1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ግጭት ተፈናቃዮች አቤቱታ

ሐሙስ፣ ጥር 20 2013

በአማራ ክልል ምዕራብ አርማጭሆ አካባቢ የሱዳን ኃይሎች ከፈጠሩት ማፈናቀል ጋር በተያያዘ በምድረ ገነት ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በቂ መኖሪያና ርዳታ አላገኘንም አሉ። ከመተማ እከ ሁመራ ባሉት አካባቢዎች በሱዳን ኃይሎች ተከበን በስጋት ተውጠናል ሲሉም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/3oXRL
Äthiopisch- sudanesische Grenze
ምስል Alemenw Mekonen/DW

የሱዳን ኃይሎች በየቀኑ ወደ መሀል እየተጠጉ ነው ተብሏል

በአማራ ክልል ምዕራብ አርማጭሆ አካባቢ የሱዳን ኃይሎች ከፈጠሩት ማፈናቀል ጋር በተያያዘ በምድረ ገነት ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በቂ መኖሪያና ርዳታ አላገኘንም አሉ። ከመተማ እከ ሁመራ ባሉት አካባቢዎች በሱዳን ኃይሎች ተከበን በስጋት ተውጠናል ሲሉም ተናግረዋል። የአካባቢው ባለስልጣናት ደግሞ አስፈላጊው እገዛ ይደረጋል ብለዋል።

ከጥቅምት 2013 ዓም መጀመሪያ አካባቢ የሱዳን ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ 32 ኪሎ ሜትር ገብተው ሰላም በር የተባለውን አካባቢ በኃይል በመያዛቸው ከ1700 በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በምድረገነት ከተማ እንደሚገኙ አንድ ተፈናቃይ አብራርተዋል፣ ተፈናቃዮች የመኖሪያ ቤት እጥረት እንዳለባቸው፣ የተወሰኑት ደግሞ ወደ ዘመድ መበታተናቸውን አብራርተዋ። የተሰጠው መኖሪያ ቤት አንድ ብቻ በመሆኑ ያንን ሁሉ ተፈናቃይ ለማስተናገድ አይችልም ነው ያሉት።

ሌላው ተፈናቃይ ደግሞ የተሰጠው መኖሪያ ቤት ከ30 በላይ ሰዎችን የማያሰተናግድ እንደሆነና የሚሰጠው እርዳታም በጣም አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። የሱዳን ኃይሎች በየቀኑ ወደ መሀል እየተጠጉ እንደሆነ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው መንግስት መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል ብለዋል። 

Äthiopisch- sudanesische Grenze
ምስል Alemenw Mekonen/DW

በአካባቢው በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ከነበሩ ባለሀብቶች መካከል አንዱ እንዳሉት በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የቀን ሰራተኞች ያለስራ መቅረታቸውን ፣ ብዙ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች ደግሞ ለልመና መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ 
የምድረገነት ከተማ ከንቲባ አቶ አይሸሽም ጎንቼ በበኩላቸው ለተፈናቃዮች የተሰጠው መኖሪያ ትልቅ ግቢና በቂ መሆኑን ተናግረዋል። 

የምዕረብ አርማጭሆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ታደሰ እንዳሉት ተጨማሪ ድጋፍ ለተፈናቃዮች ለማድረስ እየተሰራ እንደሆ አስረድተዋል። የሱዳን ጦር የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ሲያካሂድ የነበረውን ሕግ የማስከበር የተባለውን ዘመቻ እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ማካሄዱ ይታወሳል። 

Äthiopien | Südsudan | Grenzregion Gambela
ምስል Alemenw Mekonen/DW

የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ በትዕግስት እየጠበቀ እንደሆነ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሰሞኑን በሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች አመልክተዋል።

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ