1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መግለጫ

ዓርብ፣ ግንቦት 12 2014

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ከ2011 እስከ 2014 ባሉት ዓመታት በአገሪቱ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚዳስስ መግለጫ ትላንት ይፋ አድርጓል። መግለጫው የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች፣ ማፈናቀል እና በኃይል መሰወርን ጭምር የዳሰሰ ነው።

https://p.dw.com/p/4BdoY
Logo des Ethiopian Human Rights Council
ምስል Ethiopian Human Rights Council

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ተፈጽመዋል ያላቸውን ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያብራራ መግለጫ ትላንት ግንቦት 11 ቀን 2014 ይፋ ,ድርጓል። ኢሰመጉ 39ኛ መደበኛ መግለጫ  በሚል ርዕስ ባሰራጨው መረጃ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በአማራ ክልል እና ሌሎችም ስፍራዎች ተፈጽመዋል ያላቸውን የመብት ጥሰቶችንና የዜጎችን መፈናቀል በዝርዝር አቅርቧል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በትጥቅ የታገዘ ጥቃቶች ዜጎች በተደጋጋሚ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ዳርጓል ሲል በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ተከስቶ የነበሩ ግጭቶች ከፍተኛ ጥፋት ማድረሳቸውን ያስታወሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአንድ አንድ ስፍራዎች የጎሳ ግጭቶችን ማስተዋል የተለደመ ሆኗል ብሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ፣ምስራቅና አማራ ክልልን ከሚዋስኑ ሰሜን ሸዋ ዞኖች በመሬት ይገባኛል ጥያቄ እና በታጣቂዎች በተፈጠሩት ጥቃቶች ሰብአዊ መብቶች መጣሳቸውንና ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ እና ጅባት የተባሉ ወረዳዎች እንዲሁም በምስራቅ ወለጋ ዞን ቢሎ ቦሸ የተባለ ወረዳ ውስጥ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ደርሷል ባለው ማንነት መሰረት ባደረገ ጥቃት በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ጉዳት እንደደረሰባቸው በሪፖርቱ አካቷል።  

በጉዳይ ላይ ከአሮሚያ ክልል መንግስት ስራ ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት በስልክ ያደረኩት ጥረት ስልክ ባለመመለሳቸው አልተሳካም፡፡ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሻፊ ሁሴን በክልሉ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ተፈጽመዋል በተባለው ጉዳይ ላይ በሰጡን ማብራሪያ የህብረተሰቡን አንድነት በማይፈልጉ አካላት ጥቃቶች መድረሳቸውን ገልጸው በክልሉ የሚደረሱ ጥቃቶች በሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች ላይ የደረሰ ጥቃት ነው ብለዋል፡፡

በመስከረም 2011 ዓ፣ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ሶጌ(ሚዥጋ)ና ያሶ የተባሉ ስፍራዎች  23 በሚደርሱ ቀበሌዎች ውስጥ ሰዎች ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ከአካባቢው እንዲወጡ ተደርጎ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችም በወቅቱ ለስምንት ወራት ያህል በምስራቅ ወለጋ ዞን ቆይቶ ወደ ነባር ቀያአቸው እንዲመለሱ ቢደረጉም ንብረታቸው በመወደሙና በመዘረፉ ዜጎች ለከፋ ችግር ተጋልጦ መቆየታቸውን ኢሰመጉ ይፋ አድርጓል፡፡ በነበሩት ግጭቶች የሰዎች ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ማለፉን፣ አካል ጉዳት መድረሱንና ጥቃት አድራሾች ላይ እርምጃ ባለመወሰዱ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያደርሱ እንደነበሩም አመልክተዋል፡፡

በ2011 እና በ2013 ዓ.ም በሁለቱም ወረዳዎች ውስጥ ለተፈጠሩ ግጭቶች፣ ህይወት መጥፋትና ሌሎችም ሰብአዊ መብቶች ጥሰት በትጥቅ የታገዘ መሆኑ  ችግሩን ይበልጥ አስፊ እንዳደረገው በመግለጫው አብራርተዋል፡፡ የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽ ምክትል ኮሚሽነር ኢስፐክተር ምስጋናው ኢንጅፋታ ከሳምንት በፊት ግንቦት 4/2014 ዓ.ም በሰጡን ሀሳብ በካማሺ ዞን በ2011 ግጭት ጋር ተያይዞ በርካቶች ለህግ መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ግጭት በሚስተዋልባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች እንዲካሱ፣ አጥፊዎችም እንዲጠየቁ ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡ በካማሺ ዞን ያሶና ሶጌ ላሉት ተፈናቃዩች መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅና ሁሉን ያማከለ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያቀርብም ኢትየጵ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በመግለጫ አስፍረዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ