1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ግንዛቤ መስጫ መረሃግብር

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2015

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን "ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነት እና ፍትሕ ለሁሉም" በሚል ሲያካሂድ የቆየውን የዚህ አመት ሰብአዊ መብቶችን በፊልም የማስተማር ሥራውን ዛሬ አጠናቀቀ። በእውነተኛ የሕይወት ገጠመኞች ላይ የተሰሩ ፊልሞች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለእይታ ቀርበው በችግሮች መነሻ እና በመፍትሔውም ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

https://p.dw.com/p/4LSgJ
 Ethiopian Human Rights Commission about SNNPR human rights case
ምስል Ethiopian Human Rights Commission

በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ያለዉን ማንነትን ላይ ያተኮረ ግድያና ማፈናቀል መንግሥት እንዲያስቆም ጥሪ ቀርቧል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን "ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነት እና ፍትሕ ለሁሉም" በሚል ሲያካሂድ የቆየውን የዚህ አመት ሰብአዊ መብቶችን በፊልም የማስተማር ሥራውን ዛሬ አጠናቀቀ።

በዚሁ መርሃ ግብር የሰው ልጆች መብቶች ጥሰቶችን የሚያሳዩ በእውነተኛ የሕይወት ገጠመኞች ላይ አተኩረው የተሰሩ ፊልሞች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለእይታ ቀርበው በችግሮች መነሻ እና በመፍትሔውም ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

 Ethiopian Human Rights Commission about SNNPR human rights case
የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ለኢትዮጵያዉያንምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ያነጋገርናቸው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ በቀጥታ የሚሰሩ ተቋማት መሪዎች መንግሥት በመብት ጥሰት ፈፃሚዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲያሰፍን፣ የሰብአዊ መብት ሥራን ከዘመቻ ሥራ ነጥሎ እንዲሠራ ጠይቀዋል።

ጦርነት ላስከተላቸው የመብት ጥሰቶች ፍትሕ እንዲሰፍን እና በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ላይ ያለውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ሰዎችን የመግደልና የማፈናቀል ያልተፈታ ችግርም መንግሥት እንዲያስቆም ጥሪ ቀርቧል። 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የሰብአዊ መብቶችን በፊልም ሰርቶ በተለይ ለወጣቶች ለማስተማር ተቋማቸው የጀመረው ሥራ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ስላለው ተጨባጭ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታም ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

"አዳዲስ የግጭትና ጦርነት ላይ የደረሰውን ችግር መሰረት አድርጎ የሚከሰቱ ጉዳዮች አሉ። አንዳንድ ጊዜ የሕግ ክፍተት ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የማስፈፀም ጉዳይ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ተቋም ያለመኖር ወይም ጠንካራ ተቋም ያለመኖር ጉዳዮች ይኖራሉ" በማለት በተለይ ግጭት የመብት ጥሰቶችን እያባባሰ መሆኑን ተናግረዋል።

Präsentation Ethiopian Human Rights Defenders (EHRDC)
የሰብዓዊ ጉዳዮች ሁኔታ በኢትዮጵያምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥምረት ዋና ዳይሬክተር መሱድ ገበየሁ ለእይታ ከቀረቡት መካከል በስደት ውስጥ ያለውን የዜጎች ሰቆቃ የሚያስመለክተውን ፊልም ካዩ በኋላ "እያንዳንዳችን ስለ ሰው ልጅ ክብር የምንሟገት እንድንሆን ይህ ልምድ እጅግ ጠቃሚ ነው" ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ እና በደቡብ ክልሎች የሚታዩ የእሥር አዝማሚያዎች ትኩረት የሚሹ ናቸው የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ - ኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ ናቸው።

አጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ለማጠናከር ከማስተማር ጎን ለጎን ተጠያቂነትን ማስፈን መሠረታዊ የመንግሥት ኃላፊነት መሆነን አቶ መሱድ በ2ኛው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች የፊልም ፊስቲቫል መዝጊያ ሥና ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ