1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ ሶማሌ ክልል ግጭትና የፌዴራል መንግስት 

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ሐምሌ 30 2010

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት ተቃዋሚዎች ሰሞኑን በድሬዳዋ ባካሄዱት የጋራ ምክክር በክልሉ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም፣ ለፖለቲካዊ ቀዉሱ ተጠያቂ የሆኑ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ እንዲሁም ሌሎች ነጥቦችን የያዘ መግለጫ አዉጠተዋል።

https://p.dw.com/p/32hpC
Äthiopien Soldaten
ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughan

Edited----Oppo. calls for Fed. intervantion in Ethio-Somali Conflict - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት ተቃዋሚዎች ሰባት ነጥቦች የተካተቱበት የአቋም መግለጫ አዉጥተዋል። የሶማሌ ክልል የጎሳ እና የሀይማኖት መሪዎች ፣ እንዲሁም፣ ምሁራን ሰሞኑን በድሬዳዋ ባካሄዱት የሶስት ቀን የጋራ ምክክር ባወጡት መግለጫ በክልሉ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም፣ የክልሉ ልዩ ፖሊስ ይፈፅመዋል ያሉትን አፈናና ግድያ ለማስቆም የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እንዲገባ፣ በክልሉና በኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ግጭት የሚቀሰቅሱትን ለፍትህ እንዲቀርቡ፣ ለክልሉ ፖለቲካዊ ቀዉስ የክልሉ ተጠያቂ ናቸው ያሏቸው ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ፣ አሁን ስልጣን ላይ ያለዉ አስተዳደር ስልጣኑን እስከሚለቅና ሕዝብ የሚፈልገዉ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ ለ2011 ዓም የተመደበው የክልሉ በጀት እንዳይለቀቅ ጠይቀዋል።

የምክክሩ አዘጋጅ የሆኑት አቶ አዳም አላኔ አብይ በክልሉ የቀጠለው የመብት ጥሰት ለአቋም መግለጫው መውጣት ምክንያት መሆኑን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት የአቶ አብድ ሞሃመድ ኦማር አስተዳደር ተቃዋሚዎች አስተዳደሩ ካለፉት ሁለት ዓመት ወዲህ  እየፈጸመ ነው ያሉትን ኢሰብዓዊ ድርጊት ለፌዴራል መንግሥት ቢያሳውቁም፣ እስካሁን በአስተዳደሩ ላይ  «ምንም» ነገር አለመደረጉን አቶ አዳም ተናግረዋል።

ከአራት ወር በፊትም ስለዚሁ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ለማሳወቅ ከ150 ሽማግሌዎች ጋር ባንድነት ወደ አዲስ አበባ ቢያቀኑም ጉዳያቸዉ መፍትሔ ሳያገኝ መቅረቱን ነው አቶ አዳም አክለው የገለጹት። አቶ አዳም እንዳሉት፣ በድሬዳዋ በተጠራዉ የሶስት ቀኑ ምክክር ላይ የተካፈሉት ሰዎች በሙሉ ለማለት ይቻላል በአቋም መግለጫዉ ላይ ተስማምተውበታል። በክልሉ ለቀጠለው ግጭት አቶ አዳም የፌዴራል መንግሥትንም ተጠያቂ አድርገዋል።

አቶ ጋራድ ኡመር ዶን የተባሉ የሰብሳባዉ ተሳታፊ በአቋም መግለጫው ላይ የተጠቀሱትን ሰባት ነጥቦች እንደሚደግፉ ተናግረዋል። እንደ አቶ ጋራድ ኡማር ገለጻ በተለያዩ ዞኖች የሚኖረው የክልሉ ህዝብ መብቱን ለማስከበር በመታገል ላይ ነው።

አቶ ጋራድ ኡማር አሁን በክልሉ የሚታየዉ ግጭት ወደሌላ አካባቢ እንዳይስፋፋ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆም ደግመዉ አሳስበዋል። በአዲስ አበባ የሚኖሩ የሶማሌ ክልል ተወላጆች እና ጉዳዩ ያሳስበናል ያሉ ዜጎች ዛሬ ወደሚመለከታቸዉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመሄድ ድምፃቸዉን ማሰማታቸዉን ያይን እማኞች ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ