1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ ጉባኤ፤ መፈናቀልና አወዛጋቢው ቃለመጠይቅ

ዓርብ፣ መስከረም 25 2011

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ኤል ቲቪ ከተሰኘ ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለ-መጠይቅ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) 11ኛ ጉባኤውን በአዋሳ ባከናወነበት ሳምንት የዜጎች በየአቅጣጫው መፈናቀል እየተባባሰ መሄድ ጥያቄ አጭሯል።

https://p.dw.com/p/3608e
Äthiopien Addis Abeba - Nama Hauptquartier
ምስል DW/ S. Mantegaftot Sileshi

አወዛጋቢው ቃለ-መጠይቅ

ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) 11ኛ ጉባኤውን በአዋሳ ባከናወነበት ሳምንት የዜጎች በየአቅጣጫው መፈናቀል እየተባባሰ መሄድ ጥያቄ አጭሯል። ከማፈናቀሉ ጀርባ እጃቸው የረዘመው እነማን ናቸው? የሚል ጥያቄ ተጠናክሯል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ኤል ቲቪ ከተሰኘ ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለ-መጠይቅ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። በቃለ-መጠይቁ ሊቀመንበሩን ኾን ተብሎ ለማሳነስ ጥረት ተደርጓል፤ ከንቱ ሙግትም ነበር የሚሉ አስተያየቶች ተበራክተዋል። የለም፤ ሊቀመንበሩ እንዲህ መፋጠጣቸው የጋዜጠኝነት ብቃት መገለጫ ነው ሲሉ የሞገቱም አሉ። ሁሉንም በስፋት ዳሰናል።

በኢትዮጵያ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ መቶ ሺህ መጠጋቱ በርካቶችን አሳስቧል። የተፈናቃዮቹ ቁጥር የኢትዮጵያ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)በአዋሳ ከተማ 11ኛ ጉባኤውን በሚያከናውንበት ወቅት እንዲህ መጨመሩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጥያቄ አጭሯል። መንግሥት ግድያና መፈናቀል ሲከሰት በፍጥነት መልስ መስጠት ይገባዋል ብለዋል።  ጸጋዬ ሂድሩ፦ «መንግሥት ሁሌ ከሦስት ቀን በኋላ ነው የሚደርሰው። ያውም ሕዝቡ ዕድለኛ ከሆነ (ጅጅጋ: ቡራዩ: ቤንሻንጉል/ጉምዝ» ሲል አስተያየቱን በፌስቡክ አስፍሯል።

ጊዮን ፋንታሁን ከሦስት ቀን በፊት ትዊተር ላይ ባስተላለፈውው መልእክቱ፦ «እመኑኝ ሀገሬ የሚያመረቅዝ ቁስለት ዉስጥ ነች» ሲል ስጋትቱን ይገልጣል። «በኦነግ ስም የታጠቁ ሰዎች ደረሰ በተባለዉ ግድያ የተጀመረዉ ችግር ቤንሻንጉል ካማሺ ዞን አካባቢ» ያደረሰውን የሕይወት መጥፋት እና ስደት በመጥቀስም ጊዮን «ሀገሬ ቆስላለች፣ ህክምና ትፈልጋለች» ብሏል።

EPRDF Logo

እሸቱ ሆማ ቄኖ በበኩሉ፦ «በአንድ አመት ውስጥ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት በዓለም አንደኛ ሆንን። ይህ እጅግ አሳዛኝ አሳፋሪና አሸማቃቂ ጉዳይ ነው» ብሏል።

ከቤንሻንጉል ክልል በተጨማሪ በወልቃይት አማሮች ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን የሚገልጡ ጽሑፎችም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭተዋል። መኮንን እዘዘው፦ «በወልቃይት አማራዎች ላይ የሚደርሰዉ በደል የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች /ቤት ተፈናቃዮችን ዋቢ አድርጎ እንደሚከተለዉ ዘግቦታል» ሲል ጽሑፉን አያይዟል። «በትግራይ ክልል በዳንሻ፣ ወልቃይት ጠገዴ አካባቢዎች የሚገኙ በአማራ የወልቃይት ሕዝቦች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ተፈናቃዮች ተናገሩ። ቁጥራቸው 80 በላይ የሆኑ የአማራ ወልቃይት ሕዝቦች በአማረኛ ቋንቋ ለምን ትናገራላችሁ በሚል ሰበብ በትግራይ ልዩ ሀይል ፖሊስ ድብደባና ግድያ እንደተፈፀባቸው ይናገራሉ» ይላል ዘገባው።

ዘሩባቤል በፌስቡክ በሰጠው አስተያየት፦«ኢሕአዴግ ማስቀደም የሚፈልገው ኅልውናውን ከሆነ የሚጠብቀው አንድ እድል ነው። እሱም በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠ አውላላ ሜዳ ነው» ሲል ጽፏል። «በተቃራኒው ኢሕአዴግ ማስቀደም የሚፈልገው የኢትዮጵያን ኅልውና ከሆነ የሚጠብቀው በብርሀን የተሞላ እሾሀማ፣ ገደላማ፣ አባጣ ጎርባጣ የበዛበት የአውላላ ሜዳ መዳረሻ መንገድ ነው። ሁለተኛውን መንገድ መከተል ግድ ቢሆንም የእያንዳንዱን እህት ድርጅት መሪዎችን መለስተኛ ጤናማነት ይጠይቃል። በአጭሩ ጤናማ ሰው መሆን ብቻ ይበቃል» ሲል አክሏል።

«ተፈናቃይ ከምንቆጥር አፈናቃዩን እንፈልገው» ያለው ካሊድ አህመድ ነው። «አዋሳ ቆጥረን ስንጨርስ ቡራዩ ቆጠራ ጀመርን ቡራዩ ስንጨርስ ቤንሻንጉል ገባን ነገስ ምን ሊፈጠር ነው? ስለዚህ አፈናቃዩን መፈለግ ነው መፍትሄው» ሲል አስተያየቱን ደምድሟል።

በዚሁ ሳምንት በኤል ቲቪ የቀረበው የአብን ሊቀመንበር ቃለ መጠይቅ የብዙዎች መነጋገሪያ ኾኗል። እጅግ በብዙ ሺህ የሚገመት ሰዎች የተመለከተው የኢትዮጵያን ዲጄ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የፌስቡክ ገጽ ያቀረበው የቪዲዮ ቅንብር «ሚዲያን በእኩልነት ካልተጠቀምንበት ከፖለቲከኞች ይበልጥ ያጠፋናል» ይላል።  በቪዲዮው የኤል ቲቪ ጋዜጠኛ በተለያየ ወቅት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበርን ስትጠይቅ በመግቢያ ያደረገችው ንግግር ይደመጥበታል።

Mikrofon in der Hand
ምስል Brian Jackson/Fotolia

ጋዜጠኛዋ አቶ ጃዋርን ስታስተዋውቅ በርካታ ቅጽሎችን እንደምታስቀድም ቪዲዮው ያሳያል። «ከእንግዳ ጋር ነኝ። እንግዳዬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረገው፤ ወጣቱ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪው፤ አክቲቪስቱ ጃዋር መሐመድ ነው» ይላል መንደርደሪያው።

የአብን ሊቀመንበር ስታስተዋውቅ በአጭሩ እንደሚከተለው ነበር። «ይኽ ኤል ቲቪ ሾው ነው፤ ከእንግዳ ጋር ነኝ። እንግዳዬ የአብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ) ሊቀመንበር የኾኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ናቸው፤ እዚህ አጠገቤ ናቸው፤ አብራችሁን ቆዩ»  ይላል።

ከቪዲዮው ጋር የተያያዘው የጽሑፍ መልእክት፦ «ከፍትፍቱ ፊቱ» አለ ያገሬ ሰው በሚል ይንደረደራል። ቃለ ምልልሱ «ለምን ትክክል እንዳልነበር ልብ እንበል» በማለት ያብራራል።

«1- ጃዋርን ከያዘው ሆቴል ሩም ሂዳ ኢንተርቪው አደረገቸው ለዛውም ፈራ ተባ እያለች። 2 - የአማራው /መንበር / ደሳለኝ ጫኔ በተጠየቀው መሰረት እሷንና ሚዲያዋን አክብሮ ግሪን ስክሪን ስቶዲዮዋ ተገኙ። 3 - ልዩነቱ - አክብሮ የሄደውን በፍጥጫና በግልምጫ ኩሩውን ጃዋርን በፍራቻ .... ፍርድን ከፖሊታካ ጋር ሳታያይዙ ነገም ለኔ ብለህ እውነታውን ተመልከት» ይላል።

ቻላቸው ታደሰም «የቤቲን ቃለ ምልልስ ሰማነው» በማለት ነው ጽሑፉን የሚያንደረድረው። «ስለ ሀገር ግንባታ አማራ ብሄር ስላደረጋቸው ተጋድሎዎች ያነሳችው ሙግት ከንቱ ነው። ገዳ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ መሠረት መሆኑን እና አሁንም እንድንጠቀምበት የሚሰብኩ ብሄርተኞች የሉም እንዴ? ለማንኛውም ሊቀመንበሩ የመለሰላት መልሶች በቂ ባይሆኑም በጣም የተመጠኑ ናቸው።»

Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

ስለ አማራ ገበሬዎች ድህነት በመኻል ያስገባችው ቁንጽል ቪዲዮ አስቆኛል» ብሏል። በቃለ-መጠይቁ መሀከል ከሌላ የቴሌቪዥን ስርጭት የተወሰኑ የገጠር ቅላጼ ያላቸው ሰዎች ጫማ የማይጫሙት ተቸግረው ሳይኾን ሳይፈልጉ ስለቀሩ መኾኑን ሲገልጡ ይታይበታል። ይህን ምስል በርካታ ሰዎች «በደረቅ ቃለ-መጠይቅ መሀል ያለቦታው በግድ የገባ» ብለውታል። አስተያየት ሰጪዎቹስ ተዓማኒ አስተያየት ስለመስጠታቸው ምን ማረጋገጫ አለው ሲሉ አክለዋል።    

ጋዜጠኛ አክመል ነጋሽ ቀጣዩን አስተያየት ጽፏል። «ቃለ-መጠይቅ አደርጋለው ብለህ (ያውም ሀርድ ቶክ ባለው ዘውግ) ስቱዲዮ ውስጥ መጠየቅ የከበደህን ወይም ልታቀርብ ያልቻልከውን ማስረጃ፣ ቃለ-መጠይቁ በሚሰራጭበት ወቅት ቃለ-መጠይቁን አቋርጦ ተጠያቂውን በሚያሳጣ መልኩ ሌላ ቪዲዮ ማሰገባት የፕሮፌሽናሊዝም ችግር ብቻ ሳይኾን የገለልተኝነትም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡»

የግርማቸው እንየው አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይነበባል፦ «የአማራ ገበሬ መሰረታዊ ጥያቄ በጫማ መኖር አለመኖር ሊያንስ አይገባውም። የአብን ሊቀመንበር አንዳንዴ የሚከፍትላት በር ለጋዜጠኛዋ ተመችቷታል። እንደውም አንድ ቦታ ላይ አልጠየቀችውም እንጂ እኔ ሳዳምጠው አብን አጀንዳው አገራዊ ፓርቲ ነው ብሏል ይህ ከሆነ ከስሙ ብንጀምር ለምን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ አልተባለም ብላ መጠየቅ ትችል ነበር? ምርጥ ጋዜጠኛ ጥሩ ተናጋሪ ሳይሆን ጥሩ አድማጭ መሆን ይገባዋል። ያም ሆነ ይህ በእኔ መስፈርት ቃለ-ምልልሱ ስሜታዊነት ለሚወዱ ቢያስደስታቸውም ብዙ ክፍተት ያለበት መሆኑ የጋዜጠኝነት ልምዴ አስተምሮኛል» ይላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ