1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል የመዛወር ውጥን

ረቡዕ፣ ሰኔ 9 2013

የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ወደ ግል የማዞር ሂደት ለማንኛውም ተወዳዳሪ አካል ያለ ምንም ገደብ ለ30 ቀናት ክፍት ማድረጉን መንግሥት አስታውቋል። መንግሥት ሕግ አውጪ፣ አስፈፃሚ፣ የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ብሎም ነጋዴ መሆኑ ከአገልግሎት ቅልጥፍናና ጥራት አንጻር አዋጭ አለመሆኑ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዞር እንዳስገደደ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/3v3S3
Äthiopien | Dr Biruk Taye und Zinabu Yirga
ምስል Solomon Muche/DW

የኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል የመዛወር ውጥን

በዚህኛው የኩባንያው 40 በመቶ ሽያጭ የፍላጎት መግለጫ ማሳወቂያ ሂደት በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ አገልግሎት ለመስጠት ተወዳድረው በቅርቡ ያሸነፉት «ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ» ስብስብ መወዳደር እንደማይችሉም ተገልጿል። መንግሥት 40 በመቶውን የኩባንያውን ድርሻ ለግል ድርጅቶች ፣ 5 በመቶውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማዞር 55 በመቶውንና የአስተዳደር ድርሻውን ይዞ መቀጠል እንደሚፈልግ ሲያስታውቅ በኢትዮጵያ የተሻለ የቴሌኮም ዘርፍ እንዲኖር ውጥን የያዘው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር አካል መሆኑን ደጋግሞ ጠቅሷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያዎች የተቃረነ አቋም አንፀባርቀዋል።
የኩባንያውን ድርሻ በከፊል ለግል ድርጅቶች ማዞሩ ተገቢ ነው የሚሉት ባለሙያዎች ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ የወሰዱት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውጤታማነት ታይቶና ተመዝኖ በሂደት ይሄኛው ሥራ ቢከወን ይሻላል ብለዋል። በተጨማሪም መንግሥት እነዚህን ግዙፍ ኩባንያዎች በብቸኝነት ይዞ መቀጠሉ ከዘመኑ ጋር እንደማይሄድና ብዙም እንቅስቃሴ የማያሳዩትና በመክሰር ላይ ያሉት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለአብነት የስኳር ፋብሪካዎች ለግል ድርጅቶች ድርሻቸው ቢሸጥ ተገቢ ነው ይላሉ።
በሌላ በኩል አንድም አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ ባለመሆኑ ይህንን ግዙፍ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን የለውም፣ በሌላ በኩል ዓለም በኮሮና ተኅዋሲ መናጋት ውስጥ ወድቆ ባለበት በቢህ ጊዜ የተሻለ የሽያጭ ዋጋ ላይኖር ይችላል፣ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ የውስጥም የውጭም ጫና የበረታባት ወቅት ላይ በመሆኗ ሰላም ፣ ደህንነትና የአገር አንድነት ብሎም ሉዓላዊነትን ማስከበር ላይ የምታተኩርበት እንጂ እንዲህ ያለውን ሌላ ኃላፊነት የምትሸከምበት አይደለም በማለት ውሳኔውን ውድቅ ያደርጋሉ። ከዚህም ባሻገር ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የቴሌኮም አገልግሎት እስረኛ በመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮምን ለግል ያውም ለውጭ ድርጅት ማዞር ከአገር ደኅንነትና ሉዓላዊነት አንፃር ችግር ሊያስከትል ስለሚችል ተቋሙ በመንግሥት እጅ ሥር መቆየት አለበት ይላሉ።

Äthiopien Addis Abeba | Ethio Telecom building
ምስል DW/H. Melesse

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ