1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተቃዋሚዎች እና ተንታኞች የሰላ ትችት ገጥሞታል

ሰኞ፣ የካቲት 12 2010

ኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር ኢትዮጵያም ጠቅላይ ምኒስትር እየፈለጉ ነው። አገሪቱ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ የምትመራው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሆኗል። እስካሁን ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዕረፍት አልተጠራም። በፍጥነት በሚቀያየረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በርካታ ጉዳዮች የገዢውን ግንባር ውሳኔዎች ይፈልጋሉ።

https://p.dw.com/p/2swfw
Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. Gebireegziabher

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተቃዋሚዎች እና ተንታኞች የሰላ ትችት ገጥሞታል

የመጀመሪያው በተነሳ በሰባተኛ ወሩ ኢትዮጵያ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ተመልሳለች። የአሁኑ ግን እንደ ቀድሞው አይደለም። በኢሕአዴግ ሹማምንት ውሳኔ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የነበሩ ክሶች ተቋርጠዋል፤ በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የኃይማኖት መሪዎች ተለቀዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣናቸው ሊለቁ መንገድ ላይ ናቸው። ማን እንደሚተካቸው እስካሁን በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም።

በሁለት አመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተቃዋሚዎች እና ተንታኞች የሰላ ትችት ገጥሞታል። አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ "የኢትዮጵያ መንግሥት የመሰብሰብ እና ሐሳብ መግለጽን ጨምሮ መሰረታዊ መብቶች የሚገድብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ የደረሰበትን ውሳኔ በብርቱ አንስማማበትም" ብሏል። ኢትዮጵያ ለገጠሟትፈተናዎች ገደብ ከመጣል ይልቅ በአካታች ውይይት እና ፖለቲካዊ ሒደት መፍትሔ ቢፈለግላቸው እንደሚሻል ኤምባሲው ጠቁሟል። የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እውቅና የተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች እና መሰረታዊ ነፃነቶችን እንዲያከብር ጠይቋል። በብሪታኒያው የኪል ዩኒቨርሲቲ በመምሕርነት የሚያገለግሎት ዶ/ር አወል አሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ከኢሕአዴግ ቃል ኪዳኖች ጋር ለመስማማቱ ጭምር ጥያቄ አላቸው።

"ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ የኹከት የብጥብጥ ተግባራት" በመበርታታቸው የአስቸኳይ ጊዜ ዋጁ መደንገጉን የኢትዮጵያ የመከላከያ ምኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ተናግረዋል። አዋጁ የመከላከያ ምኒስትሩ የጠቀሷቸውንም ሆነ አገሪቱ የገጠሟትን ቀውሶች ለመፍታቱ ማረጋገጫ የለም። ቢያንስ የቀደመው ድንጋጌ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳለው ዘላቂ መረጋጋት አላመጣም። የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ኢትዮጵያ የገጠማት "በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚፈታ ችግር አይደለም"ሲሉ ይሞግታሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመውን ኮማንድ ፖስት በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ከተጣለባቸው ሹማምንት መካከል አንዱ የሆኑት ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ሥልጣናቸውን ሊለቁ መንገድ ላይ ናቸው። የአቶ ኃይለማርያም ተተኪ የሚመረጥበት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ እና ውሳኔ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

የጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ሥልጣን የመልቀቅ ውሳኔ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ ለሚከታተሉ በእርግጥ ዱብ እዳ አልሆነም። የተተኪያቸው ማንነት ግን አገሪቱ ለቆመችበት መንታ መንገድ መልስ ይሰጣል። መፍትሔ አሊያም ሌላ ቀውስ። በገዢው ግንባር ምሥጢራዊ ባሕሪ ምክንያት ቀጣዩን ጠቅላይ ምኒስትር ለመምረጥ የሚደረገው ክርክር ፍንጭ ባይሰጥም ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊሆን ይገባል የሚለው ጉምጉምታ ግን ከፍ ብሎ ይሰማል። ገዢው ግንባር ከውስጥም ከውጭም ያሉበትን ችግሮች እንዳለው በውይይት የመፍታቱ ነገር ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ለሚያሳስባቸው አቶ ክቡር ገና ግን ችግሩ ከኢሕአዴግም በላይ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ