1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የክረምት ወራት የዓየር ጠባይ ትንበያ

ሐሙስ፣ ግንቦት 15 2016

ከሰኔ- መስከረም ባሉት ወራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ከመደበኛው በላይ የሆነ ዝናብና የሙቀት መጠን እንደሚከሰት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (IGAD) ትንበያ አመለከተ። የምእራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ የሰሜን ሶማሊያ አንዳንድ ክፍሎችና ሰሜን ምዕራባዊ የደቡብ ሱዳን ስፍራዎች ደረቃማ ዓየር ሊገጥማቸው ይችላል።

https://p.dw.com/p/4gBrE
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ - መንግሥታት (IGAD) አባል አገራት ሰንደቅ ዓላማ
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ - መንግሥታት (IGAD) አባል አገራት ሰንደቅ ዓላማምስል Yohannes G/Eziabhare

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የክረምት ወራት የዓየር ጠባይ ትንበያ

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የክረምት ወራት የዓየር ጠባይ ትንበያ

ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት የክረምት ወራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ከመደበኛው በላይ የሆነ ዝናብ እና የሙቀት መጠን እንደሚከሰት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ - መንግሥታት (IGAD) ትንበያ አመለከተ። በሌላ በኩል ሩቅ የሆኑ የምእራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ የሰሜን ሶማሊያ አንዳንድ ክፍሎች እና ሰሜን ምዕራባዊ የደቡብ ሱዳን ስፍራዎች ከመደበኛው የተለየ ደረቃማ የዓየር ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል ተተንብይዋል። 
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲቲዩት በበኩሉ ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት አካባቢዎች ለግብርና ሥራ እንቅስቃሴዎች ዓወንታዊ ጎን ይኖረዋል የተባለ "ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ሥርጭት እንደሚኖራቸው" የትንበያ ውጤት ማሳየቱን አስታውቋል። 


ተደራራቢ ችግር ውስጥ ያለው ቀጣና 


የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ - መንግሥታት ድርጅት (IGAD) የዓየር ንብረት ትንበያ ማዕከል ሰሞኑን ደቡብ ሱዳን ውስጥ ያደረገውን ውይይት ተከትሎ ባወጣው የክረምቱ ወራት የቀጣናው የዓየር ጠባይ ትንበያ፤ በመካከለኛው እና ሰሜን ኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከቀደመው ጊዜ የበለጠ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል። በኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጅ ኢንስቲትዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምርዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ ተቋማቸው ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች "ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት" ይኖራቸዋል ብለዋል።

ጉዳትም ጥቅምም የቀላቀለው የዓየር ንብረት ለውጥ

የቀጣናዊ ድርጅቱ ትንበያ በሌላ አንፃር በመካከለኛው እና በምእራብ ኢትዮጵያ፣ በሰሜን ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ እና በታንዛኒያ በዚሁ የክረምት ወቅት ከመደበኛው ጊዜ በላይ የሆነ የሙቀት መጠን ሊመዘገብ እንደሚችል አመልክቷል። ከግጭት፣ ከጦርነት፣ ከድህነት፣ ከድርቅ እና በጠቅላላው ከከፋ የዓየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅእኖዎች መላቀቅ ያልቻለው እና የአካባቢው ሕዝብ ለተደራራቢ ችግር  የተጋለጠበት ይህ ከባቢ የማህበረሰቡን ችግርን የመቋቋም አቅም ከፍተኛ አደጋ ላይ ስለመጣሉም ይነገራል። የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲቱዩትከመደበኛ በላይ የሚኖረው ዝናብ ለግብርና ሥራ በጎ ሚና የሚኖረው መሆኑን ገልጿል። "የተለያዩ የግብርና የሥራ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ፣ በሀገራችን ለሚገኙ ወደ 12 የሚደርሱ ተፋሰሶች የውኃ አቅማቸው እንዲጨምር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል" የበልግ እና የበጋ ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችም በተወሰነ መጠን በክረምቱ ወቅት ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ኃላፊው አመልክተዋል።


ጎርፍ በቀጣናው ያደረሰው የጉዳት መጠን

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ኤል ኒኖ የሚያስከትለው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ሆኖ የሚከሰተው ጎርፍ የሚያደርሰው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የቀጣናውን ዜጎች ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን አስታውቃል። ከሳምንት በፊት ጎርፍ በዚሁ ቀጣና ያስከተለውን ገዳት አስመልክቶ ባወጣው መረጃም 473 ሰዎች ለሞት፣ 1.6 ሚሊዮን ዜጎች ተጋላጭ እንዲሁም ወደ ግማሽ ሚሊየን ያህል የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿል። አደጋው በመንገድ፣ በድልድይ፣ እና በግድብ መደርመስ፣ በውኃ መጥለቅለቅና በመሬት መንሸራተት ምክንያት የተከሰተ መሆኑንም አመልክቷል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ