1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ ኤርትራ ድንበርና የኤርትራ መንግሥት

ሐሙስ፣ ግንቦት 30 2010

«ለፕሬዚዳንት አፈወርቂ  200 ሺህ ወታደሮችን መሣሪያ አስታጥቆ በተጠንቀቅ የሚያስቆሙበት ምንም ምክንያት አይኖራቸውም። ጊዜዉ ከባድ እንደሆነባቸዉ እሙን ነዉ። ለሃገሪቱም ቢሆን ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ከባድ ነገር ነዉ። እናም ይህን ያህል ጦር ሠራዊት ይዞ የሃገሪቱ ከፍተኛ በጀት ለጦሩ ወጭ ለማድረግ ሌላ ምክንያት ካላቸዉ አይታወቅም»

https://p.dw.com/p/2z6Re
Karte Ethiopia und Eritrea ENG

«በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ለሚገኙት ሃገራት በሙሉ ተጨማሪ ደኅንነት ማለት ነዉ»

የኢትዮጵያ እና የኤርትራን የድንበር ላይ ጦርነት ለማስቆም የሁለቱ ሐገራት መሪዎች በ1993 አልጀርስ-አልጄሪያ ላይ የተፈራረሙትን ሥምምነት ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ መቀበሏን ይፋ እንዳደረገች የጀርመኑ  «ጌዜልሻፍት ፊውር በድሮተ ፈልከር» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የጀርመናውያኑ የውሁዳን ሕዝቦች መብት ተሟጋች ድርጅት ዉሳኔዉን አወድሶአል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ስልጣናቸዉን ሲረከቡ በገቡት ቃል መሰረት ተግባራዊ ያደረጓቸውን ሥራዎችንም አድንቋል። በሌላ በኩል ይህ የኢትዮጵያ ዉሳኔ ኤርትራን አጣብቂኝ ዉስጥ ሳይከታት እንደማይቀርም ድርጅቱ ግምቱን አስቀምጧል። 

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን የድንበር ላይ ጦርነት ለማስቆም የሁለቱ ሐገራት መሪዎች በ1993 አልጀርስ-አልጄሪያ ላይ የተፈራረሙትን ሥምምነት ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ መቀበሏን እንዳስታወቀች ነበር የጀርመኑ የውሁዳን ሕዝቦች መብት ተሟጋች ድርጅት በአፍሪቃ ቀንድ ለሚደረገዉ የሰላም ጥረት ተጨማሪ ርምጃ ሲል ዉሳኔዉን ያወደሰዉ። በተለይ በሁለቱ ሃገራት ድንበር አካባቢ ከብዙ መከራና ሞት በኋላ ለጉዳዩ መቋጫ በማግኘቱ የኤርትራና የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውሳኔዉን በአዎንታ ይቀበሉታልም ሲል በመግለጫዉ አስቀምጦአል። የድርጅቱ  ኃላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ  ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ዉሳኔዉ ለአካባቢዉ ሃገራት ተጨማሪ የሰላም ማረጋገጫ ነዉ ብለዋል።

«ይህ ትልቅ እመርታ ነዉ ምክንያቱም በአካባቢዉ ሃገራት በተለይ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ለሚገኙት ሃገራት በሙሉ ተጨማሪ ሰላም እና ደኅንነት ማለት በመሆኑ ነዉ።»

ኡልሪኽ ዴልዩስ ይህ የኢትዮጵያ ዉሳኔ የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ስልጣናቸዉን ሊያጡ የሚችሉበት ወሳኝና አጣብቂኝ ሁኔታ ላይ ሊከታቸe እንደሚችልም ተናግረዋል። ውሳኔው ትንሽትዋን ሃገር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጦርነት ይነሳብኛል ከሚል ስጋት ውስጥም ሙሉ በሙሉ እንደሚያወጣት ገልጸዋል።

Deutschland Gesellschaft für bedrohte Völker Logo

«ለፕሬዚዳንት አፈወርቂ  200 ሺህ ወታደሮችን መሣሪያ አስታጥቆ በተጠንቀቅ የሚያስቆሙበት ምንም ምክንያት አይኖራቸውም። ጊዜዉ ከባድ እንደሆነባቸዉ እሙን ነዉ። ለሃገሪቱም ቢሆን ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ከባድ ነገር ነዉ። እናም ይህን ያህል ጦር ሠራዊት ይዞ የሃገሪቱ ከፍተኛ በጀት ለጦሩ ወጭ ለማድረግ ሌላ ምክንያት ካላቸዉ አይታወቅም»

በኤርትራ መንግሥት ወጣቶች ገደብ ለሌለዉ ብሔራዊ ዉትድርና መገደዳቸዉ ፤ ኤርትራውያን በሜዲተራንያንን ባህርን አቋርጠዉ ወደ አዉሮጳ ከሚገቡት የጀልባ ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ እንዲሆኑ ምክንያት ነዉ ሲሉ ዴልዩስ አክለዋል። የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ጫና ጠንክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ዴልዩስ ጫናዉ ሲጠነክር አቶ ኢሳያስ በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ተሃድሶ እንዲካሄድና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ያደርጉ ይሆናል ብለዋል።    

«በቅርብ ርቀት፣ ይህ ርምጃቸው ጎረቤት ኤርትራን ከማረጋጋት ይልቅ እንዳትረጋጋ ሊያደርግ የሚችል እጅግ ብልሃት የተመላው ርምጃቸዉ  ሆኖ ሊታይ ይችላል።»

ኢትዮጵያ እስከዛሬ የድንበር ኮሚሽኑን ዉሳኔ ተግባራዊ ባለማድረግዋ ከኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይሰማ የነበረዉ ክስ ስህተት ነዉ ማለት አይቻልም ነበር ያሉት ዴሊዮስ አሁን ግን ኤርትራ የያዘችዉን 200 ሺህ ጦር መቀነስዋ የግድ ነዉ ብለዋል። የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ ማርቲን ፕላውት ከዚህ በኋላ የተመድ ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል የበኩላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። 

"ይህ በትክክል ከተረጋገጠ  የተባበሩት መንግስታት በአልጀርሱ ስምምነት ላይ እንዳለው በሁለቱ ሃገራት መንግሥታት መካከል ያለዉን ዉዝግብና ግጭትን ለማብቃት ትልቅ ሚና አለው."

ኡልሪኽ ዴልዩስ
ኡልሪኽ ዴልዩስ ምስል GfbV

 ስልጣን በተረከቡበት እለት ለኤርትራ መንግሥት የሰላም ጥሪ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥታቸው የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር አካላይ ኮሚሽኑን ውሳኔ ለመቀበል የደረሰበትን ውሳኔ ተግባራዊ ያደርጋሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ዴልዩስ  ገልጸዋል

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከዛሬ የተናገሩትን ሁሉ በርግጥም ተግባራዊ በማድረጋቸዉ በቀጣይ ይህን የተናገሩትን ነገር ተግባራዊ አድርገዉ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ አጠራጣሪ አይደለም።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያደርጉት ያሰቡትን ነገር በቅድምያ ስለሚያስቡበት የሚሰሩትን ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። በዚህም ምክንያት ይህን ጉዳይ ከሃገሪቱ ጦር ሰራዊት ጋር ከተነጋገሩ እና ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ማስታወቃቸዉ እሙን ነዉ።» 

የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት ዉሳኔ ላይ ያለዉን አስተያየት ለመጠየቅ ያደረግነዉ ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም ጥረታችንን ግን እንቀጥላለን።

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሠ