1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ

ሰኞ፣ ጥቅምት 24 2012

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥቅምት 12 ጀምሮ ሲያካሄድ የቆየውን ጉባኤ ዛሬ አጠናቅቋል። በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም የቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ 14 ነጥቦች የያዘ መግለጫ አውጥቷል። ሲኖዶሱ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ችግር እንዲያበቃ የተጀመረው ሱባኤ እንዲቀጥልም ውሳኔ አስተላልፏል።

https://p.dw.com/p/3SRyo
Äthiopien Addis Abeba | Abune Mathias, Patriarch der Orthodoxen Kirche
ምስል DW/G. Tedla

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥት ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳሰበ። ቅዱስ ሲኖዶሱ ለ12 ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ ዛሬ ሲያጠቃልል በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በኩል ዛሬ በሰጠው 14 ነጥቦችን በዘረዘረው መግለጫ ፤ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋት እና የዜጎች ንብረት መውደም፣ በእጅጉ እንዳሳዘነዉ አመልክቷል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ መንግሥት የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ፣ የተፈናቀሉት ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ ለጠፋው ንብረታቸው ማቋቋሚያ እንዲሰጥ፣ በክርስቲያኖች እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለው ስደት እና መከራ እንዲያበቃ እና ጥፋተኞች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ ጠይቋል። ከዚህም ሌላ በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት የሚገኙ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተከታዮች በቋንቋቸው ማስተማር እና ማገልገል እንዲቻል በየአህጉረ ስብከቶቹ የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጿል።

የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ማፍራት እንዲቻል ለትምህርት ቤቶቹ ማጠናከሪያ የሚሆን ቋሚ በጀት እንዲመደብም ወስኗል። ሲኖዶሱ በሁሉም አፍ መፍቻ ቋንቋ በማዕከል ደረጃ ማሰልጠኛ እንዲቋቋም መወሰኑም በመግለጫው ተመልክቷል። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ጌታቸው ተድላ 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ