1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ምርጫና ወጣቶች

ዓርብ፣ ግንቦት 7 2007

ግንቦት በሚደረገዉ በ5ኛው የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ የ58 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች ይፎካከራሉ።36 ሚሊየን 851 ሺህ 650 ዜጎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። የወጣቶች ተሳትፎና አቋምስ እንዴት ነዉ? የዛሬዉ ከወጣቶች ዓለም ዝግጅት ትኩረት ነዉ።

https://p.dw.com/p/1FQSS
ምስል DW/Getachew Tedla HG

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ በደረገዉ መርሐ-ግብር መሠረት፤ ግንቦት16 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ12 ሰዓትእስከምሽቱ12 ሰዓት ኢትዮጵያውያን የብሔራዊና የክልላዊ ምክር ቤቶች ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ድምጽ ይሰጣሉ።ይህ የሚመለከተው ግን እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸውን እና የመምረጥ መብታቸው በህግ ያልተከለከለ እንዲሁም ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበው የመራጭነት ካርድ የወሰዱ ዜጎችን ብቻ ይሆናል።

ባለፉት አስር አመታት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት አስመዘገበች ነዉ የሚባልላት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ህዝቧ ከፍተኛዉን ቁጥር የሚይዘዉ ወጣቱ ነዉ። የኢኮኖሚ እድገቱ የአገሪቱን ወጣቶች ለሚፈታተኑት እንደ ትምሕርት፤ ስራ አጥነት፤ተገቢ ክፍያ፤አመቺ የስራ እና የኑሮ ሁኔታ እጦት፤የኑሮ ውድነት ላሉ ፈተናዎች መፍትሄ አላቀረበም የሚል የሰላ ትችት ይሰነዘርበታል።

ብዙዎች እንደሚሉት ምርጫና ዉጤቱ ለዜጎች ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ከቻለ፤ አሊያም መራጮች በምርጫ ካርዳቸው ለየጥያቄዎቻቸው ተገቢዉን መልስ የማግኘት ነጻነትን ካጎናጸፈ ኢትዮጵያ ዉስጥም ለመንግስታዊ ስልጣን ምረጡኝ ሲሉ የከረሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚገጥማቸው ፈተና አንዱ የወጣቶችን ጥያቄ መመለስ ይሆናል።

አምስተኛው የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ ገና ከዝግጅቱ ጀምሮ እንደ ወትሮው ንትርክ አላጣውም። በምርጫ ታዛቢ ምልመላ፤የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ምዝገባ፤የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀት ክፍፍል፤የምረጡኝ ዘመቻ እና መሰል ጉዳዮች ።

ድምፅ ለመስጠት ካርድ የወሰዱ ወጣቶች ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያ ሲጓዙ ትኩረት ያሻቸዋል የሚሏቸው በርካታ ጉዳዮችም አሏቸው።ዘገባውን በድምፅ ያገኙታል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ