1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለምን አነከሰ? 

እሑድ፣ ሚያዝያ 16 2014

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ከሥራ ገበያው ፍላጎት የተጣጣመ ዕድል ለመፍጠር ለምን ተሳነው? መረጋጋት በራቃት ኢትዮጵያ፣ የዋጋ ግሽበት በተጫነው ኤኮኖሚ ውስጥ የበረታው ሥራ አጥነት መፍትሔ ካልተበጀለት ምን ያስከትላል? ምንስ ሊደረግ ይችላል? ሥራ አጥነት በኢትዮጵያ ያለበትን ይዞታ በሚዳስሰው በዚህ የእንወያይ መሰናዶ ሶስት ባለሙያዎች ተካፍለዋል። 

https://p.dw.com/p/4AJf5
Afrika junge Männer arbeitslos
ምስል Imago/photothek/T. Imo

እንወያይ፦ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለምን አነከሰ? 

አዲስ አበባ ከሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ደጃፍ ከታዩ መካከል የ3ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደሆነ የተናገረ ወጣት "መማር ዋጋ አለው ብዬ አላስብም" የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። በጥሩ ውጤት የተመረቁ ጓደኞቹ ጭምር አብረውት በቦታው እንደነበሩ ለዶይቼ ቬለ የተናገረው ተማሪ እንደሚለው ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ ለሌላ አገር ተሰልፎ መዋጋት ለእርሱ "የተሻለ ዕድል" ነበር።  በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለሩሲያ ጦር ወታደር ከኢትዮጵያ እንደማይመለምል ቢያስታውቅም ጉዳዩ ግን ሥራ ፈላጊዎች የገቡበትን አሳዛኝ ግፋ ሲልም አሳሳቢ አጣብቂኝ አሳይቷል። 

በኢትዮጵያ ከሚገኙ አርባ አምስት የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ ከ150 ሺሕ በላይ ወጣቶች እየተመረቁ የሥራ ገበያውን ይቀላቀላሉ። በኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ መሠረት የሥራ ገበያው በየዓመቱ በ2 ሚሊዮን ይጨምራል። ይሁንና ባለፉት አመታት ፈጣን ዕድገት አሳየ ሲባል የቆየው ኤኮኖሚ በከተማም ሆነ በገጠር ያለውን ሥራ አጥነት በቅጡ መፍታት የቻለ አይመስልም። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥሮችም ይኸንንው የሚያጠናክሩ ናቸው። በፕላን እና ልማት ኮሚሽን ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት የአስር አመት የልማት ዕቅድ በ2003 በጀት ዓመት 18 በመቶ የነበረው የከተማ ሥራ አጥነት ምጣኔ በ2012 ወደ 18 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ማለቱን ያሳያል። 

ይኸ የእንወያይ መሰናዶ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለምን አነከሰ? ሲል ያጠይቃል። በውይይቱ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ረታ፤ በአሜሪካው ኦሬጎን ዩኚቨርሲቲ  የኤኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ካሳሁን መለሠ እና የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ በቅርበት የሚከታተሉት የፋይናንስ ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ተሳትፈዋል። 

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ