1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎች መንግስትን ተቃወሙ

እሑድ፣ መስከረም 21 2010

ዓመታዊው የኢሬቻ በዓል ዛሬ ከአዲስ አበባ አቅራቢያ በምትገኘው ቢሾፍቱ በድምቀት ሲከበር ወጣቶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተቃውሞዎችን አሰሙ፡፡ በሆራ አርሰዲ ሀይቅ የተሰበሰቡ ወጣቶች መፈክሮች እና ዘፈኖችን በከፍተኛ ድምጽ ሲያሰሙ ተደምጠዋል። በስፍራው የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ተቃውሞውን በዝምታ አልፈውታል።

https://p.dw.com/p/2l4NP
Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎች መንግስትን ተቃወሙ

ወጣቶቹ ያሰሙት ከነበሩት መፈክሮቻቸው ውስጥ «ዶ/ር መረራ፣ በቀለ ገርባ ይፈቱ» ፣ «ኦሮሞዎችን መግደል ይቁም» የሚሉ ይገኙበታል። «ጭቆና በቃን፣ ለኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ለፍርድ ይቅረቡ፣ ነፃነት ለኦሮሚያ» የሚሉም ነበሩበት። ወጣቶቹ ከመፈክሮቻቸው ባሻገር ባለፈው ዓመት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማስታወስ ተንበርክከው፣ እጃቸውን ከጭንቅላታቸው በላይ በማጣመር አሳይተዋል። ጧፍ በማብራትም ሀዘናቸውን ገልጸዋል። 

Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

ተቃውሞቸውን ሲያሰሙ ከነበሩት ውስጥ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው «ወያኔ አይገዛንም፣ ካሁን በኋላ የራሳችንን መንግስት እንፈጋለን» ሲሉ ተናግረዋል። ሌላኛው የበበዓሉ ተሳታፊ በበኩሉ «እንደ ማንኛውም ሰው እና ብሔር ፍትህ እና እኩልነት እንፈልጋለን» ብለዋል። «የወያኔ መንግስት በጣም አስቸግሮናል። በገዛ ሀገራችን ወጥተንም መግባት አልቻልንም» ሲሉ ሌላ ታዳሚ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከወረቀት አልዘለለም ያሉም ነበሩ።

በቢሾፍቱ በመገኘት በዓሉን የተከታተለው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር እንደነገረን የተቃውሞ ድምጸች መሰማት የጀመሩት ከዋዜማው ምሽት ጀምሮ ነው። ትላንት ከምሽቱ ሶስት ሰአት ገደማ በቢሾፍቱ ዋና ዋና ጎዳናዎች በቡድን በቡድን ሆነው እየጨፈሩ  የነበሩ ወጣቶች ድንገት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ዘፈኖች እና መፈክሮች ሲያሰሙ በመንገድ ዳር ንግድ ቤቶች ያሏቸው ሰዎች ሱቆቻቸውን ሲዘጉ ዘጋቢያችን ታዝቧል። በበዓሉ ላይ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና በክልሉ ባንዲራ ላይ ዋርካ የታተመበት ሰንደቅ አላማ ሲውለበለብ ነበር። ዘግየት ብሎ የኦነግ ባንዲራ ሲውለበለብ የበዓሉ ቦታ በከባድ የድጋፍ ጩኸት ሲናወጥ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ተመልክቷል።

ይህ አይነቱ ተቃውሞ እና ባለፈው ዓመት በክብረ በዓሉ ወቅት በደረሰ አደጋ በርካቶች መሞታቸው በከተማይቱ ስጋት እንዲያንዣብብ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖም ያለ የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቅቋል። ይህንንም የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋግጠዋል። አቶ አዲሱ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው «የኢሬቻ በዓል አከባበር በሰላም ተጠናቅቋል» ሲሉ በዘንድሮው በዓል ችግር እንዳልነበር አስታውቀዋል። የበዓሉን ተሳታፊም አመስግነዋል።

ዛሬ ወደ በዓሉ ስፍራ በሚወስደው መንገድ ላይ የክልሉ ፖሊሶች እና ጸጥታ ለማስጠበቅ የተሰማሩ ወጣቶች ታዳሚዎችን እየፈተሹ ሲያሳልፉ ነበር። ወደ ሆራ ሀይቅ ከሚወስደው አደባባይ እስከ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ድረስ በየጥጉ የክልሉን ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች የጦር መሳሪያ እና አስለቃሽ ጭስ የሚተኩሱ መሳሪያዎች ታጥቀው በተጠንቀቅ ሲጠብቁ ዘጋቢያችን ተመልክቷል።

Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ተቃውሞ ያሰሙ የነበሩ የበዓሉን ታዳሚዎች ጸጥታ ለማስጠበቅ ከተሰማሩ ወጣቶች ጋር በመሆን  ለማረጋጋት ሲሞክሩ ተስተውለዋል። በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በድምጽ ማጉያ መልዕክት ሲያስተላልፉ ታይተዋል። «በዓሉን የሰላም ያድርግልን፣ ግጭት ለማንም አይጠቅምም» ሲሉ ተደምጠዋል።

ስለ ኢሬቻ አከባበር እና ተቃውሞ ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር ከስፍራው ያደረሰንን ዝርዝር ዘገባ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 

 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር/ ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ