠው ከቀረቡት ቴያትሮች መኻከል "ዚቀኛው ጆሮ" የተሰኘው ይገኝበታል::ተዋናይ ሽመልስ ጆሮ ሲጫወተው የተቀነጨበው ክፍል እነሆ

'አንድ መቶኛ ዓመት የልደት በዓሉን ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴያትር የኅዳሴ መጀመሪያ እናድርግ' በሚል መርዕ አንግቦ በተከበረው የዲሲው ክብረ በዓል ላይ አንጋፋ የቴያትር ባለሙያዎች ምስጋና ተችሯቸዋል::በሕይወት የሌሉ ባለሙያዎች ደግሞ ተዘክረዋል::አንጋፋና ወጣት የቴያትር ባለሙያዎች የተካተቱበት የፎቶ ኤግዚቢሽን ቀርቧል::

ባለሙያዎቹ ወደፊት በሚወዱት ሙያ ዘላቂ በሆነ መንገድ ሊሠሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ተስፋ ሰንቀዋል::ከዚህ ባለፈም የተዳከመውን የቴያትር ጥበብ ለማነቃቃት በሃገር ቤት የሚካሄደውን ተግባር ደግፈው የሚቆሙበትን ዕድል ለመፍጠር  እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን የቴያትርና ስነፅሑፍ ባለሙያው አለማየሁ አጫውቶናል::

በአጠቃላይ ክብረ በዓሉ ለብዙ ዓመታት በአካል የተለያዩ የሙያ ባልንጀሮችን መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር በአንድ መድረክ ያገናኘና መልካም ዕድል የፈጠረ ልዩ ቀን ነበር::

የዝግጅታችን ተከታታዮች የዛሬው መዝናኛ ዝግጅታችን በዚሁ ተጠናቀቀ::

ታሪኩ ኃይሉ

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ