1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን ፕሬዝደንት ፖለቲካዊ ስብዕናና ሕልፈታቸዉ

ሐሙስ፣ ግንቦት 15 2016

ረኢሲ 63 ዓመታቸዉ ነበር።ባልትዳርና የሁለት ሴቶች አባት።የ85 ዓመቱን የኢራን ላዕላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻሚኒን ይተካሉ ተብለዉ በሰፊዉ ይጠበቁም ነበሩ።የኢራን ፖለቲካዊ መርሕ ብዙዎች እንዳሉት አይቀየርም ነገር ግን ከእንግዲሕ በረኢሲ አይዘወርም።ሞት ቀደማቸዉ።

https://p.dw.com/p/4gCwb
የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሒም ረዒሲ፣ አራት ባለስልጣኖቻቸዉና ሶስት የሔሊኮብተር አብራሪዎች ባለፈዉ ዕሁድ በሔሊከብተር አደጋ ሞተዋል
የማሻድ-ኢራን ሕዝብ ለፕሬዝደንት ኢብራሒም ረኢሲ ሞት ሐዘኑን ባደባባይ ሲገልፅምስል Ilya Pitalev/Sputnik/SNA/IMAGO

የኢራን ፕሬዝደንት ፖለቲካዊ ስብዕናና ሕልፈታቸዉ

 

ባለፈዉ ዕሁድ በሔሊኮብተር አደጋ የሞቱት የኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ረኢሲ በቅድስቲቱ የትዉልድ ከተማቸዉ ማሻድ ዛሬ ተቀበሩ።በሔሊኮብተሩ አደጋ ከፕሬዝደንት ረኢሲ ጋር ከሞቱት 7 ባለስልጣናት መካከል የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴይን አሚርአብዶላሒያን ይገኙበታል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ነገ ደቡባዊ ቴሕራን በሚገኘዉ አብዶላዚም መካነ ቀብር ይቀበራሉ።ኢራን ዛሬ የተቀበሩትን ፕሬዝደንቷን የሚተካ ፖለቲከኛ ከአምስት ሳምንት በኋላ ትመርጣለች።

የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ
                                     

የኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ በአሜሪካ ድሮን፣ በእስራኤል ሚሳዬል፣ በነብሰ ገዳዮች ጥይት፣ በአሸባሪዎች ቦምብ ሳይቲስቶቿን፣ ፖለቲከኞቿን፣ የጦር መሪዎቿን፣ ለቀስተኞቿን ሳይቀር ማጣት በርግጥ አዲሷ አይደለም።ጥር 12፣ 2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የቴሕራን ዩኒቨርስቲ ዕዉቅ የኑክሌር ሳይቲስት መስዑድ ዓሊ መሐመዲ መኪናቸዉ ላይ በተጠመደ ቦምብ ተገደሉ።ቴሕራን አዘነች።ለብቀላ ፎከረችም።

ከ2010ሩ ጥር እስከ 2020 ጥር በሰዉ እጅ የተገደሉ የኢራን ፖለቲከኛ፣የጦር አዛዥና ሙሁራንን ለመቁጠር ይሕቺ ዘገባ ቦታ የላትም።እንደገና ጥር 2020 ግን የጠንካራዉ የአል ቁዱስ ጦር አዛዥ ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒያና ሌሎች የኢራንና የኢራቅ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ባግዳድ ዉስጥ በአሜሪካ ድሮን ታጨዱ።

በአራተኛ ዓመቱ ዘንድሮ ሚያዚያ።እስራኤል እንደተኮሰችዉ በሚታመን ሚሳዬል ደማስቆ-ኢራን ቆስላ ዉስጥ የነበሩ ሁለት የኢራን ከፍተኛ ጄኔራሎችና ሌሎች ባለሥልጣናት ተገደሉ።ለቴሕራን እስላማዊ አብዮተኞች ሌላ ሐዘን፣ ተጨማሪ ዛቻና ቁጭት።የበቀደሙ ዕሁድ ሟቾች ግን ከእስካሁኖቹ በጣም የላቁ ባለሥልጣናት፣ አሟሟታቸዉ እስካሁን እንደተነገረዉ አደጋ ነዉ።የብቀላ ዛቻም የለም።ፕሬዝደንት ኢብራሒም ረኢሲ፣ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴይን አሚርአብዶላሒያን፣ የምሥራቅ አዘርበጃን ክፍለ-ግዛት አገረ ገዢ። የምሥራቅ አዘርበጃን አያቶላሕ፣ የፕሬዝደንቱ የክብር ዘብ አዛዥና ሶስት የሔሊኮብተር አብራሪዎች-ሁሉም አለቁ።ለቀሪዎቹ መሪር ሐዘን

የ63 ዓመቱ የኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ረኢሲ በቅዱስቲቱና በትዉልድ ከተማቸዉ ማሻድ ከመቀበራቸዉ በፊት
የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሒም ረኢሲ ከመቀበራቸዉ በፊት የማሻድ ነዋሪዎች ሐዘናቸዉን ሲገልፁምስል Ilya Pitalev/Sputnik/SNA/IMAGO

                      የረኢሲ ጠላትና ወዳጆች
                                      

ፐሬዝደንት ረኢሲ ለእስራኤልና ለዩናይትድ ስቴትስ፣ የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማቲዉ ሚለር ሰዉዬዉ ከሞቱ በኋላ እንኳን በጥሩ የማይነሱ  ጨቋኝ፣ረጋጭ ነበሩ።
«ኢብራሒም ረኢሲ፣ የኢራን ህዝብን ለ40 ዓመት ያሕል በመጨቆኑ ሒደት ጨካኝ ተካፋይ እንደነበሩ ግልፅ አድርገናል።በ1998 ከፍርድ ቤት ዉሳኔ ዉጪ የተፈፀሙ ግድያዎችን ጨምሮ በበርካታ ጨካኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተሳትፈዋል።» 
ለወዳጆቻቸዉ ግን ብልሕ ዳኛ፣በሳል ፖለቲከኛ፣ ቅን መንፈሳዊ መሪ፣ ጎበዝ አስተባባሪም ነበሩ።«ለኢራን፣ ለእስላማዊ አብዮቷና ለሕዝቧ ኖረዉ-ሲሰሩ ተሰዉ።» አሉ የድሮ አስተማሪ፣ አርዓያ፣ የኋላ አለቃቸዉ አያቶላሕ ዓሊ ኻሚኒ-ትናንት።ከመንፈሳዊ መሪ አባት፣በቅዱስቲቱ ዉብ ከተማ ማሻድ ተወልደዉ በመንፈሳዊ መሪዎች መፈልቂያቱ ቁም ዩኒቨርስቲዎች ተምረዉ ለዶክተርነት የበቁ ነበሩ።
የአያቶላሕ ሩሁላሕ ሆምኒ የመሯቸዉ የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች በ1979 የቴሕራን ቤተ-መንግስትን ሲቆጣጠሩ ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበሩ።ይሁንና ከ20 አመታቸዉ ጀምሮ የእስላማዊ ሪፐብሊኪቱ የተለያዩ ክፍለ ሐገራት ረዳት አቃቤ ሕግ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ የፍትሕ ተወካይ እያሉ የሪፐብሊኪቱ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሆኑ።
በ1998 በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንዲገደሉ የወሰነዉ ልዩ ኮሚቴ አባልም ነበሩ።በ2016 የታላቁ የኃይማኖት ተቋም የአስታን ቁዱስ ረዛቪ የበላይ ኃላፊ ሆነዉ ሲሾሙ በእስላማዊ ሪፐብሊኪቱ ፖለቲካዊ አዉራ ጎዳና የሚያቆማቸዉ እንደሌለ አረጋገጡ።በሺዓ ሐራጥቃ አስተምሕሮታቸዉ  ጠበቅ፣ በፖለቲካ መርሐቸዉ ከረር፣ በአመራር-አሰራራቸዉ ኮምጨጭ ያሉም ነበሩ።ረኢሲ።በ2015 ኢራን 5+1 ከሚባሉት ኃያላን መንግስታት ጋር ያደረገችዉን የኑክሌር ስምምነት ይቃወማሉ።ስምምነቱን ያደረጉትን የያኔዉን ለዘብተኛ ፕሬዝደንት ሐሰን ሩኻኒን ለመተካት በ2017 በተደረገዉ ምርጫ ተወዳድረዉ ነበር።በሩኻኒ ተሸነፉ።

               ሰዉዬዉ ተስፋ አይቆርጡም

 

ተስፋ ግን አልቆረጡም።ፋርስ ተስፋ አይቆርጥም።ቀኝ ፅንፈኛዉ የአሜሪካ ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ ያን መዘዘኛ የኑክሌር ስምምነት አሽቀንጥረዉ ሲጥሉት ደግሞ ረኢሲና ደጋፊዎቻቸዉ «ብለን ነበር» እያሉ፣ በ2021ዱ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የቴሕራን ቤተ-መንግስት ገቡ።

በኢራኑ ፕሬዝደንትና በሌሎቹ ባለሥልጣናት ሞት ጥልቅ ሐዘናቸዉን ከጘለጡ መንግስታት አንዱ የሩሲያ መንግስት ነዉ
ለኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ረኢሲና አብረዋቸዉ ለሞቱ ባለስልሥልጣናት በሞስኮ-ሩሲያ የተዘጋጀዉ የሐዘን መግለጫ መዝገብ ሲፈረምምስል Sofya Sandurskaya/dpa/picture alliance

ረኢሲ ባጭር ጊዜ ዘመነ ሥልጣናቸዉ የቴሕራን-ቴል አቪቭ-ዋሽግተን-ለንደኖችን ጠላትነት አክረርዉታል።የዚያኑ ያክል የቴሕራን-ሪያዶችን፣ የቴሕራን-ባኩ ጠብ አርግበዋል። ቴሕራን-ዶሐ፣ የቴሕራን-አንካራ፣ የቴሕራን-ቤጂግ ከሁሉም በላይ የቴሕራን-ሞስኮን ወዳጅነት አጠናክረዋል።ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የምክር ቤት እንደራሴያቸዉ ወደ ቴሕራን ሲልኩ ያስተላለፉት መልዕክትም የሁለቱን የምዕራብ መንግስታት ጠላት ሐገራትን ጥብቅ ወዳጅነት ያረጋገጠ ነዉ።
                                      
«ታማኝ ወዳጅ ነበሩ።ቀጥተኛ፣ በራሳቸዉ የሚተማመኑ፣ ከሁሉም በላይ ለሐገር ብሔራዊ ጥቅም የቆሙ፣ የሚመሩ፣ ቃላቸዉን አክባሪ ሰዉ ነበሩ።ከሳቸዉ ጋር መሥራት አስደሳች ነበር።ባንድ ጉዳይ ላይ ከተስማማን ስምምነቱን ገቢር እንደሚያደርጉት አንጠራጠርም ነበር።»

ረኢሲ 63 ዓመታቸዉ ነበር።ባልትዳርና የሁለት ሴቶች አባት።የ85 ዓመቱን የኢራን ላዕላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻሚኒን ይተካሉ ተብለዉ በሰፊዉ ይጠበቁም ነበሩ።የኢራን ፖለቲካዊ መርሕ ብዙዎች እንዳሉት አይቀየርም ነገር ግን ከእንግዲሕ በረኢሲ አይዘወርም።ሞት ቀደማቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ